- የወለጋ ዞኖች በኮማንድ ፖስት ሥር እንዲተዳደሩ ተጠየቀ
በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች እየተፈጸሙ ባሉ ጭፍጨፋዎች የፌዴራል መንግሥት በሕዝብ የተሰጠውን ኃላፊነት ባለመወጣቱ፣ ‹‹መንግሥት ነኝ የማለት የሞራል ልዕልና የለውም፤›› ሲሉ ሦስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና እናት ፓርቲ ትናንት ማክሰኞ ኅዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢሕአፓ ጽሕፈት ቤት በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብረሃም ሃይማኖት፣ መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት ለማስጠበቅ ተቸግሮ ከሆነም መፍትሔ በሕዝቡ ዘንድ ስለሚሆን በግልጽ ይናገር ብለዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ትልቁ ሀብት አርሶ አደሩ ነው፡፡ አሁን ግን አርሶ አደሩ ተረጋግቶ መሥራት የማይችልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው፤›› ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
ፓርቲዎቹ የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በክልሉ እየተከናወነ ስላለው ጭፍጨፋ ማብራሪያ እንዲሰጡ በጋራ ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም ዘላቂ ሰላም እስከሚሰፍን ድረስ የወለጋ ዞኖች በኮማንድ ፖስት ሥር እንዲተዳደሩና መከላከያ አካባቢውን እንዲቆጣጠር ጠይቀዋል፡፡
ዜጎች መንግሥትን የሚፈልጉት ከውጭና ከውስጥ ኃይሎች በመከላከያ፣ ከጉልበተኞች ደግሞ በፖሊስ እንዲያስጥላቸው መሆኑን፣ እንዲሁም በፍርድ ሥርዓት ወንጀለኞችን እንዲቀጣላቸው ነው ሲሉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ከተሠራ ግን ‹‹ለስሙ አለን እንጂ መንግሥት አልባ ነን›› ሊያስብል እንደሚችል ፓርቲዎቹ ገልጸዋል፡፡ መጋቢ ብሉይ አብርሃም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሩ በነፃነት እየተዘዋወረ መሥራት አልቻለም ብለው፣ ‹‹አሥራ አንዱም ጥቃቅን መንግሥታት ችግር ፈጣሪ ሆነዋል፤›› ሲሉ የክልል አደረጃጀቱን የችግሩ ምንጭ እንደሆነ አድርገው አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ የወለጋ ዞኖች ውስጥ ሸኔ ተብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን ንፁኃን ዜጎች ጭፍጨፋ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ፣ መንግሥትም ለበርካታ ጊዜያት ማስቆም አቅቶት የሚተችበት መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል፡፡
የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ በበኩላቸው፣ የመከላከያ ሠራዊት ጭፍጨፋውን የማስቆም አቅም እንዳለው እንደሚያምኑ፣ መንግሥት ትክክለኛ እንቅስቃሴና ሙከራ ቢያደርግ ሕዝቡን ማዳን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
‹‹እዚያ አካባቢ ባለው ኃይል ማስቆም አቅቶ ከሆነ ልክ እንደ ሰሜኑ ለሕዝብ ጥሪ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ከባድ ከሆነ በሕዝብ ኃይል ሊቆም እንደሚችል ብዙ ቦታ ታይቷል፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ማሙሸት በተጠያቂነትና መሰል ጉዳዮች ላይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ አሁን ባለው የፌዴራሊዝም አደረጃጀት በዋነኝነት ተጠያቂው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ነው ብለዋል፡፡ የመረጡትና ግብር የሚከፍሉት ኢትዮጵያውያን በክልሉ እየተገፉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የክልሉ መንግሥት በዚያ መንፈስ ዜጎችን ማዳን ካልቻለ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ዜጎችን መታደግ የግድ መሆን አለበት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