Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጎህ ቤቶች ባንክ ወደ ቤት ልማት ለመግባት ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በስምንት ወራት ውስጥ 7.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ባንኮች በተለየ የቤት ልማትን መሠረት በማድረግ ሥራ የጀመረው ጎህ ቤቶች ባንክ፣ የኅብረተሰቡን አቅም ያገናዘበ ቤት ግንባታ ውስጥ ለመግባት የሚያስችለው ፈቃድ እንዲሰጠው ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ማቅረቡ ተገለጸ፡፡

የጎህ ቤቶች ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አስማረ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባንኩ ለቤቶች ልማትና ለተያያዥ ሥራዎች ከሚያቀርበው ፋይናንስ በተጨማሪ፣ እንደ አንድ የሞርጌጅ ባንክ በቤት ልማት ላይ ለመግባት ስትራቴጂ ቀርጿል፡፡ ይህንንም ከግብ ለማድረስ ለብሔራዊ ባንክ ፈቃድን ለማግኘት ጥያቄ አቅርቦ መልስ እየተጠባበቀ እንደሆነ አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡ ፈቃዱ ከተገኘ ቤት ልማት ላይ በሰፊው በመግባት፣ በተለይ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን አቅም ያገናዘበ ቤቶችን ለመገንባት አቅዷል፡፡ ከወዲሁም የመገንቢያ ቦታ ለማግኘት ከተለያዩ ከተሞች አስተዳደሮች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

‹‹እኛው ራሳችን ቤቶች ማልማት ውስጥ ልንገባ እንችላለን፤›› ያሉት አቶ ሙሉጌታ፣ ወደ ቤቶች የልማት ሥራ እንዲገቡ ገፊ ምክንያት የሆናቸው በሪል ስቴት አልሚዎች የሚገነቡ ቤቶች ውድ በመሆናቸው ነው፡፡ በተለይ መካከለኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ለመደገፍ፣ እንዲሁም ከመክፈል አቅም ጋር የተጣጣሙ ቤቶችን ማልማት ይኖርብናል ለሚል ወደ እዚህ ውጥን መሸጋገራቸውን አመልክተዋል፡፡ ‹‹የቤት ችግር መነሻው እጥረት ነው፡፡ ሊኖር የሚገባው የቤት ቁጥር ከኅብረሰባችን ፍላጎት ጋር ፈጽሞ የሚጣጣም አይደለም፤›› የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፣ ከዚህ አንፃር የቤቶችን ቁጥር መጨመር አስፈላጊ በመሆኑ እንደ አንድ መፍትሔ ሊቀርብ የሚችለው፣ ባንካቸው በአዲስ አበባና በክልል በከተሞች ለመገንባት ያቀደው የመክፈል አቅምን ያገናዘበ የቤቶች ልማት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ወደ ልማቱ ሲገባም በተለይ ዋጋው አቅምን ያገናዘበ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፣ እሳቸው የሚመሩት ባንክ ሞርጌጅ ባንክ እንደመሆኑ መጠን ብሔራዊ ባንክ ቤት የማልማት ሥራ ውስጥ እንዲገባ ሊፈቀድ ይገባል ብለው ያምናል፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጎህ ቤቶች ባንክ የመጀመርያ ጠቅላላ ጉባዔውን ትናንት ባካሄደበት ወቅት እንዳስታወቀው፣ በመጀመርያ የሥራ ዘመኑ በስምንት ወራት ውስጥ ከታክስ በፊት 7.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ገልጿል፡፡

ባንኩ ሥራ በጀመረበት የመጀመርያ ዓመት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ስምንት ወራት አበረታች እንቅስቃሴዎችን አድርጓል ያሉት የጎህ ቤቶች ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሰቢ አቶ ጌታሁን ናና፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 256.6  ሚሊዮን ብር ማድረሱንም ጠቅሰዋል፡፡ ለደንበኞች የተሰጠው ብድርና ቅድመ ክፍያ ደግሞ 298.5 ሚሊዮን ብር እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ባንኩ የሰጠው ብድር ለቤት ግዥና ለግንባታ እንዲሁም ከቤት ልማት ጋር ለተያያዙ ሥራዎች የተሰጠ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባንኩ ከሰጠው ብድር ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሙሉጌታ፣ ባንኩ በዋናነት ለቤት መግዣና መሥሪያ የሚሆን ብድር ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱም ከሰጠው አብዛኛው ብድር ለቤት መግዣና መሥሪያ የዋለ ነው፡፡ በጣም ጥቂት የሚሆነው ብድር ደግሞ ለሪል ስቴት አልሚዎች የተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሰው የመክፈል አቅም ከሁለት ሚሊዮን ብር እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርስ ብድር መልቀቁን አመልክተዋል፡፡ የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን አቶ ሙሉጌታ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የቦርድ ሰብሳቢው ባቀረቡት ሪፖርት ደግሞ ባንኩ በስምንት ወራት ውስጥ 121.7 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ወጪ ደግሞ 113.8 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴው በስምንት ወራት ውስጥ 7.9 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡንም የቦርድ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ያልተጣራ ትርፍ ውስጥ ሕጋዊ መጠባበቂያ 1.98 ሚሊዮን ብር፣ የረዥም ጊዜ የግብር ዕዳ ወጪ ሥሌት ማስተካከያ 459.5 ሺሕ ብር፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ለብድርና ለተሰብሳቢዎች የሚያዝ ተጨማሪ መጠባበቂያ 3.1 ሚሊዮን ብር ተቀናሽ ሆኖ የተጣራ ትርፉ 2.4 ሚሊዮን ብር እንደሆነም አቶ ጌታሁን ገልጸዋል፡፡

‹‹ባንኩ የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት፣ ንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በተቀዛቀበት፣ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚ በተዳከመበትና ጠንከራ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውድድር ባለበት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ነው፤›› ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው፣ ይሁን እንጂ የቤቶች ገበያ በኢትዮጵያ ትልቅና በአንፃራዊነት ገና ያልተነካ በመሆኑ የባንኩ ዕድል አቅም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአንፃሩ ዕድሉን ለመጠቀም ለቤቶች ብድር የሚውል የረዥም ጊዜ ፈንድ ማሰባሰብ ለባንኩ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በተለይ ቤት ለመሥራት መሬት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ከተሞች በተለይ በአዲስ አበባ መሬት ማግኘት እጅግ ፈታኝ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ባንኩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በቅርበት የሚሠራ ሲሆን፣ ለኅብረተሰቡ የመኖሪያ ቤቶችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት ሁሉ ባለድርሻ አካላት መደገፍ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡   

ጎህ ቤቶች ባንክ ባለፈው ዓመት ካፒታሉን ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ባሳለፈው ውሳኔና መሠረት ተጨማሪ ሁለት ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች በሚቀጥሉ ሁለት ሳምንታት መሸጥ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ በጎህ ባንክ እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ጠቅላላ መጠኑ 1.2 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ የጎህ ባንክ የተከፈለ ካፒታል 780 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ አገልግሎቱን እንደታሰበው በአራት ቅርንጫፍ በ127 ሠራተኞች ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች