Friday, March 1, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ንፁኃንን ከአጥቂዎች መከላከል ነው!

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ንፁኃን ያለ ኃጢያታቸው የሚጨፈጨፉበት ምክንያት ብዙዎችን ግራ ከማጋባት አልፎ፣ የአገርና የጠቅላላው ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ እያሳሰበ ነው፡፡ መንግሥት ሰላማዊ ሰዎችን ከአጥቂዎች ጥቃት መከላከል አቅቶት ንፁኃን በጅምላ ለፍጅት ሲዳረጉ፣ የነገዋ ኢትዮጵያ ህልውና ጉዳይ ለብዙዎች አስፈሪ ቢሆን አይገርምም፡፡ ለዘመናት የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች አለመከበር አንገብጋቢ በሆነባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ አሁን ደግሞ በሕይወት ለመኖር አዳጋች የሆነበት ጊዜ ላይ መደረሱ አሳዛኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ እያቃታቸው፣ በዚያ ላይ ደግሞ ወገኖቻቸው ያለ ምንም ጥፋት እየታረዱ ሲጣሉ የአገራቸው መፃኢ ዕድል ቢያሳስባቸው አይፈረድባቸውም፡፡ ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት የሌላቸው ወገኖች፣ ሰብዓዊነት ከውስጣቸው ተንጠፍጥፎ ባለቀ ጨካኞች ሲጨፈጨፉና የሚከላከልላቸው ሲጠፋ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ በተደጋጋሚ አድኑን እየተባለ ጩኸቱ ከአድማስ እስከ አድማስ ቢያስተጋባም፣ ገዳዮችን የሚያስቆም በመጥፋቱ ንፁኃን በማንነታቸው እየተመረጡ እየተጨፈጨፉ ነው፡፡ መንግሥት ንፁኃንን መታደግ ካልቻለ ማን ነው የሚታደጋቸው? የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት እኮ ንፁኃንን ከአጥቂዎች መከላከል ነው፡፡

በተለይ ወለጋ ውስጥ በተደጋጋሚ በንፁኃን ወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው የጅምላ ግድያ ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ነው? ወይስ ሌላ የማይታወቅ ፍላጎት አለ? ለሚለው  የብዙዎች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሚደፍር አልተገኘም፡፡ አገር የሚያስተዳድረውን መንግሥት ከበላይ ሆኖ የሚመራው ብልፅግና ፓርቲም ሆነ አመራሮቹ፣ አባላቱና ደጋፊዎቹ ለዚህ ዘግናኝ ግድያ መልስ ያላቸው አይመስሉም፡፡ በተደጋጋሚ ወለጋ ውስጥ ንፁኃን በማንነታቸው እየተለዩ ሲጨፈጨፉ፣ ለዓመታት ከኖሩባቸው ቀዬዎች ንብረታቸው እየተዘረፈና እየወደመ ሲፈናቀሉና የሰው ልጅ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ መከራና ሰቆቃ ሲደርስባቸው የሚታደጋቸው አልተገኘም፡፡ ወለጋ የደም ምድር ሆኖ ለአማራ ተወላጆች ብቻ ሳይሆን፣ ለኦሮሞ ተወላጆች ጭምር መከራ መቁጠሪያ ከሆነ ሰነባበተ፡፡ በአካባቢው በከፍተኛ ሁኔታ ይንቀሳቀሳል የሚባለውን ኦነግ ሸኔ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጠፋዋለሁ ያለው የክልሉ መንግሥትም፣ ውስጡ ምን እንደገጠመው አይታወቅም እሱም ድምፁ ከጠፋ ሰነባበተ፡፡ መንግሥት ንፁኃንን የመከላከል ተቀዳሚ ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን በኪራሙና በጊዳ አያና ወረዳዎች ውስጥ የሚኖሩ ንፁኃን ዜጎች በተፈጸመባቸው ጥቃት፣ ከሞት የተረፉት በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በእግራቸው በመሸሽ የመንግሥት ያለህ እያሉ ነው፡፡ በተጠቀሱት ወረዳዎች ውስጥ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካቶች መገደላቸውና መፈናቀላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በአሁኑም ጥቃት ለመግለጽ የሚያዳግት ግፍ መፈጸሙን ሕይወታቸውን ያተረፉ ወገኖች እየተናገሩ ነው፡፡ በተሽከርካሪዎች በመታገዝ የሰላማዊ ዜጎችን መንደሮች በመውረር የግፍ ጭካኔ የፈጸሙ ታጣቂዎች፣ ያለ ምንም ከልካይ የፈለጉትን እየገደሉ መሆናቸው ጭምር ነው የተነገረው፡፡ በአካባቢው በተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚፈጸም እየታወቀ ንፁኃንን የሚከላከል ኃይል ማስፈር ሲገባ፣ አሁንም ለጆሮ መስማት የሚከብድ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት በአካባቢው ተፈጽሟል፡፡ መንግሥት ከእንዲህ ዓይነቱ የለየለት አውሬነት ይከላከለን የሚል ጩኸት በርክቷል፡፡ በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎችም በግድያዎችና በዕገታዎች ምክንያት ዜጎች መንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የመከላከል ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ ቁርጡን ይናገር፡፡

