የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማንዋል ያከናወነውን ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ በቀጣይ በሚደረጉ ምርጫዎች የመራጮች ምዝገባና የመራጮች ኦዲት ክንውን በኤሌክትሮኒክስ ምርጫ ለማካሄድ በጀመረው ትልም ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎቸ ሥጋት እንዳላቸው ገለጹ፡፡
ቦርዱ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከጀርመን መንግሥትና ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ለአንድ ዓመት ያህል ሲያዘጋጀው የቆየውንና በሙከራ ደረጃ ይፋ ያደረገውን የመራጮች መዝገብና የመራጮች ኦዲት ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች በተገኙበት ይፋ አድርጓል፡፡
በሙከራ ደረጃ ያለው አዲሱ ቴክኖሎጂ በ2886 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ መሞከሩን በቦርዱ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኃላፊ አቶ ድሪባ መገርሳ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይፋ የተደረገውን የዲጂታል ዘዴ አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሓፓ) ተቀዳሚ ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፣ ቦርዱ ያቀረበው ሶፍትዌር ሰፊ የሆነ ሀብት ተመድቦለት የተረጋገጠ የደኅንነት መረጋገጫ ካልተቀመጠለት፣ የሳይበር ጥቃት ሊደርስበትና ለመጭበርበር ሊዳረግ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ አክለውም ገዥው ፓርቲም በሚፈልገው መንገድ ሊዘውረው ይችላል የሚል ሥጋት አለብን ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት የመጡት አቶ ገብሩ በርሄ በበኩላቸው፣ ከአቅም እንዲሁም በአገሪቱ ካለው የኤሌክትሪክና የቴሌኮም ሲስተም መቆራረጥ የተነሳ የታሰበው ትልም ዓላማውን ሊስት እንደሚችል በመሥጋት ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቶታል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ከአዲስ ትውልድ ፓርቲ የመጡት አቶ ፍቅረ ማርያም ሙሉጌታ በበኩላቸው የታሰበው ኤሌክተሮኒክ ዘዴ ምዝገባ ካለው አገራዊ አቅምና የሕዝብ ብዛት አንፃር መረጃው ለዳታ መዝባሪዎች ሊጋለጥ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ በቅርቡ በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ላይ የወጣውን የመረጃ መጭበርበር በመጥቀስ ፍረጃቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ይሁን እንጂ በቀጣይ አምስት ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህን ሲስተም፣ ቦርዱ ተመልክቶት ወደ ዲጂታል ይቀየር ወይስ በዚሁ የማንዋል አሠራር ይቀጥል የሚለው ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሏል፡፡