Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ቢሰጠውም ምርታማነት በሚፈለገው መጠን አላደገም ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ብትሰጥም በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ አጠቃቀምና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ምርታማነት በሚፈለገው መጠን አለማደጉን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን አስታወቁ፡፡

‹‹ግብርናን ለበለጠ ውጤት መቅረፅ›› በሚል መሪ ቃል ግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩትና ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ባዘጋጁት የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ ገለጻ ያደረጉት አቶ ዑመር፣ ‹‹ምርታማነትን ለመጨመር ተግተን እየሠራን ነው፣ አሁንም ከዚህ በላይ መሄድ ይጠበቅብናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ግብርናችን ምርታማነት ያንሰዋል፣ ምርታማነት የመሬትና የእህል ብቻ ሳይሆን የሰው ምርታማነትም ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በምርታማነት ከተወሰኑ የአፍሪካ አገሮች ብትሻልም ያላት አማካይ የምርት ግኝት በዓመት 2.5 ሜትሪክ ቶን መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በተለይ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ከሆኑት ታይላንድ፣ ቬትናምና ቻይና ጋር ሲነፃፀር ኢትዮጵያ አናሳ ደረጃ ላይ እንደምትገኝና ይህም ሊታሰብበት እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

‹‹ምርታማነትን ለመጨመር ለምርቱ ግብዓት የሚሆኑ ነገሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ጠንቅቆ ማወቅ ይገባል፡፡ በማዳበሪያ አጠቃቀምም ኢትዮጵያ ከብዙዎቹ አገሮች ያነሰ ድርሻ ነው ያላት፤›› ብለው፣ ለማዳበሪያ አቅርቦት በዓለም ያለው ፈተና የሚታወቅ መሆኑንና ይህም አገሪቱን ወደኋላ የሚጎትት ነው ብለዋል፡፡

ምርታማነትን ጨምሮ የግብርናው ዘርፍ የታቀደውን ያህል ስኬት እንዲያስመዘግብ ያለውን አገር በቀል ዕውቀት በአግባቡ መጠቀም፣ በዘርፉ ያሉ ምሁራን ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት ዋጋ ሊከፍሉ እንደሚገባ፣ ዘርፉ ሀብት ስለሚፈለግ የግሉ ዘርፍ ተበረታቶ እንዲገባ ማድረግ እንዲሁም የፖሊሲና ፕሮግራሞች ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አቶ ዑመር ገልጸዋል፡፡

ይነስም ይብዛ አገሪቱ ሊቆጠሩ የሚችሉ ውጤቶችን ማግኘቷ የተገለጸ ሲሆን፣ እነዚህን ውጤቶች ማስቀጣል እንደሚገባ፣ አዲስ ፕሮግራም ተብለው ይፋ የተደረጉትንና በተለይም የሥነ ምግብ ሁኔታዎችን ሊቀይሩ የሚችሉትን የወተት፣ የዶሮ፣ የሥጋና እንቁላል እንዲሁም የማር ልማት ኅብረተሰቡን በማንቀሳቀስ ጭምር፣ በመጨረሻም ኤክስፖርት በሚታሰብባቸው ምርቶች ላይ ጥራትና ዋጋ ተመጣጣኝ ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

ግብርና ከዚህ በኋላ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ሰዎች ገብተው ድጋፍ ሊያደርጉበት የሚገባ፣ እየገዘፈ ያለና የትኞቹ ዘርፎች ላይ ነው ትኩረት ማድረግ የሚገባው ሊለይ የሚገባው ነው ተብሏል፡፡

ባለፉት አራት የሪፎርም ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት፣ በእንስሳት ሀብት ልማት፣ በገበያ ትስስር፣ በዘርፉ ላይ በሚሠሩ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም በግብርና ፋይናንስ ተቋማት ላይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እንደተሠራበት ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የስንዴ ልማት፣ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ዘመቻ ንቅናቄ፣ የአኩሪ አተር ልማት፣ ቡና፣ ሜካናይዜሽን፣ እንዲሁም ፖሊሲዎች ላይ የተገኘውን ስኬት የባለድርሻ አካላት ውይይቱ ላይ ባቀረቡት ገለጻ አስረድተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያ 36 ሚሊዮን ሔክታር ለእርሻ ሥራ ተስማሚ የሆነ መሬት ያላት ቢሆንም፣ ጥቅም ላይ የዋለው 13.4 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹የእርሻ መሬታችንን አረስርሰው ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ብዙ ወንዞች ቢኖሩንም፣ ሳንጠቀምባቸው በመቅረታችን ለምግብ ተረጂነት ተጋልጠናል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የማኅበረሰቡን ሰብዕና ለማሳደግ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች