Thursday, September 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር መቻሉን አስታወቀ፡፡ ባንኩ ባለፉት እሑድ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ከቀረበው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው በ2014 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 1.19 ቢሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል፡፡ ይህ በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ የሚባል ትርፍ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የሒሳብ ዓመቱን የትርፍ ግኝት በተመለከተ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ ዓለማየሁ በሪፖርታቸው እንዳሰፈሩት ‹‹በሒሳብ ዓመቱ ባንካችን በ13 ዓመታት ታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የአንድ ቢሊዮን ብር ጣራን በመሻገር ከግብር በፊት 1.19 ቢሊዮን ትርፍ ተመዝግቧል›› ብለዋል፡፡ 

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ የደረሰበት የትርፍ መጠን ከቀዳሚው የ2013 የሒሳብ ዓመት ከተገኘው በ249.6 ሚሊዮን ብር ወይም 26.6 በመቶ ብልጫ ያለው እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ 

የባንኩን የ2014 የሒሳብ ዓመት ሌሎች አፈጻጸሞችን በተመለከተ ዘርዘር ያለ ሪፖርት ያቀረቡት የቡና ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ዓለማየሁ ሰዋገኝ ባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑም በ32.8 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ 6.7 ቢሊዮን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን የሚያመለክተው የቦርድ ሰብሳቢው ሪፖርት ይህም የባንኩን አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ወደ 27.2 ቢሊዮን ብር ሊያደርሰው ችሏል፡፡ 

ባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በዚህን ያህል ደረጃ ለማሳደግ ከቻለባቸው ምክንያቶች ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ አንዱ በሒሳብ ዓመቱ ብቻ 572,334 አዲስ አስቀማጭ ደንበኞች ማፍራት በመቻሉና አጠቃላይ አስቀማጭ ደንበኞቹን ቁጥር ከ1.9 ሚሊዮን በላይ ማድረስ በመቻሉ ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የከፈታቸው 58 አዳዲስ ቅርንጫፎችም ለተቀማጭ ገንዘብ ዕድገቱ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ስለመሆኑም የባንኩ መረጃ ያመለክታል፡፡ 

ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠን 41.3 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የሚያመለክተው ሪፖርት በሒሳብ ዓመቱ ተጨማሪ 7.6 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር ሰጥቷል፡፡ የባንኩን አጠቃላይ የብድር ክምችት መጠን 25.8 ቢሊዮን አድርሶታል፡፡

ቡና ባንክ ከሚሰጠው ብድር ጋር በተያያዘ የባንኩ አጠራጣሪ ብድሮች (የተበላሸ ብድር ምጣኔ) በተመለከተ የተሰጠው መረጃ የአጠራጣሪ ብድሮች በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 4.1 በመቶ መድረሱን ነው፡፡ 

የቦርድ ሊቀመንበሩ እንዳመለከቱትም አጠራጣሪና የተበላሹ ብድሮች ከጠቅላላው ብድር ያላቸው ድርሻ 4.1 በመቶ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአምስት በመቶ ጣሪያ ያነሰ ነው፡፡ 

ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት የነበረበት የተበላሸ ብድር መጠን 2.4 በመቶ ሲሆን፣ በ2014 የሒሳብ የተበላሸ የብድር ምጣኔው በ2014 የሒሳብ ዓመት ግን ጭማሪ ማሳየቱን ከባንኩ ሪፖርት መረዳት ትችሏል። በቀዳሚው ዓመት የባንኩ የቀድሞ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ሪፖርት መሠረት ‹‹ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት የነበረ ሲሆን በ2013 የሒሳብ ዓመት ግን ወደ 2.4 በመቶ መውረድ ችሏል›› በሚል ገልጸውት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ 

የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በተመለከተ በቀረበ ሪፖርትም እንደ አብዛኞቹ ባንኮች የቡና ባንክም የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ ቅናሽ ታይቶበታል፡፡ 

ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን 149.1 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም በቀዳሚው ዓመት ተገኝቶ ከነበረው የ14.8 ሚሊዮን ዶላር በ9.1 በመቶ ቅናሽ ታይቶበታል፡፡ የባንኩ የተከታታይ ዓመት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩትም የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከዓመት ዓመት ቅናሽ እየታየበት መምጣቱን ነው፡፡ ለዓብነትም ባንኩ በ2011 የሐሲሳብ ዓመት 194 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ አግኝተ የነበሩ ሲሆን በቀጣዩ 2012 የሒሳብ ዓመት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ደግሞ 160 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በ2013 የሒሳብ ዓመት 164 ሚሊዮን ዶላር ያገኘው ቡና ባንክ፣ በተጠናቀቀው 2014 የሒሳብ ዓመት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ 149.1 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የባንኩ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ቅናሽ ያሳየበትን ምክንያት አስመልክቶ የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር ለጠቅላላ ጉባዔው በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹በ2014 የሒሳብ ዓመት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ካለፈው የሐሳብ ዓመት ቅናሽ ያሳየበት መሠረታዊ ምክንያት የጥቁር ገበያ መስፋፋትና ያልተመጣጠነ የግዥ ዋጋ ነው›› ብለዋል። አያይዘውም ኮቪድ-19 በዘርፉ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ አሁንም በውጭ ምንዛሪ ግኝት በኩል ባንኩ በሚፈለገው መንገድ እንዳይጓዝ እንቅፋት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ 

ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ ገቢውን በ37.6 በመቶ በማሳደግ 4.54 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን ወጪው ደግሞ በ42.1 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ በሒሳብ ዓመቱ 3.35 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ 

የባንኩ ዓመታዊ ገቢ በ1.25 ቢሊዮን ብር ጨምሮ 4.5 ቢሊዮን ብር ቢደርስም በተመሳሳይ ከፍተኛ ወጪ የተመዘገበበት የሒሳብ ዓመት እንደነበር የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር በሪፖርታቸው ጠቁመዋል።

ለወጪ ጭማሪው ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያም፣ ‹‹በ2014 የሒሳብ ዓመት በዋናነት ለአጠራጣሪ ብድሮችና ለእርጅና ቅናሽ የተያዘው መጠባበቂያ ካለፈው የሒሳብ ዓመት በ992.1 ማሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየቱ የባንኩ አጠቃላይ ወጪ 3.35 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፤›› ብለዋል፡፡ ቡና ባንክ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የሀብት መጠኑን በ31.4 በመቶ በማሳደግ 34.1 ቢሊዮን ብር ማድረሱን የሚያመላክተው የባንኩ መረጃ፣ የተከፈለ ካፒታሉን ደግሞ ከቀዳሚው ዓመት በ32 በመቶ ወይም በ807.5 ሚሊዮን ብር በማሳደግ 3.3 ቢሊዮን ብር ማድረሱን ጠቁሟል፡፡ 

ቡና ባንክ በአሁኑ ወቅት የቅርንጫፎችን ቁጥር 343 ያደረሰ ሲሆን ከ2,900 በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች