Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የናይጄሪያ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያው ምሁር ገጠመኝ

ትኩስ ፅሁፎች

አንድ ሰኞ ቀን ከሌጎስ አንድ ሰዓት ተኩል ብቻ የሚወስደው በኦዮ ክፍለ አገር ዋና ከተማ ኦቢዳን ዳርቻ ወደ ሚገኘው ዓለም አቀፍ የሞቃት አየር ንብረት ሰብሎች እርሻ ምርምር ጣቢያ ሄድኩ፡፡ በግቢው የሚታየው የዛፍ የሳር አበባ የምርምር ሥፍራ ትምህርታዊ መግለጫ የሚሰጥበት መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲኒማ ማሳያ ሥፍራ የአስተማሪዎቹ መኖሪያ የውስጥና የውጭ የስፖርት ሜዳዎች ምግብ ቤቱ ወዘተ. የናይጄሪያን ሳይሆን፣ የአውሮፓን ወይም የአሜሪካን የዩኒቨርሲቲዎች ግቢ አስመስለውታል፡፡ ስለዚህም የአጉ ተወላጆች ግቢውን ትንሿ አሜሪካን ብለው ሰይመውታል፡፡

እኔም በሁሉም ነገር የተመቻቸ በመሆኑ አብዛኛዎችን የኅብረት ሥራ ኮርሶችን የማዘጋጀው እዛ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ምጂንዳዲና እኔ ስድስት ወር የወሰደ ጥናት ብዙ ጉዞና ብዙ ምርምር ካደረግን በኋላ ‹‹የእርሻ ኅብረት ሥራ በናይጄሪያ›› የሚል አንድ መጽሐፍ አሳተምን፡፡ መጽሐፉን በሚመለከት ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት የተውጣጡ ታዋቂ የእርሻ ምርምር ባለሙያዎች በአብዛኛው ከዩኒቨርሲቲ የመጡ አስተማሪዎችና ፕሮፌሰሮች የተሳተፉበት የሦስት ቀን አገር አቀፍ ስብሰባ አካሂደናል፡፡ አዳራሽና መኝታ ቤት ተከራይተን ምግብም እዚያው ከፍለን እየተመገብን ስብሰባው በጥሩ ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡

ማታ እራቴን ለመብላት ምግቡን ይዤ በረንዳ ስወጣ አንድ ትልቅ ሰው በጣታቸው ወደ እኔ እያመለከቱ ወደ እሳቸው እንድሄድ ጠሩኝ፡፡ በውጭ ዓለምና በአገር ውስጥ በልዩ ልዩ ሚዲያ መልካቸውን ስለማውቀው ማን እንደሆኑ ለማወቅ ጊዜ አልወሰደብኝም፡፡

ዞር አልኩና ‹‹እኔን ነው የሚጠሩኝ?›› አልኳቸው ‹‹አዎን! አንድ ጊዜ ና››! አሉኝ ምግቤን እንደያዝኩ ወደ ተቀመጡበት ጠረጴዛ ጠጋ አልኩና ‹‹ይቅርታ የምንተዋወቅ አይመስለኝም፡፡ ማን ልበል? አልኳቸው፡፡ ‹‹እኔ ጄኔራል ኦሊሴጉን ኦቦሳንጆ የቀድሞው የናይጄሪያ ፌዴራል መንግሥት ፕሬዚዳንት ነኝ፤›› አሉኝ ፈገግ ብለው፡፡ ‹‹ክቡር ፕሬዚዳንት ከማደንቃቸው ጥቂት የአፍሪካ መሪዎች ውስጥ እርስዎ አንዱ ነዎት፡፡ ምንም እንኳን እዚህ አገር ብዙ ብቀመጥም ዛሬ በአካል ስለተገናኘን ደስታዬ የላቀ ነው›› ስላቸው እጃቸውን ዘረጉልኝና ጨበጥኳቸው፡፡ ከዚያም አብሬያቸው እንድቀመጥ ጋበዙኝ፡፡

አብራቸው የተቀመጠችው አንደኛዋ የፉላኒ ባለቤታቸው ቀላ ወፈር ያለች ከመሆኗም ባሻገር በጣም ቆንጆና ሳቂታም ናት፡፡ እሳቸውን እያየች ‹‹እኮ ጠይቀው! ›› አለቻቸው፡፡ ‹‹ቅድም ወደ እኛ እንድትመጣ የጠየቅሁህ ባለቤቴ ይህ ሰውዬ ከማሊ የመጣ ነው ስትል፣ እኔ ደግሞ ከኢትዮጵያ ነው ብዬ ስለተከራከርን ነው፡፡ ከየትኛው አገር ነህ?›› ብለው ጠየቁኝ፡፡ ‹‹እርስዎ የዓለም አቀፍ ሰው ስለሆኑ በትክክል ኢትዮጵያዊ መሆኔን አውቀውታል፤›› አልኳቸውና ‹‹ከአክብሮት ጋር ክቡርነትዎ እዚህ የእርሻ ምርምር ጣቢያ ምን ለመሥራት እንደመጡ መጠየቅ ቢፈቀድልኝ?›› ብዬ በትህትና ጠየቅኳቸው፡፡ ‹‹እኔ የገመትኩት ምናልባት ለሌላ ስብሰባ የክብር እንግዳ ሆነው ስብሰባውን ሊከፍቱ የመጡ መስሎኝ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት እዚህ አይአይቲኤ ውስጥ ስለሽንብራ ሰብል አተካከልና ምርት ኮርስ ስለሚሰጥ እሱን ለመከታተል ነው የመጣሁት፡፡ በመጭው ዓመት በብዙ ሔክታር ማሳ  ላይ ሽንብራ ለማምረት ሐሳብ አለኝ፤›› አሉኝ፡፡ ጄኔራሉና የትልቁ የአፍሪካ አገር መሪ  የነበሩት አዛውንት የሽንብራ ልማት ኮርስ እወስዳለሁ ሲሉኝ በጣም ገረመኝ፡፡

… ከኦቦሳንጆ ጋር ያለው ግንኙት አድጎ አንድ ወቅት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ካርተር ከኚሁ ሰው ጋር ተቀምጠው ወግ ጀመሩ፡፡ ካርተር በወሬ መሀል! ‹‹ኢትዮጵያውያን ስሞች በሙሉ ትርጉም እንዳላቸው ተነግሮኛል፡፡ ስምህን ምን አልከኝ?›› ‹‹ስሜ ጌታቸው ይባላል›› ‹‹ትርጉሙ ምን ይባላል?›› “Master of all“ እንደ ማለት ስላቸው፡፡ ‹‹እንዴ ያንተማ ጠንከር ያለ ነው›› ብለው ሁለቱም የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ከት ብለው ሳቁ፡፡

  • ጌታቸው ተድላ (ዶ/ር) ‹‹የሕይወቴ ጉዞዬና ትዝታዎቼ›› (2008 ዓ.ም.)
- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች