Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናሕዝብ በሌለበት ሕዝበ ውሳኔ ይካሄድ መባሉን እንደማይቀበለው የቁጫ ምርጫ ክልል አስታወቀ

ሕዝብ በሌለበት ሕዝበ ውሳኔ ይካሄድ መባሉን እንደማይቀበለው የቁጫ ምርጫ ክልል አስታወቀ

ቀን:

በኢዮብ ትኩዬ

ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ይካሄዳል የተባለውን ‹‹የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል›› ሕዝበ ውሳኔ እንደማይቀለው የቁጫ ምርጫ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዓርብ ታኅሳስ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ፡፡

ሕዝብ በሌለበት ሕዝበ ውሳኔ መካሄካድ ስለሌለበት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔን ውድቅ ማድረጋቸውን የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የጋራ ምክር ቤት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ በቀለ አበራ በተለይም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

ኃላፊው ‹‹ምርጫ ቦርድ የደቡብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ አደረጃጀትን በተመለከተ የጊዜ ቀጠሮ ቢሰጥም፣ አስፈላጊው ነገር ሳይሟላ፣ ሕዝብ ተበትኖ ባለበት ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ አግባብ አይደለም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አክለውም፣ ‹‹ውሳኔውን እየተቃወምን ሳይሆን ሕዝበ ውሳኔ የሚደረገው ሕዝብ ሲኖርና በሰላማዊ መንገድ ወጥቶ ሲገባ ስለሆነ ሕዝበ ውሳኔ የተባለውም ሕዝቡ እንዲወስን ሆኖ ሳለ፣ ከፊሉ ሕዝብ ተፈናቅሎ እየተሰቃየ፣ ቀሪው ደግሞ ሕግ አስከባሪ ነን በሚሉ የመንግሥት ኃይሎች እየተደበደበ በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በቁጫ ምርጫ ክልል የ2013 ዓ.ም. ውጤትን ተከትሎ በቁጫ ሕዝብና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው በመፈናቀላቸው ለከፋ ችግር መዳረጋቸውም ተመላክቷል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው የተገኙት የሶዴፓ፣ ኢዜማ፣ ነኢፓ እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሕዝበ ውሳኔ ከመደረጉ በፊት በቁጫ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ፣ የሃይማኖት ተቋማትና ምዕመናን የብልጽግና ፓርቲ አባል የማይሆኑ ከሆነ፣ ‹‹በቁጫ ምድር መኖር አይቻልም ለቃችሁ ውጡ፤›› ማለቱን ተከትሎ በየቀበሌው ከ50 እስከ 60 የሚደርሱ ነዋሪዎች ተለቅመው መታሰራቸውም ተጠቅሷል፡፡

ቦርዱ ሕዝብ ውሳኔ ለማካሄድ ወስኗል ያሉት ኃላፊው፣ ሕዝበ ውሳኔ ሕዝብ በሌለበት እንዴት ይካሄዳል? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

በዚህም፣ ገዢው የብልጽግና ፓርቲ በደቡብ ክልል የሚፈጸመውን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔውን የአካባቢ ምርጫ ቅስቀሳ አስመስለው፤ ‹‹ምርጫ ደርሷል ምረጡ፡፡ የብልጽግና ፓርቲ አባል አልሆንም የሚል ካለ በፍጥነት ከቁጫ ምድር ራሱንና ቤተሰቡን ይዞ ይውጣ፤›› ስለማለቱም ተነግሯል፡፡

መንግሥት ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት በጽንፈኛ የአካባቢው የብልጽግና አመራርና መደበኛ ፖሊስ፣ ቤት ለቤት እየገባ ሕዝብ ላይ ድብደባ እየፈጸመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የቁሕዴፓ ኃላፊ፣ መደበኛ ፖሊስም፣ የሌሎች ፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ‹‹አይደለም እናንተን መደብደብ፣ መግደለም ወንጀል አይደለም፤›› በማለት ፍፁም የፖለቲካ ውግንናን ለገዢው ፓርቲ በማሳየት መላ ዜጋውን እያሰቃየ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም፣ በቁጫ ምርጫ ክልል ከብልጽግና ፓርቲ ውጪ የሌላ ፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደወንጀል ስለመቆጠሩና ‹‹የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ናችሁ›› በመባል የሕክምና አገልግሎት፣ የነዋሪነት መታወቂያ ካርድና ከሴፍቲኔት መርሐ ግብር ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ተደርገዋል ተብሏል፡፡

በአጠቃላይ ‹‹በምርጫ ክልሉ በኢትዮጵያ መንግሥታት ታሪክ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ጭካኔ የተሞላበት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመንግሥት አካላት መፈጸሙን›› የቁጫ ምርጫ ክልል ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በተጨባጭ መገምገማቸውን ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም የቁጫ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚኖረውን ግንኙነት እንዲሁም፣ በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች በሚገዛ የአሠራር ሥርዓት ቃል ኪዳን አንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 4 መሠረት ብልጽግና ፓርቲን ከምርጫ ክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባልነት ከኅዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የሰረዘ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ‹‹የደቡብ ኢትዮጵያን ክልል›› አደረጃጀትን በተመለከተ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ሕዝበ ውሳኔ ለመስጠት መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...