የአፍሪካና የአሜሪካ መሪዎች ጉባዔ በመጪው ማክሰኞ ታኅሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ ሲጀመር፣ አሜሪካ የቀዝቃዛውን የዓለም ጦርነት ስህተት በአፍሪካ እንደማትደግም አስታወቀች፡፡ በአጠቃላይ 49 የአፍሪካ አገሮች መሪዎች የሚካፈሉበት ጉባዔ ለሁለት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡ አሜሪካ በተለይም የጆ ባይደን አስተዳደር ለአፍሪካ አገሮች ያለውን ሁለንተናዊ አጋርነት ለማሳየት ትጠቀምበታለች ተብሎ የሚጠበቀው ጉባዔ፣ በርካታ አሳሳቢ የአፍሪካ ጉዳዮች እንደሚነሱበት ተነግሯል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የምግብ ዋስትና፣ የጤና፣ የደኅንነት ጉዳይ፣ በተለይም በአፍሪካ እየጨመረ የመጣው መፈንቅለ መንግሥትና የሽብርተኝነት አደጋ የጉባዔው አጀንዳ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
ስለጉባዔው ከሰሞኑ በኦንላይን መግለጫ የሰጡት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ረዳት ጸሐፊ ሞሊ ፊ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ዳይሬክተር ጁድ ዴቨርሞንት ከአፍሪካ አገሮች ጋዜጠኞች በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለምን በቀጥታ እንዳልተጋበዙ፣ እንዲሁም አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ለምን እንዳልተጠሩ ሁለቱ ባለሥልጣናት ተጠይቀው፣ ስለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ሳይናገሩ አልፈውታል፡፡
ሆኖም ሳይጠሩ ቀሩ ስለተባሉት ማሊ፣ ሱዳን፣ ጊኒ፣ ቡርኪናፋሶና ኤርትራ በተመለከተ፣ ብዙዎቹ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ግንኙነታቸው በመላላቱ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ስለሌላቸው ነው ብለዋል፡፡ ሁለቱ ባለሥልጣናት የአፍሪካ አገሮች በዋናነት በአፍሪካ ኅብረት በኩል እንደሚወከሉ ለማሳመን ሞክረዋል፡፡
የአፍሪካ መሪዎችን የምትሰበሰቡት ከሩሲያ ጋር ለገባችሁበት የጂኦ ፖለቲካ ጦርነት ድጋፍ ለማሰባሰብ ነው ተብለው የተጠየቁት ሁለቱ ባለሥልጣናት፣ አገራቸው የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነትን ስህተት እንደማትደግም ተናግረዋል፡፡ ቅኝ ግዛትና የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በአፍሪካ ያደረሰውን ሰቆቃ የጆ ባይደን አስተዳደር እንደሚገነዘብ የጠቀሱት ባለሥልጣናቱ፣ ያን የመድገም ፍላጎት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል የጆ ባይደን አስተዳደር በአፍሪካ ለተፈጸመው የባሪያ ፍንገላ ሥርዓት ይቅርታ ይጠይቃል ወይ ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ፣ ምላሽ ሳይሰጡ ነው ያለፉት፡፡
በአፍሪካ አሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ አሜሪካ ለአፍሪካ አገሮች የሰጠችው ከቀረጥና ታሪፍ ነፃ ንግድ ዕድል አጎዋ፣ እንዲሁም በቅርቡ የፀደቀው የአፍሪካ አኅጉር ነፃ የንግድ ስምምነት የመነጋገሪያ ጉዳይ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ የአሜሪካ የንግድ ሴክሬታሪ ካትሪን ታይ (አምባሳደር) የኢኮኖሚና የንግድ ውይይት መድረኮችን ይመራሉ ተብሏል፡፡
የአፍሪካ የፀጥታና ደኅንነትና የዴሞክራሲ ጉዳዮች አሳሳቢ እንደሆኑ የተናገሩት ሞሊ ፊ እና ጁድ ዴቨርሞር፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮችም በስፋት እንደሚነሱ ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ ዴሞክራሲ ፍላጎት ከ70 በመቶ በላይ ነው ያሉት ሁለቱ ባለሥልጣናት የዴሞክራሲ፣ የመፈንቅለ መንግሥት፣ የፀጥታና የሽብርተኝነት አጀንዳዎች በዋነኝነት ይነሳበታል ብለዋል፡፡