- ዛሬ እንዴት ትዝ አልኩህ ክቡር ሚኒስትር?
- ልትመዛት ያሰብካት ነገር አለች ማለት ነው?
- እንዴት?
- ክቡር ሚኒስትር ብለህ ጠራኸኛ?!
- ክቡር ሚኒስትር አይደለህም እንዴ?
- እንደዚያ ብለህ በጠራኸኝ ቁጥር አንድ ያልተዋጠለህን ነገር ታነሳለህ። ስለዚህ ዛሬም አንድ ነገር አለ ማለት ነው።
- አንድ ብቻ አይደለም።
- ይኸው…?
- እንዲያው ግን ምን እየሆናችሁ ነው? የምታደርጉትን ነገር ታውቁታላችሁ?
- ምን አደረግን ደግሞ?
- የበለጠ የሚያብከነክነኝ ደግሞ ይኼ ነገራችሁ ነው?
- ምኑ?
- የምትፈጽሙትን ስህተት እንኳን በቅጡ አትገነዘቡትም።
- ስህተት ያልከውን ለምን አትነግረኝም?
- የክረምቱን ዝናብና ቁር ችሎ ሕዝብ ድምፁን በሰጣችሁ ማግስት አናውቅህም አላችሁት?
- መቼ ነው ደግሞ እንደዚህ ያልነው?
- አንድ የሕዝብ እንደራሴ ሰሞኑን ላነሱት ጥያቄ ምን ብላችሁ ነው የመለሳችሁት?
- ምን አልን?
- ሕዝብ ድምፁን የሰጠው ለፓርቲያችን እንጂ እርስዎን ማን ያውቅዎታል ብላችሁ የሕዝብ ተወካይን አላንጓጠጣችሁም?
- ማንጓጠጥ እኮ አይደለም?
- እና ምንድነው? ለዚያውም ለሰፊው ሕዝብ በቴሌቪዥን እያስተላለፋችሁ አይደል እንዴ ያንጓጠጣችሁት?
- አገላለጹን ላትወደው ትችል ይሆናል ነገር ግን በወቅቱ የተባለው ዓለም አቀፍ እውነታ ነው።
- ሆሆ… የሕዝብ ተወካይን ማንጓጠጥ ነው ዓለም አቀፍ እውነታ?
- እንደዚያ ማለቴ አይደለም።
- እህሳ?
- የፓርላማ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ውስጥ ሕዝብ የሚወክለውን ፓርቲ እንጂ ግለሰብን አይመርጥም ማለቴ ነው።
- አርጅቷል ምንም አያውቅም ብለህ ነው?
- ኧረ በጭራሽ? እውነታውን ነው የነገርኩህ አጎቴ።
- እንደዚያ ከሆነ መራጩ ሕዝብ አንድን የሕዝብ ተወካይ አልሠራልኝም ብሎ ሲያምን ማንሳት አይችልም ማለት ነው?
- እንደዚያ እንኳ ማለቴ አይደለም።
- ፓርቲውስ አባሉ የሆነ አንድ የሕዝብ ተወካይን ስላልፈለገው ብቻ ከሕዝብ ተወካይነቱ ሊያነሳው ይችላል?
- ኧረ በጭራሽ። ምናልባት ከፓርቲ አባልነቱ ያሰናብተው ይሆናል እንጂ ከሕዝብ ተወካይነቱ እንኳ ማንሳት አይችልም።
- እና አንድን የሕዝብ ተወካይ ማን ያውቅሃል፣ የተመረጠው ፓርቲያችን ነው ማለት ማንጓጠጥ አይደለም።
- ምን መሰለህ አጎቴ?
- ቆይ ቆይ! ልጨርስ!
- እሺ
- አንድ የሕዝብ ተወካይ እንደዚያ ሲንጓጠጥ ማየቴ ሲገርመኝ ትልቁን ጉድ ዘርግፋችሁት መደበቂያ አጣሁ። አሁን እንደዚያ ይባላል?
- ምንድነው እሱ?
- የአገሪቱ የመጨረሻ የሥልጣን አካል የሆነውን ምክር ቤት በጀት አልሰጠኸኝምና ልትቆጣጠረኝ አትችልም አላላችሁም።
- ቆይ ላስረዳህ አጎቴ!
- ምክር ቤቱ በጀት ባይፈቅድስ? ልማት ተብዬው የመንግሥትና የሕዝብ የጋራ ሀብት በሆነው መሬት ላይ አይደለም የሚገነባው?
- ቆይ አጎቴ ምን መሰለህ ላስረዳህ፡፡
- እንደዚያ ከሆነ ምክር ቤቱ ከውጭ የተገኘ ብድርና ስጦታ አጸደቀ ከምትሉን ስጦታውን ወስዳችሁ ብድር ብቻ አጸደቀ ለምን አትሉንም?
- እንዴት ይሆናል?
- እናንተ ዘንድ ምን የማይሆን ነገር አለ?
- እንዴት? ምን ማለትህ ነው?
- ከአሁን አሁን የሕዝብ ተወካዮቹ ይቃወማሉ ስል….
- እ… ምን ሆነ?
- አጨብጭበው እርፍ!
- ይኸውልህ አጎቴ፣ የፓርላማ ሥርዓትን በሚከተል አገር…
- አታስረዳኝ አልኩህ እኮ። እናንተን የሚያስልፍጋችሁ ሌላ ነገር ነው።
- ምንድነው?
- ትግል ነው!
- ኪኪኪኪ… አይ አጎቴ…
- እውነቴን ነው።
- እንዴት?
- አልተገነዘባችሁትም እንጂ ጊዜው የትግል ሊሆንባችሁ ነው።
- ታዲያ ለምን አትቀላቀልም?
- ምኑን?
- ትግሉን?
- መድኃኒት ላይ ነኝ!
- Advertisment -
- Advertisment -