- ለተሰንበት በመጀመሪያ ማራቶኗ የምንጊዜም ምርጥ ሰዓት አስመዝግባለች
በዓመታዊ ውድድሮች አዲስ ነገር የማያጣው የቫሌንሺያ ማራቶን ዘንድሮም በአዲስ ታሪኮችን አስመዝግቦ አልፏል፡፡ በተለይ በየጊዜው እየተሻሻለ ለመጣው የጎዳና ሩጫ ሰዓት የቫሌንሺያው ውድድር ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
እሑድ ኅዳር 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው የቫሌንሺያ ማራቶን፣ በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ አማኔ በሪሱ 2፡14፡58 በመግባት በአንደኝነት ስታጠናቅቅ፣ በማራቶን ለመጀመርያ ጊዜ የሮጠችው ለተሰንበት ግደይ 2፡16፡49 ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡ ባለፈው ነሐሴ የሜክሲኮ ማራቶንን ማሸነፍ የቻለችው አማኔ፣ በቫሌንሺያ የማራቶን ክብረ ወሰን ለመስበር ተቃርባ የነበረ ቢሆንም፣ በውድድሩ አድናቆትን የተቸረችበትን አጨራረስ ማስመልከት ችላለች፡፡
አትሌቶቹ የውድድሩን 5 ኪሎ ሜትር ለማጠናቀቅ 16፡03 የወሰደባቸው ሲሆን፣ 10 ኪሎ ሜትሩን 32፡01፣ እንዲሁም 15 ኪሎ ሜትሩን 48፡03 በሆነ ጊዜ መሮጣቸው ተጠቅሷል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ለተሰንበትና አማኔ ከ25 እስከ 35 ኪሎ ሜትር ያለውን ርቀቱን 3፡44 በሆነ ጊዜ መሮጥ ችለዋል፡፡
በግማሽ ማራቶን 1፡08፡43 ሰዓት እንዲሁም በማራቶን 2፡20፡48 ምርጥ ሰዓት ያላት አማኔ፣ በቫሌንሺያው ማራቶን የግሏን ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ የቻለችበት ውድድር ሆኖላታል፡፡
ከዚህም ባሻገር አትሌቷ የዓለም የሴቶች የማራቶን ክብረ ወሰንን ለመስበር 54 ሰከንዶችን ብቻ ዘግይታ መግባቷ በቀጣይ በማራቶን ተስፋ እንዲጣልባት አድርጓል፡፡
ሌላዋ የቫሌንሺያ ማራቶን ድምቀት የነበረችው የ5 ሺሕ፣ የ10 ሺሕና የግማሽ ማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤቷ ለተሰንበት ግደይ ነበረች፡፡ ለተሰንበት ለመጀመርያ ጊዜ በተሳተፈችበት የማራቶን ተሳትፎ የምንጊዜም ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ በምትካፈልባቸው እያንዳንዱ ርቀቶች ላይ አዲስ ታሪክ እየጻፈች የምትገኘው ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት፣ በ5 ሺሕና በ10 ሺሕ ርቀቶች ላይ ያሳየችውን ገድል፣ በጎዳና ሩጫውም ለመድገም አዲስ ምዕራፍ ጀምራለች፡፡
የአትሌቷ የመጀመርያ ተሳትፎ በበርካቶች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን፣ የማሸነፍ ግምትም አግኝታ ነበር፡፡ ሆኖም ለተሰንበት ውድድሩን በሁለተኛነት ስታጠናቅቅ ፊቷ ላይ ቅሬታ እንደተነበበ ዘገባዎች ይፋ አድርገዋል፡፡
ማራቶንን በይፋ የተቀላቀለችው ለተሰንበት፣ ከዚህ በኋላ በጎዳና ውድድሮች ላይ ደምቃ የምትታይበት ጊዜዋ እንደሚሆን በርካቶች አስተያየታቸውን እየሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል በቫሌንሺያው ማራቶን ሴቶች ባደረጉት ውድድር ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን መካፈል የቻሉ ሲሆን፣ ሰባቱ አትሌቶች ከአንድ እስከ አሥር ውስጥ መካተት ችለዋል፡፡
በዚህም ታዱ ተሾመ (2፡17፡36) አራተኛ፣ ጥሩዬ መስፍን (2፡18፡47) ስድስተኛ፣ ትዕግሥት ግርማ (2፡18፡52) ሰባተኛ፣ እታገኝ ወልዱ (2፡20፡03) ስምንተኛ እንዲሁም ዶልሺ ተስፋ (2፡20፡40) ዘጠነኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው፡፡
በዚህም መሠረት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ አራት ሴት አትሌቶች 2፡18 ሰዓት ሲያጠናቅቁ፣ ሰባት አትሌቶች ደግሞ 2፡19 በሆነ ጊዜ ውስጥ ያጠናቀቁበት የማራቶን ውድድር ሆኗል፡፡
የቫሌንሺያው ማራቶን በሴቶቹ ብቻ ሳይሆን በወንዶቹም ውድድር አዲስ ታሪክ የተመዘገበበት ዕለት ነበር፡፡ ኬንያዊው የ23 ዓመቱ ኪልቭን ኪፕቱም የዓለም የወንዶች ማራቶን ፈጣን ባለቤት ከሆኑት ኢሉድ ኪፕቾጌ (2፡01፡09) እና ቀነኒሳ በቀለ (2፡01፡41) ምርጥ ሰዓት ቀጥሎ 2፡01፡53 በማጠናቀቅ ሦስተኛው አትሌት ሆኗል፡፡ አትሌቱ የዓለም ሦስተኛውን ምርጥ ሰዓት ከማስመዝገብ ባሻገር፣ በመጀመርያ የማራቶን ተሳትፎ የዓለም ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል፡፡
የርቀቱን ሁለተኛው አጋማሽ 1፡00፡11 ያጋመሰው አትሌቱ በበርካቶች ዘንድ ሙገሳን አስገኝቶለታል፡፡ ኪልቪን የኬንያን አራተኛ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ የቻለበት ውድድር ሆኗል፡፡
በወንዶቹ ውድድር ስድስቱ 2፡05 ሰዓት ውስጥ ሲያጠናቅቁ 12 አትሌቶች ደግሞ 2፡07 ጊዜ ውስጥ መግባት የቻሉበት ሌላው የውድድሩ ክስተት ነበር፡፡
የኦሪገን ዓለም ሻምፒዮና የማራቶን ባለዕድሉ ታምራት ቶላ በ2፡03፡40 በሆነ ጊዜ አራተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ ጫሉ ደሶ በ2፡04፡56 ስድስተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ሚልኬሳ መንገሻ በ2፡05፡29 ሰባተኛ፣ እንዲሁም ጎይቶም ክፍሌ በ2፡06፡09 አሥረኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ አትሌቶች ናቸው፡፡
ታንዛንያዊው ገብርኤል ጌይ በ2፡03፡00 በሆነ ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ የራሱንና የአገሩን ክብረ ወሰን ማሻሻል ችሏል፡፡
ዓለም አቀፍ የጎዳና ውድድሮች መበራከቱን ተከትሎ በርካታ አትሌቶች ፊታቸውን ወደ ማራቶን እያዞሩ ይገኛል፡፡ በትራክ ውድድር ላይ ነግሠው የነበሩ አትሌቶቹ በጎዳናው ላይ ምን ይፈጥራሉ? በአብዛኛው ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል፡፡