ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ የተመሠረተበት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከፀደቀ ዘንድሮ ኅዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ሃያ ስምንት ዓመት ሆኖታል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የፀደቀበት ቀንን ለተወሰኑ ዓመታት ‹‹የሕገ መንግሥት ቀን›› በመባል የተከበረ ሲሆን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚያዝያ 1998 ዓ.ም. በወሰነው መሠረት ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ዕለቱ ‹‹የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን›› ተብሎ እየተከበረ 17ኛው ዓመቱ ላይ ደርሷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በየክልሉ በሚገኙ ተቋማት ቀኑ የታሰበው ‹‹ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላም›› በሚል መሪ ቃል ነው፡፡
በቀኑ አጋጣሚ ከደቡብ እና ከሰሜን የአገሪቱ ክፍሎች መካከል በደቡብ ኦሞ ዞንና በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙት ትውፊቶች መካከል ጥቂቱን አቅርበናል፡፡
ፀማይ
በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ከሚገኙት ወረዳዎች መካከል የበናና ፀማይ ወረዳ አንዱ ነው፡፡ እንደ ቱባ መጽሔት አገላለጽ፣ በወረዳው ውስጥ የሚገኙት የፀማይ፣ የብራይሌና የበና ብሔረሰቦች ለዘመናት ሲሸጋገር የመጣ ድንቅና ታሪካዊ ሥርዓት ብዙ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተካተቱ፣ ለቱሪዝም መስህብ የሆኑ የተለዩ ባህላዊ እሴቶችና የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት ናቸው፡፡ በቱባ ከተዳሰሱት መካከል የፀማይ ብሔረሰብ ትውፊታዊና ባህላዊ መገለጫዎች አንዱ የግጭት አፈታት ዘዴ ነው፡፡
የፀማይ የግጭት አፈታት ዘዴ ባልኮ /ባሌ/ ይባላል፡፡ በአካባቢው ሰው ከተፈነከተና ደም ከፈሰሰ ባልክ /የሀገር ሽማግሌዎች/ በመሰብሰብ የተደበደቡበትን ዱላ አስቀርቦ ባላ ያለው ብትር በመትከል ውኃ ይዞ ቡሎ የሚባል ፍሬ ወይም በግ በማረድ ፈርሱን ከአፈር ጋር በማነካካት እና በባላው ሥር በመድፋት እርቅ ይፈፅማሉ፡፡
በግጭቱ ነፍስ ከጠፋ ሽማግሌዎች ከጎሳው በጉዳዩ ይግባቡና የገዳይ ወገን ማለትም ለሟች ወገን ለሟቹ ተብሎ ልጃገረድ እንዲሰጥ ይደረጋል፣ አዲስ ሾርቃ ከቅል የተሠራ መጠጫ የእህል ዘር ይቀርብና ካብ ተቆፍሮ ሁለቱም ወገኖች በተቃራኒ አቅጣጫ ቆሞ ሾርቃውንና የበሎን ፍሬ እየለዋወጡ በመቀባበል እንዲነኩ ይደረጋል፡፡ በግ ታርዶ ሁለቱም ወገኖች ፈርስ ውስጥ እጃቸውን እንዲነክሩ ይደረጋል፡፡ በባህሉ ሰው ሲሞት በሟች ስም አዋልኮ የሚባል ሥርዓት ይፈፀማል፤ ይህም በስሙ ሚስት ትዳራለች፡፡ ከሟቹ ወንድሞች ብትወልድ የሚወለደው ልጅ በሟቹ ስም እንዲጠራ ይደረጋል፡፡
