Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹እንደ አገር ቢያንስ ኮንዶም ማቅረብ አልቻልንም››   አቶ ባይሳ ጫላ፣ የኔፕ ፕላስ ተጠባባቂ ዳይሬክተር

ቀደም ሲል በኤችአይቪ የተያዙ ሰዎችን የጋራ ድምፅ ለማሰማትና ተደራሽ ለማድረግ፣ ‹ከኤችአይቪ ኤድስ ጋር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማኅበር› በጥቅምት ወር 1997 ዓ.ም. መቋቋሙ ይታወቃል፡፡ ይኸውን ማኅበር ጨምሮ በየክልሉና በአዲስ አባባና ድሬዳዋ ከተሞች ያሉ ማኅበራትን አስተሳስሮ የያዘው አውታረ መረብ ‹‹ኔትወርክ ኦፍ ኔትወርክስ ኦፍ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ኢን ኢትዮጵያ›› በምሕፃሩ ኔፕ ፕላስ (NEP+) ይባላል፡፡ ተቋሙ እንደገለጸው፣ ኔፕ ፕላስን በመጀመሪያ ያቋቋሙ 18 ማኅበራት ሲሆኑ፣ አሁን ቁጥሩ  ወደ 500 አድጓል፡፡ ሁሉም ክልሎች፣ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ የሚገኙ የኤችአይቪ ማኅበራት እንዲሁም የየራሳቸውን ክልላዊ ትስስር መሥርተዋል። እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በጋራ በመሰባሰብ የተቀናጀ ጥረቱን ለመምራት በኔፕ ፕላስ ጥላ ሥር ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ አውታረ ማኅበሩ አንድ አገር አቀፍ የሴቶች ማኅበርን ጨምሮ 14 ኔትወርኮችንና በእነዚህም ኔትወርኮች ሥር የተደራጁ 500 ማኅበራትን ያቀፈ አካል ነው፡፡ አቶ ባይሳ ጫላ የኔፕ ፕላስ ጠባባቂ ዳይሬክተርና የሀብት ማፈላለግ ዲፓርትመንት ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በኤችአይቪ ኤድስ ፕሮግራም፣ በኔትወርኩ እንቅስቃሴና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኔትወርኩ ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ላለባቸው ወገኖች ምን የሚፈይደው ነገር አለ?

አቶ ባይሳ፡- ስለ ፋይዳው ከመናገሬ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸው ወገኖች ብዛት 460 ሺሕ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ከእነዚህም መካከል 170 ሺሕ ያህሉ ኔትወርኩ በሚያስተዳድራቸው ኔትወርኮች በሚገኙ 500 ማኅበራት የታቀፉ ናቸው፡፡ ኔትወርኩ በመላ ኢትዮጵያ ለሚገኙና ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ላለባቸው ወገኖች ሁሉ ድምፃቸውን የማሰማት ተግባር ያከናውናል፡፡ ይህንንም ተግባር የሚያካሂደው የተለያዩ ፍላጎታቸውንና አልተሟላልንም የሚሏቸውን ጉዳዮች እየተቀበለ ወደ ሚመለከተው አካል በማቅረብና ከፍጻሜም እንዲደርሱ በማድረግ ነው፡፡ በተረፈ በማኅበራቱ ለታቀፉት ወገኖች ድምፃቸውን ከማሰማት ባሻገር መረጃና የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት፣ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራም በማዘጋጀት፣ መድኃኒቶቻቸውን በጊዜውና በአግባቡ ሳያቋርጡ እንዲወስዱ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ሁኔታዎች የማመቻቸት ሥራ ሳያቋርጥ ያካሂዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ቫይረሱ በደማቸው ያለና የኤድስ በሽተኞች ምን ልዩነት አላቸው?

አቶ ባይሳ፡- ክሊኒካል አሴስመንት የሚባል አለ፡፡ አንድ ሰው ቫይረሱ በደሙ ውስጥ ቢኖርም ጤናማ ኑሮ ይኖራል፡፡ ለዚህም መድኃኒት መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት መድኃኒቱ በደሙ ውስጥ ያለውን የቫይረስ መጠን በጣም ይቀንሰውና ጉልበት እንዳይኖረው ያደርገዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ቫይረሱ ምንም እንኳን በደሙ ውስጥ ቢኖርም እንደማንኛውም ዜጋ ሠርቶ መኖር፣ ወይም አምራች ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹ኤድስ›› የሚባለው ግን በአግባቡ መድኃኒቱን ሳይወስድ ይቀርና ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ጭርሱኑ ይተወውና ቫይረሱ የበሽታ መከላከል አቅሙን እየበላው፣ እየበላው ይሄድና መጨረሻ ላይ ለሞት ይዳርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ኤድስ ያለባቸው ሰዎች በምን ደረጃ ላይ ነው ያሉት?

አቶ ባይሳ፡- በኤድስ ደረጃ ያሉ ሰዎች በቁጥር በእኔ ግምት ዜሮ ነጥብ አምስት በመቶ እንኳን አይሞሉም፡፡ በእርግጥ ይህ ጉዳይ ጥናትና ምርምር ያስፈልገዋል፡፡ በተረፈ ቫይረሱ በደማቸው ያሉና መድኃኒቱን በአግባቡ የሚወስዱ ሰዎች ከኤድስ አደጋ ይተርፋሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን አንዳንድ መንጠባጠቦች ይታያሉ፡፡ ይህም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ከእንግዲህ ወዲያ እኔ የት እደርሳለሁ? መድኃኒት ከምውጥ ይልቅ በየአብያተ ክርስቲያኑ እየሄድኩ ለምን አልጸልይም ከሚል የተሳሳተ እምነትና ምክንያት መወሰድ የሚገባቸውን መድኃኒት ሲያቋርጡ ይስተዋላል፡፡ መድኃኒት ከተቋረጡ ደግሞ ሰውየው ቆየ ቢባል ለስድስት ወራት ያህል ቢሆን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በሽታው እያሸነፈ መጥቶ ለሞት ይዳርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኔትወርኩ ከጤና ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት እንዴት ይገመገማል?

አቶ ባይሳ፡- ከጤና ተቋማት ጋር ያለን ግንኙነት እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ይህንን ልል የቻልኩት ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው 1,760 ወገኖች በ760 የመንግሥት ጤና ተቋማት ተቀጥረው እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡ በዚህም የመንግሥት ሠራተኛ ሆነዋል፡፡ አንድ ቫይረሱ በደሙ ያለበት ሰው ለምርመራ ወደ ሐኪም ዘንድ ሲቀርብ ችግሩንና አድራሻውን በፍርኃት የተነሳ ለሐኪሙ ላይገልጽ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ሐኪሙ እኛ ለቀጠርናቸው ወገኖች አነጋግሩት ብሎ ሪፈር ይጽፍላቸዋል፡፡ በየጤና ተቋማት የተቀጠሩትም ወገኖች ለምርመራ የመጣውን ሰው ‹‹እኔ እንዳንቺው/እንዳንተው ነኝ!! አትፍሩ፣ ምንም አትሆኑም፣ ቀላል ነገር ነው!!›› እያሉ ያረጋጉታል፡፡ ወይም ያግባቡታል፡፡ በመካከሉም መስተጋብርና ጓደኝነት ይፈጠራል፡፡ ወደ ሐኪሙ እንዲመለስና መድኃኒቱን እንዲጠቀሙ ያደርጋቸዋል፡፡ ሲጠፋም ፈልገው ያመጡትና የኬር ኤንድ ሰፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጉታል፡፡ ድርጅቱ ይህ ዓይነቱ ሥራ የሚሠራው ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ የገጠሟችሁ ተግዳሮቶች ምንድናቸው?

አቶ ባይሳ፡- አሁን በተፈጠሩት ግጭቶች ምክንያት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ጠፍተዋል፡፡ የት እንዳሉ እንኳን አይታወቁም፡፡ ይህ ዓይነቱ ተግዳሮት የተከሰተው በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ነው፡፡ በተለይ የትግራይ ክልል ሁኔታ ከሁሉም የከፋና አስቸጋሪ ነው፡፡ በተጠቀሱት ክልሎች የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ውይይት ከመንግሥት ጋር አካሂደናል፡፡ ከብዙ ውይይትና የሐሳብ መለዋወጥ በኋላ የጠፉትን ለመመለስ ዘመቻ መካሄድ እንዳለበት በሙሉ ድምፅ ተስማማን፡፡ በስምምነቱም መሠረት ዘመቻ ውስጥ ገባን፡፡ በአማራ ክልል ብቻ በተካሄደው ዘመቻ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸውን 60 ሺሕ ወገኖችን ለማግኘት ችለናል፡፡ መድኃኒታቸውንም በአግባቡ እየወሰዱ ናቸው፡፡ ከዚህ ችግር ሌላ ደግሞ የጤና ተቋማት በመፍረሳቸውና መድኃኒቶቹም በመጥፋታቸው የተነሳ ጊዜያዊ የሆነ የአገልግሎት መቆራረጥ ተፈጥሯል፡፡ የሥነ ልቦና ችግርም አጋጥሟል፡፡ አሁን ግን በክልሎች አንፃራዊ ሰላም ስለሰፈነ ዘመቻው በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ቫይረሱ በደማቸው ካለባቸው ወገኖች መካከል ሴቶች ምን ያህል ናቸው?

አቶ ባይሳ፡- አገራዊ መረጃው 65 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው ይላል፡፡ በኔትወርኩ ከታቀፉት ከ170 ሺሕ መካከል 70 ከመቶ ሴቶች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በሴቶች ላይ በብዛት የታየው ለምንድነው?

አቶ ባይሳ፡- በዚህ ዙሪያ የተሠሩት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ አንደኛው ምክንያት ሴቶች የኢኮኖሚ ችግራቸውን ለመወጣት ሲሉ በወንዶች ጥገኛ ይሆናሉ፡፡ ከዚህም ሌላ የወንዶችን የጤንነት ሁኔታ ሳያረጋግጡ ጋብቻን ይመሠርታሉ፡፡ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ይፈጽማሉ፡፡ ይህም ለኤችአይቪ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ድህነቱም በራሱ አንድ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ሕፃን ልጅ ዛሬ ጊዜ የኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሆኖ መወለድ የለበትም፡፡ ምክንያቱም ከእናት ወደ ልጅ መከላከል ይቻላል፡፡ ለዚህም መድኃኒት አለ፡፡ የሚያስፈልገው በአግባቡ መጠቀም ብቻ ነው፡፡ ችግሩ እናቲቱ የጤና ሁኔታዋን የምታውቀው ከእርግዝና በኋላ መሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኤችአይቪ ገዳይና አሁንም ያልተገታ የኅብረተሰብ የጤና ችግር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከመከላከያዎቹ አንዱና ወሳኝ የሆነው ኮንዶም በገበያ ላይ አይታይም ምክንያቱም ምን ይሆን?

አቶ ባይሳ፡- ኮንዶም እንደ አገር ትልቅ ችግር አለብን፡፡ አንደኛ የኮንዶም እጥረት አለ፡፡ እጥረት ከየት መጣ ቢባል የገንዘብ ችግር አይደለም፡፡ ለዚህም ከግሎባል ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በቂ በጀት ተመድቦለታል፡፡ ችግሩ በመጀመርያውና በሁለተኛው ዙር የተገዙት ኮንዶሞች ጥራታቸው ያልተጠበቀና የዓለም ጤና ድርጅት ዕውቅና ያልሰጣቸው ሆነው በመገኘታቸው እንዲወገዱ ተደርጓል፡፡ ጥራታቸውን ያልጠበቁና የማይከላከሉ ከሆነ አማራጩ ማስወገድ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ችግር እንደ መፍትሔ ተብሎ የተወሰደው ጥራቱን የጠበቀ ኮንዶም በጥንቃቄ መግዛት ነው፡፡ ገዢውም በሒደት ላይ ነው እየተባለ ይነገራል፡፡ ይህም ቢሆን እስከዛሬ ድረስ ተገዝቶ ተጠቃሚዎች እጅ አልደረሰም፡፡ እንደ አገር ቢያንስ ኮንዶም ማቅረብ አልቻልንም፡፡ ያለውም ቢሆን በጣም ውድ በሆነ ዋጋ ወደ ገበያ ወጥቷል፡፡ በተለምዶ ‹‹ቺቺኒያ›› እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ምሽት ላይ ቢቆም ኮንዶም በስንት እንደሚሸጥ በጣም የሚገርም ነው፡፡ በመካከሉም ሕገወጦች ገብተው ዋጋውን እያናሩ በመሸጥ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አሁንም አስምሬ ለመግለጽ የምፈልገው ነገር ቢኖር ችግሩ የበጀት ሳይሆን በመጀመርያውና በሁለተኛው ዙር ግዥ ላይ ስህተት መፈጸሙ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመጀመርያውና በሁለተኛው ዙር ግዥ ላይ ምን ያህል ገንዘብ እንደወጣባቸው ይታወቃል?

አቶ ባይሳ፡- ይህንን መንግሥት ነው የሚያውቀው፡፡ እኔ አላውቀውም፡፡ ግን ታርጌት ተደርጎ ወይም ታቅዶ የተገዛው ለወጣቶች፣ በወሲብ ንግድ ለሚተዳደሩ ሴቶች፣ ረዥም ርቀት ለሚያሽከረክሩ ሾፌሮች፣ የኤችአይቪ ኔጋቲቭ ለሆኑ ባል ወይም ሚስት ተብሎና በቁጥራቸው ልክ ነው፡፡ ነገር ግን ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነም አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- የኤችአይቪ ሥርጭት በብዛት የሚታይባቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?

አቶ ባይሳ፡- ሥርጭቱ በብዛት የሚታይባቸው፣ በዚህም የተነሳ የመከላከሉና የመቆጣጠሩ ሥራ እየተካሄደ ያለው በ265 ወረዳዎች ውስጥ ነው፡፡ በተጠቀሱት ወረዳዎች ሥርጭቱ ሊስፋፋ የቻለው የሕዝብ ብዛትና ልዩ ልዩ እንቅስቅሴዎች ስለሚበዙባቸው ነው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ወደ 100 የሚጠጉ ወረዳዎች አሏት፡፡ ከእነዚህም መካከል በጣም ከፍተኛ የሆነ ጫና ይታይበታል ተብሎ የተለየው አውቶቡስ ተራ መናኸሪያ ነው፡፡ በዚህም በተለምዶ ‹‹ሰባተኛ›› እየተባለ የሚጠራ ቦታ ከዚሁ መናኸሪያ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ የሆነ የወሲብ ንግድ ይጧጧፍበታል፡፡ ከየክልሎች ሰዎች ወደ መናኸሪያው ይጎርፋሉ፡፡ በዚህ ላይ ደላላው፣ ነጋዴው፣ ሾፌሩ ሁሉ የሚተረማመስበት ነው፡፡ ቀጥሎ አዳማንም ማየት ይቻላል፡፡ የስብሰባ ማዕከል ነው፡፡ የሕዝብና የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ይዘወተርበታል፡፡ መተሐራ፣ የሜጋ ፕሮጀክት ያሉባቸው አካቢዎች፣ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች የኤችአይቪ ሥርጭት ከሚበዛባቸው ቦታዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ኤችአይቪን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ እስካሁን ሲከናወን የቆየው በውጭ የዕርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ ዓይነቱ ድጋፍ ቀጥሏል? ወይስ ቀንሷል?

አቶ ባይሳ፡- የውጭ ዕርዳታ ድርጅቶች ቀደም ሲል ይሰጡት የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ አሁን አይሰጡም፡፡ በፐርሰንት እንኳን ብንለካው ከ60 በመቶ በላይ ቀንሰዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀነሱበት ምክንያት ይታወቃል?

አቶ ባይሳ፡- የዕርዳታ ድርጅቶቹ ለዚህ የሚሰጡት መልስ በዓለም ላይ ኤችአይቪ በአሁኑ ጊዜ የኅብረተሰብ የጤና ችግር አይደለም፡፡ እንደ አንድ መደበኛ በሽታ በመከላከልና በሕክምና ሊድን የሚችል ነው የሚል መልስ ነው የሚሰጡት፡፡ የኤችአይቪ ሥርጭት ከአንድ በመቶ በታች ከሆነ በዓለም ጤና ድርጅት መሥፈርት መሠረት በሽታው በቁጥጥር ሥር ውሏል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው የሥርጭት መጠን 0.93 በመቶ ነው፡፡ ይህም ማለት በሽታው በቁጥጥር ሥር ውሏል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም እንደ ሌሎች መደበኛ በሽታዎች ታክሙታላችሁ እንጂ በፕሮግራም ተይዞ ሊንቀሳቀስ የማይገባው ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህ በዓለም ደረጃ ፈንዶች በሙሉ ከኤችአይቪ ይልቅ ወደ ሌላ ጉዳይ እየዞሩ ነው፡፡ በተለይ ወደ እኛ አገር ስንመጣ ፈንዱ እንደሚቀንስ ቀደም ብለን እናውቀው ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ፈንዱ መቀነሱ ከታወቀ ክፍተቱን ሊሸፍን የሚችል ምን የታቀደ ነገር አለ?

አቶ ባይሳ፡- የታቀደው ነገር ቢኖር አገር በቀል ወደሆኑ የፋይናንስ ምንጮች ላይ ትኩረት ማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በአገር ውስጥ ሀብት ማፈላለግ የተባለ የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ቀርቧል፡፡ በቅርቡም ጸድቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለዕቅዱም ስኬት ስትራቴጂ ወጥቶለታል፡፡ ስትራቴጂውም መንግሥት ከሚያስከፍለው ወይም ከሚሰበሰበው ታክስ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለበረራ ከሚቆርጠው ትኬት የተወሰነ ገንዘብ ለክፍተቱ መሸፈኛ እንዲውል ያደርጋል፡፡ ከዚህም ሌላ ከኢንዱስትሪያል ፓርኮች፣ ከሜጋ ፕሮጀክቶች፣ ከአገልግሎት፣ እንዲሁም ከማምረቻና ማከፋፈያ ተቋማት የተወሰነ ገንዘብ ለመሰብሰብ ጥረት ይደረጋል፡፡ በተረፈ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ወገኖች የሚጠቀሙትን መድኃኒት ራሳቸው ይግዙ ቢባል 75 ከመቶ ያህሉ አቅም የላቸውም፡፡ ስለሆነም መንግሥት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ለዚህም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያስፈልገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኤችአይቪ ቫይረስን ለመግታት ወይም እንዳይተላለፍ ለማድረግ በምን መልኩ መከናወኑ ይኖርበታል?

አቶ ባይሳ፡- ቫይረሱ እንዳይተላለፍ ለማድረግ ሦስት ‹‹መ››ዎችን በአግባቡና በጥንቃቄ መተግበር፣ እነሱም መታቀብ፣ መወሰን፣ መጠቀም ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ መድኃኒትን በአግባቡ መውሰድ ወደ ማለት መጥተናል፡፡ ይህም ያልንበት ምክንያት መድኃኒቱን በአግባቡ ተወስዶ የቫይረሱን መጠን ዝቅ ከተደረገ በላቦራቶሪ ሳይንስ ከ50 ኮፒ በታች (የቫይረሱ ብዛት) ከሆነ በሽታው ወደ ሌላ አይተላለፍም፡፡ ይህም ሁኔታ ‹‹የተገታ የቫይረስ መጠን›› ወይም ‹‹የተገታ መተላለፍ› ይባላል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ቫይረሱ እንዳለ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን የማይተላለፍ ቫይረስ ነው፡፡ አይተላለፍም ተብሎ መድኃኒቱን ካቆሙ ቫይረሱ ብድግ ይላል፡፡ ስለዚህ መድኃኒቱን እስከ ሕይወት መጨረሻ ድረስ መጠቀም ግድ ይላል፡፡ እኛም እያስተማርን ያለነው ይህንኑ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...