በላቀው በላይ
በዚህ ክፍል ስለዳኝነት ሥርዓታችን ተቋማዊ ሥነ ልቦና (Organizational Psychology in the Judiciary) እና ተያያዥ ጉዳዮች ለመመልከት ይሞከራል፡፡ ተቋማዊ ሥነ ልቦና በተቋሙ ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች የሥራ አካባቢያቸውን የሚያዩበትን፣ የሚያስቡትን፣ የሚያደርጉትን፣ እርስ በርሳቸው የሚግባቡበትን ሁኔታ የሚመለከት ስለመሆኑ ከዚህ በታች ከሰፈረው መረዳት ይቻላል፡፡
“Broadly speaking, organizational psychology deals with various aspects of people’s behavior and attitudes and connects them to functions and productivity in an organizational setting. In other words, it is about how employees experience their environment and how they think, feel, behave, act, and interact in the organizational environment.”
ተቋማዊ ሥነ ልቦና የብዙ ነገሮች ተዋጽኦ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ተቋማዊ ሥነ ልቦና በአንድ ወንዝ መልክ፣ ጣዕምና ይዘት ሊመሰል ይችላል፡፡ ወንዙ የብዙ ጅረቶች ተዋጽኦ ነው፡፡ አንዱ ጅረት ንፁህ የምንጭ ውኃ ይዞ ወደ ወንዙ ሲቀላቀል ሌላው የደፈረሰ ውኃ ይዞ ይቀላቀላል፡፡ ሦስተኛው ጅረት የሽንት ቤት ፍሳሽ፣ አራተኛው ጅረት ሕይወት አጥፊ ኬሚካል፣ አምስተኛው ጅረት ደግሞ በሽታ ተሸካሚ ተውሳክ ይዞ ወንዙን ሊቀላቅል ይችላል፡፡ ወንዙ መልኩን፣ ጣዕሙንና ይዘቱን የሚያገኘው ከዚህ ሁሉ የጅረቶች ስብስብ ነው፡፡ ወደ ዳኝነት ተቋማዊ ሥነ ልቦና ስንመጣ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚል አባባል አለን፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከነፃነት ታሪካችን ጎን ለጎን አንድ የተፈጸመብን ሴራ የነበረብን ስለመሆኑ ይህ አባባል ያስረዳል፡፡ የነፃ አገር ዜጎች እንደመሆናችን መጠን ‹‹ሲሾም ያልሠራ ሲሻር ይቆጨዋል›› ልንል ሲገባ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› እንድንል ተደርገናል፡፡ አለመሥራትን ሆኖም ግን መብላትን የሚያበረታታ ሴራ ከየት እንደመጣብን ታሪካችንን ወደ ኋላ መለስ ብለን መመርመር ይኖርብናል፡፡ እንደመነሻ ግብፆችን ልንጠረጥር እንችላለን፡፡
ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለውን የተቀበለው ሰፊው ኅብረተሰባችን ሹመት የሕዝብ ማገልገያ መሣሪያ ሳይሆን የራሱ የሹሙ መጠቀሚያ፣ የወገኖቹ (የዘመዶቹ) ደግሞ ማስፈራሪያ፣ መከበሪያና መፈሪያ አድርጎ ወስዶት ቆይቷል፡፡ አሁንም ይህ ዝንባሌ በኅብረተሰባችን በሰፊው ይታያል፡፡ በስጋውና በአጥንቱ ሹመኛ ዘመድ ያለው የሹም ዘመዱን ስም እየጠራ፣ ሹመኛ ዘመዱ የሚበላውንና የሚለብሰውን ከጠዋት እስከ ማታ እያወራ ጎረቤቶቹን ሲያስፈራራበት ኖሯል፡፡ ሹመኛ ዘመድ የሌለው ደግሞ ከሹመኛው ጋር የጥቅም ወዳጅነት ለመመሥረት ለሹሙ ነጭ እየጫነ፣ ሙክት እየጎተተ፣ ማርና ቅቤ እየተሸከመ ቤተሰቡን ሲያስርብ ኖሯል፡፡ በገጠርም ሆነ በከተማ ይህ ልማድ በእጅጉ የተለመደ ነበር፡፡ በዚህ ልማድ ተወልዶ ያደገው ልጅ ዛሬ የፍርድ ቤት ዳኛ ነው፡፡
አብዛኞቻችን ኢትዮጵያዊያን ትምህርትን የተማርነው የጋራ ችግራችንን ለመፍታት ሳይሆን፣ የግል ችግራችንን ለማራገፍ መሆኑ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ለግላችን ትምህርትን ስንማረውም ምን እሠራበታለሁ በሚል ሳይሆን ምን እበላበታለሁ፣ ምን ይበላበታል በሚል ስለመሆኑም የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ሰው የሕግ ትምህርቱን ሲማር ስለራሱ ምን እያሰበ እንደተማረ፣ ስለራሱም ሌሎች ሰዎች ምን እየነገሩት ሕጉን እንደተማረ መገመት እንችላለን፡፡ ከከሳሹም ከተከሳሹም ቢዝነስ አድርጌ በሦስት ዓመት ችግሬን አራግፋለሁ እያለ ሕግን የተማረ፣ ከከሳሹም ከተከሳሹም ቢዝነስ ሠርቶ ቤተሰቦቹን በሦስት ዓመት ያሳልፍላቸዋል እየተባለ ሕግን የተማረ ልጅ/ሰው አሁን የፍርድ ቤት ዳኛ ነው፡፡
የዛሬውን አያድርገውና በ1983 ዓ.ም. ወያኔ የመንግሥት ሥልጣን እንደያዘ ፍርድ ቤትን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም በሚል ሊያቋቁመው የማይችል መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ወያኔ ፍርድ ቤትን በወረቀት ላይ ነፃና ገለልተኛ አድርጎ ያቋቋመው ቢሆንም፣ በተግባር ፍርድ ቤቱን የተገለገለበት ለሁለት ጉዳይ ነው፡፡ አንዱ ይህ ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤት አቋቁመንላችኋል እያለ ከፈረንጆች ዕርዳታና ብድር ለማግኘት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን በሐሰት እየወነጀለና እየከሰሰ ምን እናድርግ ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ብሎ ማረሚያ ቤት ወረወራቸው እያለ ለማላገጥ ነበር፡፡ ለዚህ ዓላማው በመሣሪያነት እንዲያገለግሉት በዳኝነት የመለመላቸው የሰለቹ የገጠር አስተማሪዎችንና ፈተና የወደቁ የወያኔ ሽርጥ አገልዳሚዎችን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የዳኝነት ሥራ በምርጫና በፍላጎት፣ በነፍስ ጥሪ የሚከናውን ቢሆንም ወያኔ የዳኝነት አካሉን የደጋፊዎቹና የካድሬዎቹ የደመወዝ መክፈያ ተቋም አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡ በነፍስ ጥሪና በዕድሜ ልክ ዝግጅት በሚገኘው የዳኝነት ሥራ ላይ በወያኔ ድልድል የተመደቡ ዳኞች ዛሬም በሁሉም የፍርድ ቤት ደረጃ በዳኝነት ይሠራሉ፡፡
ከእነዚህና ከመሳሰሉት ገጽታዎች የተሰባሰበው የዳኝት አካሉ ሥረ ሥነ ልቦና (Inner Core Psychology) በነፃና ገለልተኛ ዳኝነት ጥላ ሥር (Under the Auspices of an Independent and Impartial Judiciary) የፍትሕ ገበያ ማስፈን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለታሪኩ የኢፌዴሪ ጠቃላይ ሚኒስቴር ክቡር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን እንደመጡ ‹‹የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ፍትሕን በገንዘብ ሲቸበችብ ነበር፤›› በማለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሰሙት ንግግር ማስረጃ ሲሆን፣ ለአሁኑ ፍትሕን በገበያ የሚያቀላጥፉ የይግባኝ ሰሚና የሰበር አጣሪ ችሎቶችን በማስረጃነት ልንጠቅስ እንችላለን፡፡ ያለ ምንም ምክንያት ፀና/ተሻረ የሚልን ይግባኝ ሰሚና ሰበር አጣሪ ችሎት ፍትሕን በገበያ ያቀላጥፋል ከምንለው በቀር፣ የዳኝነት አገልግሎት ይሰጣል ልንለው አንችልም፡፡ ፍትሕ በግልጽ አደባባይ የሚደረግ ብቻ ሳይሆን፣ በግልጽና በበቂ ምክንያት የሚሰጥና የሚከለከል ነው፡፡ አንድ ሰው በደፈናው፣ ያለ ምንም ምክንያት፣ ያለ በቂ ምክንያት የጠየቀውን ፍትሕ ከተከለከለ ይህ ሰው ጉዳዬ ለገበያ ውሏል ለማለት ሥልጣን ያገኛል፡፡
ሰውዬ ጉዳዬ ለግብይት ውሏል እንዳይል፣ ይህንን የማለት ሥልጣንም እንዳያገኝ ከተፈለገ የጠየቀው ፍትሕ በግልጽ ተብራርቶ ሊሰጠው ወይም ሊከለከል ይገባል፡፡ ጸሐፊው በግልጽ አደባባይ ያልተደረገን ፍትሕ፣ በግልጽ ተብራርቶ ያልተሰጠን ወይም ያልተከለከለን ፍትሕ የተሸጠ ወይም የተገዛ ፍትሕ አድርጎ ነው የሚረዳው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፍትሕ ገበያውን አናስደፍርም የሚሉ የፍትሕ ገበያው ተከላካይና ጠባቂ (Defender and Guardian of the Justice Market) አካላት በስፋት መታየት ጀምረዋል፡፡ አንዱ በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም. በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ሌባ የለም በሚል በሸራተን አዲስ የተሰጠው መግለጫ ነው፡፡ በሸራተን አዲስ ሌባ የለም በማለት መግለጫ የሰጡ አካላት እየሮጡ ሄደው ‹‹በዳኝነት አካሉ ውስጥ የሚታይ ሌብነትን መቆጣጠሪያ ደንብ፤›› የሚል ደንብ አፅድቀዋል፡፡ የፍትሕ ገበያው ተከላካይና ጠባቂ ከመካከሉ አንዱን ወይም ሁለቱን መስዋት በማድረግ የገበያውን ልዕልና ለማስቀጠል ሲል በሕገ መንግሥቱ እንደ ነፃ የመቆጠር መብት ያላቸውን ተጠርጣሪ ዳኞች በሚዲያ ሲወነጅል ታይቷል፡፡
አሁን ያለውን የዳኝነት አካል ለ30 ዓመት በአንድ ጎኑ እንደተኛ፣ እጁን፣ እግሩን፣ ፊቱን፣ አካሉን ለ30 ዓመት እንዳልታጠበ፣ ለ30 ዓመት ፀሐይ እንዳልሞቀ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ ከፈነጠቀው ሥልጣኔ እንዳልተቋደሰ ታማሚ ሰው አድርጎ መረዳት ይቻላል፡፡ የዳኝነት አካሉ ዘመን ካፈራቸው የሥራ አመራር መርሆዎች የራቀ፣ ከድክመቱ ለማወቅና ለመማር ያልተዘጋጀ፣ በውስጡ የተከበሩና የሚደመጡ፣ የሚታመኑ ሰዎችን ለማፍራት ያልቻለ፣ በዘሙኑ በአስፈጻሚው ጉያ ውስጥ ተሸጉጦ የራሱን ማንነት ያልገነባ፣ የሕዝብን አመኔታ ያላገኘ፣ ከእሱ የሚጠበቁ የጥናትና የምርምር ውጤቶች የሌሉት፣ ፖሊስን ለማዘዝ በመቻሉ ብቻ በከንቱ እጁን በኪሱ ከቶ የሚንጠራወዝ ሰው አድርገን ልንደራው እንችላለን፡፡ የዳኝነት አካሉ በአስፈጻሚው ተንከባካቢነትና ሞግዚትነት እንደ ጣኦት እየተመለከተ፣ እንደመብረቅ እየተፈራ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እግሩ ሥር እየተነጠፈለት ሰጪና ነሽ፣ ሰዳቢና አዋራጅ፣ አሳሪና ፈቺ የመሆን ምኞት አለው፡፡ አሁን ለዳኝነት አካሉ የራስ ምታት የሆነበት በአስፈጻሚው በመሣሪያነት አለመፈለጉና ስለሁሉም ነገሩ የአስፈጻሚውን ቡራኬ ማጣቱ ነው፡፡
አሁን ያለውን የዳኝነት አካል በስታትስቲክስ የሚጫወት ሆኖ ይታያል፡፡ ስታትስቲክስ በአግባቡ ሳይንስ መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ነው፡፡ ስታትስቲክስ ያለቦታው ጥቅም ላይ ሲውል ሸፍጥ (እውነታን መደበቅ) ያስከትላል፡፡ አሁን የዳኝነት አካሉ ስታትስቲክስን እየተጠቀመበት ያለው መንገድ አንድም “አላዋቂ ሳሚ… ይለቀልቃል” አለያም “የ… ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያወልቅ” በሚያስብል መልኩ ነው፡፡ ዜጎች ርቃናቸውን የወጡበት የፍርድ መዝገብ እየተቆጠረ፣ በአንድ ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤት ለሰበር ከቀረቡ መዝገቦች መካከል ከአሥር በመቶ በላይ ለሰበር ያስቀርባል ሊባል አይገባም የሚል አቋም ተይዞ የ90 በመቶ የሰበር ቅሬታ አቅራቢዎች መዝገብ በከንቱ (in vain) እንዲዘጋ በተደረገበት፣ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ጉዳዮች እንጂ ስለግለሰቦች ዕንባ አያገባውም የሚል አቋም ተይዞ በዘፈቀደ የተዘጋ የመዝገብ ብዛት የዳኝነት ሥርዓቱ የውጤት መለኪያ ሆኖ ቀርቧል፡፡ አሁን ያለው የዳኝነት ሥርዓታችን ዕንባ አብሶ ሳይሆን፣ ዕንባ እንዲፈስ አድርጎ ውጤታማ ነኝ የሚል ሆኗል፡፡ አገር አለን፣ ሕዝብ አለን፣ ትውልድ አለን፣ የሚሉ የፍርድ ቤት ኃላፊዎች የዳኝነት ሥራን በስታትስቲክስ መለካት ትርጉም የለሽ ደግሞም መሠረታዊ ስህተት መሆኑን ከዚህ እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡
‹‹Courts are not sausage factories. Cases are not mere statistics. The real work of the courts in society cannot be totaled up and measured by an arbitirary business tools. Each case before a court of law involves a controversy that the court must resolve as the institution in which every member of the community must have confidence. There is no simple answer to the question whether the quality of a judiciary can be measured. If the question is addressed qualitatively, the answer may be yes. This is because a society that Values and has confidence in its judiciary as adhering to the core values will have and see the quality. But if the question is addressed to quantitative measures, the answer is an emphatic no. That is because courts do not perform function that is susceptible to quantitative evaluation. Of course any attempt at comparison would be not only meaningless, it would be fundamentaly misleading.››
መልዕክቱ የፍርድ ሥራ መኮሮኒ የማምረት ሥራ አይደለም፣ ሰባት ኩንታል መኮሮኒ አምርቼ ስድስት ኩንታል ሸጥኩ፣ አፈጻጸሜ 85 በመቶ ነው የምትልበት ሥራ አይደለም፣ ፍርድን በስታትስቲክስ መጫወት ትርጉም የለሽ ከመሆኑም በላይ መሠረታዊ ስህተት ነው፡፡ የፍርድ ጥራት በስታትስቲክስ የምትደምረውና የምትቀንሰው ሳይሆን፣ ሰዎች በዓይናቸውና በልባቸው የሚያዩት ነው፣ የፍርድ ውጤትና ጥራት የሚለካው ፍርድ ቤቱ በሕዝብ ዘንድ ባለው መታመን ላይ ብቻ ነው የሚል ነው፡፡
አሁን ባለው የፍርድ ቤት ሥርዓት ውስጥ ተቀበለኝ ልጠብቅህ የሚለው የዳኞችና የፍርድ ቤቱ አመራሮች የሥነ ልቦና ትስስር ይታያል፡፡ ሕዝብ ለፍርድ ቤቱ ከሰጠው እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የተነሳ አሁን ያሉትን የፍርድ ቤት አመራሮች በፍርድ ቤቱ አመራርነታቸው አይቀበላቸውም፡፡ ሕዝቡ በፍርድ ቤቱ ችግር ዙሪያ ከፍርድ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ለመወያየት ፍላጎት የለውም፡፡ በእርግጥም ችግር ፈቺ አመራሮች ናቸው ብሎም አይረዳቸውም፡፡ ሕዝብ ስለፍርድ ቤቱ ችግር የት እንሂድ፣ ለማን እንናገር እያለ እየተጨነቀ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሕዝብ የፍርድ ቤቱን አመራሮች ትቶ ወደ ሚዲያዎችና ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚሄደው፡፡ በአፍ ከሚነገረው፣ በጆሮ ከሚሰማው ባለፈ ራሳቸው የፍርድ ቤት አመራሮች በበርካታ የሚዲያ አማራጮች ቀርበው ሕዝብ ተመልክቷቸዋል፡፡
የፍርድ ቤቱ ሕገ መንግሥታዊ መታመን በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳው የፍርድ ቤቱ አመራሮች በሚዲያ ቀርበው ባሳዩት አለመታመን ነው፡፡ አንድ የፍርድ ቤቱ ኃላፊ እ.ኤ.አ. November 19 ቀን 2022 (ኅዳር 10 ቀን 2015 ዓ.ም.) ከሪፖርተር ጋዜጣ የእንግሊዝኛው ዕትም ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ለተመለከተ የአመራሩ መታመን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ ኅዳር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀይ መስመር ክፍለ ጊዜ የቀረቡት የፍርድ ቤት ኃላፊ በጋዜጠኛው የቀረበላቸውን ጥያቄ ላለመመለስ፣ ትልልቅ እውነታዎችን ለመደበቅ ከጋዜጠኛው ጋር ሲታገሉ ታይተዋል፡፡ ከመልክሽና ከሙያሽ የቱን ትመርጫለሽ ቢሏት መልኬ ይመር እንጂ ሙያስ ከጎረቤት እማራለሁ አለች እንደተባለው ዕውቀቱ እንኳን በሒደት ሊሟላ ይችል ነበር፡፡ መታመን ጎድሎ መታየቱ ግን ሕዝብን ተስፋ ያስቆረጠ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያትም የፍርድ ቤቱ ኃላፊዎች ከዛሬ ነገ ይነሳሉ/ይለቃሉ የሚለው የሕዝቡ የዘወትር ወሬ ሆኗል፡፡ የፍርድ ቤቱ አመራሮች በዳኞች ዘንድም ተቀባይነት የሌላቸው ስለመሆኑ በሰፊው ይነገራል፡፡ ሆኖም ግን ሁለቱም ዘንድ ችግሩ ስላለ አመራሩና ዳኞች አትድረሱብን አንደርስባችሁም፣ ተቀበሉን እንጠብቃችሁ በሚል የተማማሉ ይመስላሉ፡፡
አንድ ሰው በዳኛ ላይ ቅሬታ ገጥሞት ወደ አመራሩ ቢሮ ቢሄድ አመራሩ ሥራ ላይ ናቸው ወይም የሉም ተብሎ ይመለሳል፡፡ ከለውጡ በፊት የነበረው አመራር ከሞላ ጎደል ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ የሚውል፣ የሚቀርብለትን ቅሬታ የሚቀበል፣ አሳማኝ ሆነም አልሆነም ወዲያው ምላሽ የሚሰጥ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ አሁን ከሁሉም በላይ አመራሩ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ አይውልም፣ ቢውልም በዳኛ ላይ የሚቀርበውን ቅሬታ ለመስማት ድፍረቱ የለውም፡፡ አሁን ያለው አመራር ዳኞችን ተጠያቂ ላለማድረግ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሥራውን እንዳይሠራ የሚያደናቅፍ ነው፡፡ ይህ ጉዳዩ በሚመለከተው የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ጭምር የተነሳ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ያለው አመራር ምንም ማስረጃ ሳይኖረው በዳኛው ላይ የሚነሳውን ቅሬታ በድፍረት በሚዲያ ወጥቶ የሚከላከል ነው፡፡ ዳኛውም ይህንን ሁሉ የሚያደርግለትን አመራር ከመቀበል ውጪ ምርጫ አይኖረውም፡፡
አሁን ባለን የዳኝነት ሥርዓት ፍርድ ማለት የዳኛው የፍላጎት መግለጫ (Declaration of The Will of The Judge) ነው፡፡ በዳኝነት ሥርዓታችን ውስጥ ፍርድ የሚጻፈው ከመጨረሻው ወደ መጀመርያው ነው፡፡ ፍርድ የሚገኘው ከፍሬ ነገሩና ከሕጉ ትንተና ቢሆንም፣ አሁን ፍርድ የሚገኘው ከዳኛው ፍላጎት ነው፡፡ ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት አቶ ከበደና አቶ አበበ የፍርድ ቤት ተከራካሪዎች ናቸው እንበል፡፡ የዳኛው የመጀመርያ ሥራ ምን ልፍረድ በሚለው ላይ ሳይሆን፣ ለማን ልፍረድ በሚለው ላይ መወሰን ነው፡፡ በቃ ዳኛው ለአቶ ከበደ ልፍረድ ብሎ ይወስናል፡፡ ለአቶ ከበደ ለመፍረድ ከወሰነ በኋላ ሕጉንና ፍሬ ነገሩን ለአቶ ከበደ በሚጠቅም መልኩ ለመጠምዘዝ መዝገቡን መመልከት ይጀምራል፡፡ በሕጉና በፍሬ ነገሩ መሠረት በቀላሉ በቦሌ በኩል ተሂዶ ለአቶ አበበ ሊፈረድ የሚገባውን ፍርድ፣ ዳኛው በባሌ በኩል ወስዶና ወደ መቀሌ መልሶ ለአቶ ከበደ ይፈርድለታል፡፡ በርካታ የሰበር ውሳኔዎች ሳይቀሩ በዚህ መልክ የተሰጡ ፍርዶች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
በመጨረሻ የምንመለከተው ችግር የማዳፈን የአመራር ሥነ ልቦናን ነው፡፡ እሳት ማዳፈንና ችግር ማዳፈን ሒደታቸው አንድ ቢሆንም፣ ውጤታቸው በእጅጉ የተለያየ ነው፡፡ አሳት ማዳፈን ውጤቱ እሳቱን ማቆየት፣ እሳቱን እንዳይስፋፋና ጉዳት እንዳያደርስ መገደብ ነው፡፡ ችግር ማዳፈን ግን ውጤቱ አድሮ ውሎ ቤቱን በእሳት ማቃጠል ነው፡፡ አሁን ባሉ የፍርድ ቤት አመራሮች ችግር የማዳፈን ሥራ የሚከናወን ስለመሆኑ ከዚህ በታች የቀረቡ ተጨባጭ ማስረጃዎችን መመልከት ይቻላል፡፡
- አንድ ፍርድን ናሙና በማድረግ ‹‹ተጠያቂነት የሌለው የዳኝነት ሥርዓት መስፈንን ይመለከታል፤›› የሚል ሰነድ በ2013 ዓ.ም. ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ለኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ እንዲሁም፣ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በተመዘገበ ፖስታ ተልኮላቸው ሁሉም ተቋማት መልዕክቱን የተቀበሉ ስለመሆኑ ፖስታ ቤቱ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ በተለይም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኃላፊዎች መልዕክቱ እንደ ደረሳቸውና ሰነዱን እንደ ተመለከቱት ተረጋግጧል፡፡ የሰነዱ ይዘት በአጭሩ የዳኝነት አካሉን ተጠያቂ የሚያደርግ የአሠራር ሥርዓት ካልተዘረጋ ከዚህ በኋላ ዜጎች ራቁታቸውን የሚቀሩት በዳኛ ፊርማና በፍርድ ቤቱ ማኅተም ነው፣ ስለዚህ ሲባልም ወንጀለኞች በሙሉ ወደ ፍርድ ቤቱ አጥር ግቢ መሰባሰባቸው አይቀርም የሚል ነው፡፡
ሰነዱ በወቅቱ አንድን ፍርድ በናሙናነት በመውሰድና የዳኝነት አካሉን ሥነ ልቦና በመተንበይ የተዘጋጀ ቢሆንም፣ አሁን ዛሬ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ዜጎችን እንዴት ራቁት እንደ ሚያስቀር በመላው ዓለም ፊት ቀርበው ማስረጃ መሆን የሚችሉ ፍርዶች በጸሐፊው እጅ ይገኛሉ፡፡ በፍርድ ቤቱ አጥር ዙሪያ የተኮለኮሉት ደላሎችም የሚዲያ መነጋገሪያ ሆነዋል፡፡ ለተለያዩ አካላት ለተላከው የቅሬታ ሰነድ ምላሽ ለመስጠት በሚመስል መልኩ “USAID” ከተባለው ፈረንጅ የጥናት ገንዘብ ተለምኖ፣ ‹‹የፍርድ ቤት ተገልጋዮች የእርካታ ጥናት›› የሚል ጥናት ተካሂዶ ውጤቱ የካቲት 6 ቀን 2014 ዓ.ም. በዋናነት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተገኙበት ይፋ ተደርጓል፡፡ እዚህ ላይ ቅሬታው ለማን ቀረበ፣ የጥናቱ ውጤት ለማን ቀረበ የሚለውን ማስተሳሰር ያስፈልጋል፡፡
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቅሬታ ቀረበ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የጥናቱ ውጤት ቀረበ የሚለው አንድ የሚነግረን ነገር አለው፡፡ በጥናቱ ሕዝብ በፍርድ ቤቱ ላይ አመኔታ ያሳደረ ስለመሆኑ ተረጋግጧል ቢባልም፣ በጥናቱ ላይ በርካታ ትችቶች ሲቀርቡበት ቆይተዋል፡፡ ጥናቱ ለሕዝብ ይፋ በሆነ በአምስት ወራት ውስጥ በፍርድ ቤቱ ውስጥ የሚሠሩ ዳኞች በአንደኛ ደረጃ ሌብነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተከሰዋል፡፡ በአንድ የመንግሥት ራሥ ሁለት ምላስ ማለት ይኼው ነው፡፡ ጥናቱ አሁን የሕዝብ አመኔታ በማጣቱ የሞተ ውሻ (Dead Dog) ሆነ እንጂ ጥናቱ ዋጋ የሌለው ስለመሆኑ በስታትስቲካዊ ዘዴ ጭምር መሞገት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ ለማንሳት የተፈለገው ዋናው ነጥብ ችግርን ለመፍታት ሳይሆን፣ ችግርን የሚያዳፍን ጥናት ለማድረግ፣ ስለመኖሩ በሁሉም ዘንድ የሚታወቀውን ችግር የለም ለማስባል እንዴት ገንዘብ ከፈረንጅ ይለመናል የሚለው ነው፡፡ ለዚህ የዜጎች ጥያቄ መልስ ይገባናል፡፡
- ልክ እንደ ውኃና መብራት ለአንድ ቀን እንኳን መቋረጥ የማይገባው የዳኝነት አገልግሎት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከነሐሴ 1 ቀን እስከ መስከረም 30 ቀን ለ65 ቀናት ለምን እንደተዘጋበት፣ የፍርድ ቤቱ ኃላፊዎች መልስ እንዲሰጡ መስከረም 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ስድስት ገጽ መጥይቅ ተልኮላቸው መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ በእርግጥ ፍርድ ቤቱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በተዘጋበት 65 ቀናት ዱባይ፣ ኢስታንቡል፣ ፓሪስ፣ ባሊ ኢንዶኔዥያ፣ ባንኮክ ከዚያም ኬንያ ሞምባሳ ለሽርሽር መሄድን ታሳቢ አድርጎ ፍርድ ቤቱን ለ65 ቀናት በአዋጅ እንዲዘጋ ካስደረገ ከአመራር የሚጠበቅ ምላሽ ሊኖር አይችልም፡፡ ሆኖም በ2014 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ፍርድ ቤቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በብልሹ ሥነ ምግባር መከሰሱን ተከትሎ ከነሐሴ 1 ቀን እስከ መስከረም 30 ፍርድ ቤቱን የሚዘጋው አዋጅ ፀንቶ ባለበት ፍርድ ቤቱ ከነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. የዳኝነት አገልግሎት እንዲሰጥ ተድርጓል፡፡ ነገሩ ዝም ስንባል ፍርድ ቤቱን እንዘጋዋለን፣ ስንወቀስ ደግሞ ፍርድ ቤቱን ከፍተን ወቀሳውን እናስታግሰዋለን እንደማለት ነው፡፡ እንደዚህ ያለው ወጣ ገባ የፍርድ ቤቱን አመራር ፍጹም አመኔታ እንዲታጣበት ያደረገ ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት አመራሩ ሲፈልግ የሚዘጋው አመራሩ ሲፈልግ ደግሞ የሚከፍተው ሆኗል፡፡
- ዳኞች በግልጽ ችሎት እንዲያስችሉ የሚደነግጉት መመርያ ቁጥር 008/2013፣ መመርያ ቁጥር 13/2014፣ እንዲሁም የዳኞች የሥነ ምግባርና የዲሲፕሊን ደንብ (ደንብ ቁጥር 1/2013 እንደ ተሻሻለው) በሥራ የማይተረጎሙ ከሆነ የሚሻለው መሰረዛቸው ነው፡፡ የፍርድ ቤቱ ተገልጋዮች በተግባር የማይተረጎም ሕግ በእጃችን ይዘን ከዳኞች ጋር እንድንጋጭ ሊደረግ አይገባም የሚል አቤቱታ ጥቅምት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀርቧል፡፡
ለቀረበው አቤቱታ ጤነኛው ምላሽ መመርያውን በሥራ ላይ ማዋል የማይተገበር ከሆነም መመርያውን መሰረዝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንድ የባለ አምስት ሰበር ችሎት ሰብሳቢ ሴት ዳኛ ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዜና ሰዓት ቀርበው 86 በመቶ የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ችሎቶች በግልጽ ችሎት እንደሚያስችሉ ማብራሪያ ሲሰጡ ተሰምተዋል፡፡ በመጀመርያ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በመናገር የሚፈታ ችግር የሌለ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በቀጣይ ስድስት ኪሎ የሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ሥራውን የሚሠራ የሰበር ዳኛ በየቀኑ በየምድብ ችሎቶቹ ከሚውለው የፍርድ ቤቱ ተገልጋይ የተሻለ መረጃ ሊኖረው አይችልም፡፡ መረጃ የሌለው መረጃ ያለውን ለማሳመን የሚደረገው ጥረት በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ የፍርድ ቤቱን ጉዳይ የወንዶችና የሴቶች ጉዳይ ለማድረግ ተፈልጎ ከሆነ በጣም ደስ የማይል ጉዳይ ነው፡፡
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍርድ ቤቱን ዳኞች በአንደኛ ደረጃ ሌብነት ከከሰሱ በኋላ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ‹‹በፌዴራል የዳኝነት አካል ውስጥ የሚታዩ የሙስና ተግባራትን መከላከያና መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ ደንብ ቁጥር 4/2014›› የሚል ደንብ አውጥቷል፡፡ ይህንን ደንብ አንብቦ የጨረሰ ሰው በእጅጉ መገረሙ አይቀርም፡፡ ደንቡ በፍርድ ቤት ውስጥ የሚታየውን ሌብነት ለመቆጣጠር የወጣ ሳይሆን፣ እነሱ ሲጮሁ እኛም አብረን እንጩህ የሚል ግብ የያዘ ነው፡፡ የሰረቀውም የተሰረቀውም አብረው ሲጮሁ ሌባው እንደሚያመልጥ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው የደንቡ ዓላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2014 ዓ.ም. ስለፍርድ ቤቱ የተናገሩትን በ2015 ዓ.ም. እንዳይደግሙት ለማድረግ ያለመ ይመስላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙስና ሙስና እያሉ ይናገራሉ እንጂ ይኸው ሙስናን የሚቆጣጠር ደንብ አውጥተን፣ ሙሰኛን፣ የሚይዝ ኃላፊ መድበን፣ በውስጣችን አንድም ሌባ አልተገኘም፣ ጠቅላዩ ምንድነው የሚናገሩት እያሉ ላለማሳጣት ይመስላል፡፡ ጸሐፊው ደንቡን እንዳነበበ ለዚሁ ሥራ ለተመደቡት ኃላፊ በዚህ ደንብ ውጤት እንደማያመጡና ሥራውን በሌላ መንገድ እንዲያከናውኑ ምክር ሰጥቷል፡፡ ኅዳር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀይ መስመር ክፍለ ጊዜ የቀረቡት የፍርድ ቤት ኃላፊ ያረጋገጡት ደንቡ ውጤት ያላስገኘ መሆኑን ነው፡፡ እነሱ ሲጮሁ እኛም እንጩህ ለሌባው እንጂ ለማንም አይጠቅምም፡፡
- የፍርድ ቤቱ አመራሮች እጅግ አስደናቂው ባህሪ መረጃ ደባቂነታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ገቢዎች ሚኒስቴር ያወጣቸውን መመርያዎች ማንም ሰው ወደ ሚኒስቴሩ ድረ ገጽ በመግባት በቀላሉ የፈለገውን መመርያ ለማግኘት ይችላል፡፡ ወደ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ወደ ፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ስንመጣ አወጣናቸው የሚሏቸውን መመርያዎች ለሕዝብ ተደራሽ አያደርጉም፡፡ በፍርድ ቤቱም ሆነ በጉባዔው ድረ ገጽ ወይም ፌስቡክ ገጽ ላይ መመርያዎች ተጭነው አይገኙም፡፡ ለምሳሌ ጸሐፊው የችሎት ሥነ ሥርዓት መመርያ ቁጥር 13/2014 የተባለውን መመርያ በፍርድ ቤቱ ገጽ ላይ ፈልጎ በማጣቱ የማይነበብ ፎቶ ኮፒ በአንድ መቶ ብር ለመግዛት ተገዷል፡፡ የሙስና መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 4/2014 የተባለውን ደንብ ጸሐፊው ያገኘው ሌሎች ሠራተኞች እየተጠቃቀሱ አንድ ወዳጁ አሾልኮ ስለሰጠው ነው፡፡
በጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ሆነ በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሕጎች የሚወጡት በመሬት ላይ ወርደው እንዲተገበሩ ሳይሆን፣ ይህንን ለዚያው ለፈረደበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሪፖርት ለማቅረብ ያህል ነው፡፡ አሁን ያለው የፍርድ ቤት አመራር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጣቸውን አስገዳጅ ውሳኔዎች በመጽሐፍ ማሳተም አቁሟል፡፡ ኅትመቱ የቆመው በገንዘብ እጥረት አይደለም፡፡ ፍርድ ቤተ ለአጥር ማጥበቂያና ለቀለም መቀቢያ የሚበትነውን ገንዘብ ለዕውቀት ሥራ ለማዋል ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን መረጃ መደበቅ የአመራሩ ዋነኛ ባህሪ በመሆኑ የሰበር ውሳኔዎች ታትመው እንዳይወጡ አድርጓል፡፡
ሲጠቃለል አንድ የፍርድ ቤት አመራር አራት መመዘኛዎችን መሟላት ይኖርበታል፡፡ እነሱም አንደኛ መታመን፣ ሁለተኛ መታመን፣ ሦስተኛ መታመን፣ አራተኛ መታመን ናቸው፡፡ አንድ የፍርድ ቤት አመራር አራት ድክመቶችን ማስወገድ ይኖርበታል፡፡ እነሱም አንደኛ ያለመታመን፣ ሁለተኛ ያለመታመን፣ ሦስተኛ ያለመታመን፣ አራተኛ ያለመታመን ናቸው፡፡ ዳኛም እንደዚሁ፡፡ የፍርድ ቤቱ ተቀባይነት ከስታትስቲክስ ወይም ከሚዲያ የሚገኝ አይደለም፡፡ የፍርድ ቤቱ መታመን የሚገኘው በውስጡ ከሚሠሩ ሰዎች መታመን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት የታመነ አመራር ይፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም የታመነ ፍርድ ቤት ይፈልጋል፡፡ ሕዝብ ፍርድ ቤት የሚገባኝን አይወስድብኝም፣ የማይገባኝንም አይሰጠኝም በማለት ተኝቶ እንዲያድር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የጸሐፊው ማሳሰቢያ
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የቀረበው አስተያየት የትኛውንም ግለሰብ የሚመለከት አይደለም፡፡ ጽሑፉ ያተኮረው በዳኝነታዊ ሥነ ልቦና ላይ እንጂ በየትኛውም ግለሰብ ላይ አይደለም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው wbdlakew@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