የባህላዊ ጎሬ ሥርዓት
የባህላዊ ጎሬ ሥርዓት በእናትና አባት የሚሠራ ሥርዓት ነው፡፡ በፀማይ ጎሬ ማለት ብሔረሰቡ ለማግባት የደረሰ ወንድ ልጅ የሚሠራለት ደንብ ሥርዓት ማለት ነው፡፡ ይህንን ደንብ ለመሥራት በመጀመሪያ ለጎሬ ክንውን ሥርዐት ደንቡን ለመሥራት ለአጐት ለእናት ወንድም አቢዮ ሎንጋቴ ይነገራል፡፡ የጎሬ አጐት ማለት ፈጻሚ ማለት ነው፡፡ በመቀጠል ለአድራጊው ይነገረዋል፡፡ በተስማማበት ለመሥራት እሺ ይላል፡፡
የልጁ ቤተሰብ የሀገር ሽማግሌዎችን ወደ አጐቱ ይልኩና ያስማማሉ፡፡ አጐቱም እጅ መንሻ በሬና ማር ይቀበላል፡፡ ካልተስማማበት የሀገር ሽማግሌዎች ከጎሬ ከሠሪ ቤተሰብ ይላካል፡፡ እሺ እንዲል ማር ወይም በሬ ይሰጠዋል፡፡ በመቀጠል እስከ አንድ ዓመት ሊፈጅ ይችላል፡፡ ጎሬ ሠሪው ደንቡን ለመሥራት ሲጀምር የተለያዩ የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት እንዲገኙ ይደረጋል፡፡
ቀጥሎም የባህላዊ የምግብ ዓይነቶችና ባህላዊ የመጠጥ ዓይነቶች ይዘጋጃሉ፤ ይበላል ይጠጣል፡፡ ጎሬ ከመታሰር እና ከመፈፀሙ በፊት አባትና እናት በመጋረጃ በተጋረደ ቃል ኪዳን ይገባሉ፡፡ ሥርዓቱን ከፈፀሙ በኋላ ሴት ልጅ ትመጣና በመጋረጃ ውስጥ ገብታ በወገቧ ላይ የታሰረውን ገመድ /ምርኮ/ በጥሣ ትጥላለች፡፡
የአግቢው የጎሬ ሥርዓትንም ቱባ እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡ በመጀመሪያ ወደ ሥርዓቱ አድራጊ /አብ/ ቤት ይሄዳሉ፡፡ ወንድ ልጅ በመጀመሪያ ይቀመጣል፡፡ በመቀጠል የሚቀጥለው በተራ ከተቀመጡ በኋላ ከለጌና ከዝንጀሮ ቆዳ የተሠራ የዝንጀሮው ቆዳ ግን ውሻና አውሬ ያልነካው መሆን አለበት፡፡ ከዝንጀሮ ቆዳ ትንሽ ትንሽ በመቁረጥ በላጊው /ገመድ/ ላይ በመብሣት የሥርዓቱ አድራጊ /አብዮ/ ጉርቴ/ በእጃቸው ላይ ያስራሉ፡፡ በመቀጠል ቀጠሮ የሥርዓቱ አድራጊ /አብዮ ሎንጋቴ/ ቀስት ይወስዳሉ፡፡ የቀስቱ ትርጉም ጀግና ናችሁ ማግባት ትችላላችሁ በማለት ይመርቋቸዋል፡፡
ለሴት ልጅ ግን ችግር የለውም፤ ወንድ ልጅ ግን ለአቅመ አዳም ከደረሰ ጎሬ ካልተሠራ ማግባት አይችልም፡፡ በብሔረሰቡ ዘንድ ጎሬ ካልተሠራ ከባድ የተለያዩ ረሃብ፣ ድርቅ፣ ችግርና መከራ ይከሰታል፤ የሚወለዱት ልጆችም አያድጉም ተብሎ ይታሰባል፡፡
የጊምባ እረኛ
በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙት ወረዳዎች አንዱ የለጋምቦ ወረዳ ነው፡፡ ለጋምቦና አካባቢው ካሉት ታሪካዊና ባህላዊ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል የጊምባ እረኛ አንዱ ነው፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ከለጋምቦ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ያገኘውን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አጋርቷል፡፡ እንዲህም ይነበባል፡፡
የጭሮሜዳን ጨምሮ ቀርመሜ፣ ኢብራሂም አገር፣ አዩቤት፣ ቡክዶ፣ ሰኞ ገበያና ከረጊምባ ይህ የጊምባ እረኛ ታሪክ ይነገርባቸው የነበሩ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ዋነኛ መተዳደሪያቸው ግብርና ቢሆንም ከዚህ ጎን ለጎን በስፋት የበግ ዕርባታም ያከናውኑ ነበር፡፡ ተፈጥሮ አመቻችቶ በዘረጋው የተንጣለለው ሜዳ ላይ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው በጎች ለግጦሽ የሚሰማሩ ቦታ ነበረ፡፡
የጊምባ እረኛ አለባበሱ ከስር አጭር ቁምጣ፣ ከላይ ደግሞ ኮት ደረብ አድርጎ ፎጣ ያጣፋል፣ ራሱ ላይ ደግሞ /ከበግ ፀጉርና ከጥለት በእጅ የምትሠራ ‹‹ጉኒና›› በመባል የምትጠራ ኮፍያ ያደርግና ከዚህ በላይ ከበግ ቆዳ የሚዘጋጀውን ‹‹ለምድ›› ይደርባል፡፡ ለእግሩ ጫማ የሚለብስም የማይለብስም ያለ ሲሆን፣ ይለበስ የነበረው በረባሶ /ጅብ አይበላሽ/ የሚባል ከመኪና ጎማ የሚሠራ ጫማ ነበር፡፡ ይህ እረኛ እንደ አሁን ዘመኑ የምሳ ሰዓት ስለማይታወቅ ከበግ ፀጉር በምትሠራ ‹‹ቁርቁምባ›› በምትባል የቆሎ መቆጠሪያ/መያዥያ/ ከፀጉር በተሠራ ቁርቁምባ ቆሎውን ጠዋት ቋጥሮ ይሄድና ሲርባቸው ሁላቸውም አደባልቀው በአንድ ላይ ይበሉ ነበር፡፡
እረኞች በአንድ ላይ በመሆን ከድንጋይ ካብ በመካብ ንፋስን የሚከላከሉበት መንገድ፤ በዝናብ ወቅት የሚለብሱት ከጓሳ የሚሠራ ‹‹ገሳ›› የነበረ መሆኑና እንዲሁም የተለያዩ ታሪካዊ ሁኔታዎችን /በጦርነት ጊዜ፣ በድርቅ ጊዜ፣ በመንግሥታት መውጣትና መውረድ ጊዜ፣ ዘመናዊ የመገልገያ ዕቃዎች ሲመጡ …ወዘተ በግጥምና በዜማ በማዋዛት ‹‹እልዎ›› አህያ መጣች እያሉ ትንቢታዊ ይዘት ያላቸው ንግግሮችን ያደርጉ ነበር ፡፡
ታሪካዊ አመጣጡ ከአያት ቅድመ አያት ጀምሮ ያለ ሲሆን፣ እስከ መሃል አገር ሳይቀር ‹‹የጊምባ እረኛ ዘንድሮ ምን አለ ተብሎ?›› ይጠየቅና ይታመን እንደነበር የዕድሜ ባለጸጋዎች ይናገራሉ፡፡ ትንቢት ተናጋሪው የጊምባ እረኛ የተመረጠ/ያውቃል /የተባለው እንጂ ሁሉም እረኞች አይናገሩም፡፡ በመሆኑም እረኞች በሙሉ ተሰብስበው ይህንን እረኛ በመክበብ ልብስ /ለምድ/ ድሪቶ /ይደራረብበትና ይተኛል፡፡ ከዚያ እንደ ህልም አስመስሎ ‹‹እንዲህ በል አለኝ›› ይላል፡፡ መረጃ ሰጭዎች እንደሚያስረዱት ባለፉት ዘመናት እንዳሁኑ ጊዜ መኪና ስላልነበረ መንገደኞች በእግራቸው ከተለያየ ቦታ እየተጓዙ መጥተው ጊምባ አካባቢ ሲደርሱ፣ ከያዙት ስንቅ አውጥተው ዳቦ /ዳቦ ቆሎ /አምስት ሳንቲም/ የልብስ መቆለፊያ የተገኘውን በመስጠት፣ ዘመኑ ወደፊት ምን ዓይነት እንደሚሆን ትንቢት ይጠይቋቸዋል? እረኞችም ወደፊት ወቅቱ ጥጋብ፣ ረሀብ ወይም የጦርነት ወዘተ ጊዜ ስለመሆኑ ይነግሯቸዋል፡፡