Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበደቡብ ክልል የዛላ ወረዳ ነዋሪዎች በከፍተኛ ረሃብ ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ

በደቡብ ክልል የዛላ ወረዳ ነዋሪዎች በከፍተኛ ረሃብ ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ

ቀን:

በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን የዛላ ወረዳ ነዋሪዎች ከፍተኛ ረሃብ ውስጥ መሆናቸውን ወረዳው  አስታወቀ፡፡

የዛላ ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ ጽሐፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አንጀሎ፣ በወረዳው ከሚኖረው 114,337 ሕዝብ ውስጥ 83,704 ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውን፣ ማክሰኞ ኅዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ በወረዳው ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ሕፃናት 381፣ ለመካከለኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ 3,895 እና ዝቅተኛ የምግብ እጥረት የገጠማቸው ደግሞ 12 ናቸው፡፡

በተፈጠረው ከፍተኛ የምግብ እጥረት ምክንያት 3,004 የሚያጠቡና ነፍሰ ጡር እናቶች በጉዳት ላይ መሆናቸውን አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡

በወረዳው ከአራት ዓመታት ተኩል በላይ ወቅቱን ጠብቆ ዝናብ ባለማግኘቱ፣ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የቀንድ ከብቶች አደጋ ላይ መውደቃቸውን ጠቁመዋል፡፡

በእነዚህ ዓመታት በሁሉም የዝናብ ወቅቶች ዝናብ እንዳላገኙ የገለጹት አቶ አዲሱ፣ በወረዳው የሚገኙ ወራጅ ውኃና ወንዞች መድረቃቸውን አስረድተዋል፡፡ በፌደራልና በክልል እንዲሁም በዞን የሚደረጉ ድጋፎች ቢኖሩም፣  ከችግሩ ስፋት አኳያ በቂ እንዳልሆኑ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ፣ የሚቀርበው ዕርዳታም በቤት ውስጥ መንቀሳቀስ ለማይችሉና ለአቅመ ደካሞች ይቀርባል ብለዋል፡፡

በወረዳው 36 ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ ረሃብ የተከሰተባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዛላ ወዳ በበቆሎ ምርት የምትታወቅ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ በአሁን ወቅት ምንም ዓይነት ምርት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ የእንስሳት ሀብትን ለገበያ በማቅረብ ወረዳዋ የምትታወቅ መሆኑን፣ በረሃቡ ሳቢያ በመኖና በውኃ እጥረት ማኅበረሰቡ ያለውን ሸጦ መጨረሱን አክለው ገልጸዋል፡፡

አቶ ካሳሁን ዓባይነህ የጎፋ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ናቸው፡፡ በዞኑ በሰባት ወረዳና በአራት ከተማ አስተዳደር መዋቀሩን፣ ረሃቡ የተከሰተው በሦስት ወረዳዎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች ለተከታታይ አራት ዓመታት ዝናብ ባለመዝነቡ፣ የተከሰተ ችግር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አካባቢው ሙሉ በሙሉ የዝናብ ጥገኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ካሳሁን፣ በተለይ ዛላ ወረዳ በከፍተኛ ሁኔታ ለረሃብ ተጋልጧል፡፡

በዞኑ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው 155,248 ዜጎች እንደሆኑ ከነዚህም ዛላ ወረዳ፣ ኡባ ደብረ ፀሐይ፣ ዳንባ ጎፋ በከፊል፣ በቶ ከተማ አስተዳደር በከፊል ለረሃብ ከተጋለጡ ወረዳዎች መካከል መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የጎፋ ዞን የጤና ቢሮ መምሪያ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማኖቴ በበኩላቸው፣ በዞኑ ረሃብ በተከሰተባቸው ወረዳዎች የእናቶችና የሕፃናት ሞት ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል፡፡

በተለይ የሕፃናት ሞት ከቀን ወደ ቀን በጤና ተቋማት ሪፖርት እየተደረገ መሆኑን፣ በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ ረሃቡ መጠናከሩን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...