Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ የወርቅ መግዣ ዋጋ ሊስተካከል እንደሚችል አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የወርቅ ምርትና ሽያጭን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳ ያለው የፀጥታ፣ የሕገወጥ ማዕድናት ፍለጋና ንግድ ችግሮች  ከተገቱ፣ የወርቅ መግዣ ዋጋ እንደገና ሊያስተካክል እንደሚችል አስታወቀ፡፡

ባለፉት አራት ወራት የበረታ የፀጥታ ችግርና ሕገወጥ ንግድ ወደ ውጭ የሚላከውን የወርቅ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሽቆለቆለ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ ኅዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. የባንኩን የ2015 ዓ.ም. ሩብ ዓመት አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ   ባቀረቡበት ወቅት አስረድተዋል፡፡

ባንኩ በቅርቡ ባደረገው የዋጋ ማስተካካያ ወደ ባንኩ የሚመጣውን የወርቅ ምርት መጠን ለመጨመር አቅራቢዎች በዓለም አቀፍ ገበያ ከሚሸጡበት ዋጋ 35 በመቶ ጨምሮ እየገዛ ቢሆንም፣ አሁን እያጋጠመ ያለው ዋነኛ ችግር ዋጋ ሳይሆን የፀጥታ ችግር መሆኑን ይናገር (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች፣ በተወሰኑ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ወርቅ በሚወጣባቸው አካባቢዎች የሚታየው የፀጥታ ችግር፣ ለወርቅ አቅርቦት መጠን መቀነስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አክለው አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል በወርቅ ምርትና ግዥ ሒደት ውስጥ ከላይ እስከ ታች ባሉ መዋቅሮች በጥቅማ ጥቅም በተሳሰረ አሠራር፣ ሕገወጥ አምራቾች መበራከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህንን ሕገወጥ ሰንሰለት መስበር አስቸጋሪ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ገዥ፣ በሕገወጥ የወርቅ ማምረት ሥምሪት የአገር ውስጥ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ የቻይና ዜጎችም ጭምር በስፋት አሉበት ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሻኪሶ አካባቢ በሕገወጥ መንገድ በተሰማሩ የውጭ ዜጎች ላይ እስራትን ጨምሮ የተለያዩ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡

ከወርቅ ጋር በተገናኘ የመግዣ ዋጋን ማስተካከል አስፈላጊ ከሆነ እንደገና ሊታይ የሚችልበት ዕድል መኖሩን የገለጹት ይናገር (ዶ/ር)፣ ነገር ግን ችግሩ ከዚህ በላይ በመሆኑ የፀጥታ ችግርና ሕገወጥ ንግዱ ካልተፈታ ዋጋ መጨመሩ ዋጋ አይኖረውም ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ባለፉት አራት ወራት ከወጪ ንግድ 977 ሚሊዮን ዶላር፣ ከውጭ አገሮች በሐዋላ ወደ አገር ቤት የተላከ 1.7 ቢሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ሐዋላ 217 ሚሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት መግባቱ ተገልጿል፡፡

ከውጭ አገር የፋይናንስ ግኝት አኳያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ሳቢያ ባለፈው ዓመትና ባለፉት ጥቂት ወራት ከብድርና ዕርዳታ ይመጣ የነበረው ገንዘብ ዝቅተኛ መሆኑን ይናገር (ዶ/ር) ጠቁመው፣ ይሁን እንጂ በፌደራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በተጀመረው የሰላም ሒደት የተሻለ ገንዘብ ወደ አገር ቤት ይገባል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

አገሪቱ ከወጪ ንግድ 977 ሚሊዮን ዶላር ብታስገባም በሩብ ዓመቱ 3.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦች ተገዝተው ወደ አገር ቤት መግባታቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አብዛኛው ነዳጅና የፍጆታ ዕቃዎችን መሆናቸውን አክለዋል፡፡

የስኳር ፋብሪካዎች ከሞላ ጎደል እያመረቱ እንዳልሆነ የገለጹት ገዥው፣ ከተወሰኑት በስተቀር ብዙዎቹ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሥራ ማቆማቸውንና ጥቂቶቹ ደግሞ ከአቅማቸው በታች እያመረቱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ሳቢያ በገበያ ላይ የተፈጠረውን የስኳር እጥረት ለመፍታት መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ በልዩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ መድቦ፣ በዱቤ ሽያጭ አቅርቦቱን ለማሻሻል ከውጭ በመግዛት ወደ አገር ቤት ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች