- በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ተወስኗል
- ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ የያዙ የባንክ ሒሳቦችና አክሲዮኖች ታግደዋል
በወንጀል የተወሰደ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትን ለማስመለስና በሙስና ተግባራት ላይ የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ያስችላል የተባለ ሰፊ የወንጀል ምርመራ፣ በሰባት የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ላይ እየተካሄደ መሆኑ ተሰማ።
እየተካሄደ ነው በተባለው የወንጀል ምርመራና የሕግ ማስከበር ዕርምጃ ጎን ለጎን፣ የተመዘበረ የመንግሥት ሀብት እንዳይሰወርና እንዳይጠፋ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲታገድ መደረጉም ተገልጿል።
ይህ የተገለጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የ2014 በጀት ዓመት የኦዲት ባለድርሻ አካላትን የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ሰኞ ኅዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በገመገመበት ወቅት ነው፡፡
የ2014 ዓ.ም. የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ያቀረቡት የቋሚ ኮሚቴው የፐብሊክ ፋይናንስ ኦፊሰር (ባለሙያ) አቶ ዘሪሁን አስፋው እንደተናገሩት፣ በወንጀል የተገኘ ሀብትን ለማስመለስ የኦዲት ባለድርሻ አካላቱ በ2014 ዓ.ም. ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት 175.7 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ማስመለስ ተችሏል።
በወንጀል የተወሰደ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትን ለማስመለስና የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረትም በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡ መሆናቸውን፣ በአሁኑ ወቅትም በሰባት የመንግሥት ተቋማት ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ካቀረቡት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል።
ከእነዚህ ተቋማት መካከልም የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ባለሥልጣን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሽ ናቸው።
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ባለሥልጣን ላይ በሕግ የሚያስጠይቅ ተግባር ካለ ምርመራ ተደርጎ ዕርምጃ እንዲወሰድ በማለት፣ የኦዲት ባለድርሻ አካላት መድረክ መጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን አቶ ዘሪሁን ገልጸዋል።
‹‹በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሊቢያ ጤና ሳይንስ የተባለ ኮሌጅ ከባለሥልጣኑ ከተሰጠው ዕውቅናና ፈቃድ ውጪ በአግባቡ ላልተማሩ ግለሰቦች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በመስጠት፣ ይህንንም ማስረጃ የወሰዱ ግለሰቦች በጤና ተቋማት በሕክምና አገልግሎት ተቀጥረው እየሠሩ መሆኑ ተረጋግጦ ሰፊ የወንጀል ምርመራ በኦሮሚያ ክልል ፖሊስና በክልሉ ዓቃቤ ሕግ በጋራ እየተሠራ ነው፤›› ብለዋል።
በተመሳሳይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ ያቀረበውን የኦዲት ግኝት መሠረት በማድረግ በሕግ የሚያስጠይቅ ድርጊት ካለ ምርመራ ተደርጎ ዕርምጃ እንዲወሰድ መጋቢት 23 ቀን በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ ሰፊ የወንጀል ምርመራ መጀመሩን ተናግረዋል። በተጨማሪም በብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲወሰድ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሰፊ የምርመራ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም በመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ በተቀናጀ የመንግሥት መሠረተ ልማት አቅርቦት ኤጀንሲ ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የመንግሥትን ሀብት በመመዝበር በተለዩ ስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲካሄድ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ በፍትሕ ሚኒስቴር ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ጭብጦችን የመለየት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን አመላክተዋል።
የወንጀል ምርመራ እንዲካሄድባቸው የተለዩት ዩኒቨርሲቲዎችም ቡሌ ሆራ፣ አርባ ምንጭ፣ ወልዲያ፣ ሐዋሳ፣ መቱ፣ ደብረ ታቦር፣ ዲላና ዋቻሞ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ከያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ጋር በተያያዘ የተፈጸመው የሀብት ምዝበራ በሕግ ሒደት ላይ መሆኑን በመጠቆም፣ ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ የተጠረጠረው ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት ሀብትና ንብረት በፍርድ ቤት መታገዱን፣ ከዚያም የኮንስትራክሽን ድርጅቱን ሀብትና ንብረት ተረክቦ እንዲያስተዳድር የፌዴራል ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በፍርድ ቤት መሾሙን ገልጸዋል።
በወንጀል የተወሰዱ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብቶችን ለማስመለስ በተደረገ ክትትልና ሰፊ የሕግ ማሰከበር ሥራ 175.7 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ለማስመለስ መቻሉን የገለጹ ሲሆን፣ የፍርድ ሒደቶች እስኪጠናቀቁም የተመዘበሩ ሀብቶች በፍርድ ቤት እንዲታገዱ መደረጉንም አብራርተዋል።
በፍርድ ቤት የታደጉ ሀብቶችን አስመልክቶ በሰጡት ዝርዝር ማብራሪያ ከአሥር ድርጅቶች በጥቅሉ 701.8 ሚሊዮን ብር የያዘ የባንክ ሒሳብ መታገዱን፣ በተመሳሳይም 744.8 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖችና 27.6 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቦንድ (የዕዳ ሰነድ) መታገዱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም 364 ተሽከርካሪዎች፣ 155 ቤቶች፣ 617 ማሽነሪዎች፣ 41194 ካሬ ሜትር የመሬት ይዞታና 1,830 ዶላር ላይ በፍርድ ቤት ዕግድ መጣሉን ገልጸዋል።