በተለይ ወለጋ ውስጥ በተደጋጋሚ በተፈጸሙ ጥቃቶች በተዓምር ሕይወታቸው ተርፎ ምስክርነታቸውን የሰጡ ወገኖች፣ ጥቃት አድራሾችም ሆኑ የአካባቢ አስተዳዳሪዎችና የፀጥታ አካላት ድርጊቱን እየተናበቡ እንደሚያከናውኑ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ተጠናቆ ብልፅግና ፓርቲ ካሸነፈ በኋላ በመላ አገሪቱ ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች፣ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በነበሩ መድረኮች ነዋሪዎች ይህንን እውነታ አረጋግጠዋል፡፡ የአገር ሽማግሌዎች ሳይቀሩ መረጃ እያጣቀሱ ችግሩን  ተናግረዋል፡፡ በብልፅግና የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ውስጥ የኦነግ ሸኔ ደጋፊዎች እንዳሉ ከአባላት ሳይቀር በግልጽ የተነገረ ነው፡፡ አንድ ፓርቲ አባላቱ የዓላማና የተግባር አንድነት ሊኖራቸው ሲገባ፣ በሁለት ባርኔጣ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች እንደፈለጉ የሚፈነጩበት ከሆነ ውጤቱ ይህ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በወለጋ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎችም ይህ ግራ የተጋባ ነገር መኖሩ በስፋት ይነገራል፡፡ ገዥው ፓርቲ ውስጡን ሳያጠራ በዚህ ሁኔታ አገር እንዴት መቆም ትችላለች? የዜጎች ሰላምና ደኅንነትስ እንዴት አስተማማኝ ይሆናል? መንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነቱን ካልተወጣ ማን ይወጣለት?

በተለያዩ አቅጣጫዎች ጥያቄዎች ሲነሱ መንግሥት መልስ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ መንግሥት አገርን በቅጡ ማስተዳደር አልቻልክም ተብሎ ብቻ አይደለም ጥያቄ እየቀረበለት ያለው፡፡ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚረዳ መፍትሔ እየቀረበ መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ ዜጎች በማንነታቸው ብቻ እየታደኑ እንደ አውሬ ሲጨፈጨፉ፣ መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ እስከ አፍንጫው የታጠቀ ኃይል ዜጎችን እያገተ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ሲጠይቅ፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የታጣቂዎች መፈንጫ ሆነው ማምረት ሲቸገሩና ሠራተኞቻቸው ሲታገቱ፣ ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ ሲቸግራቸውና በአጠቃላይ ሰላምን ደኅንነት ሲቃወስ መንግሥት ዝም ብሎ የሚያየው ምን እስኪሆን ድረስ ነው? ከመንግሥት ጋር ጉዳይ አለኝ የሚለው ኦነግ ሸኔስ ንፁኃንን በማንነታቸው እያሳደደ የሚፈጀው ለምን ዓይነት ዓላማ ነው? እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ድርጊት ኦሮሚያ ውስጥ መረን ተለቆ ዜጎች ለመከራ ሲዳረጉ የኦሮሞ ሽማግሌዎች፣ ፖለቲከኞችና ምሁራን ለምን ዝም ይላሉ? በሌላው ወገን ያሉ ኢትዮጵያውያንም ይህ ሰቆቃ እንዲያበቃ በሰብዓዊነት ስሜት ለግፍ ሰለባዎች ለምን በጋራ ድምፅ አይሆኑም? መንግሥትስ ለምን ዝም ይላል?

የመንግሥት ሥልጣን የያዛችሁ በሙሉ ከፓርቲ ዓላማና ፍላጎት በላይ ለሕዝብና ለአገር አስቡ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ከዳቦ በላይ ሰላም አንገብጋቢ ሆኗል፡፡ በከፋ ድህነት ውስጥ ሆኖ መከራውን የሚያየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም አጥቷል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በስንት መከራ በውጭ አሸማጋዮች ግፊት በሰላም ስምምነት እንዲቋጭ ተስፋ ሰጪ ውጤት መታየት ቢጀምርም፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚስተዋለው ሁኔታ ግን ወደ አደገኛ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይመስላል፡፡ ይህንን አደገኛ ነገር መቀልበስ የሚቻለው በሰላማዊ ንግግር ሊሆን ሲገባው፣ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ግድያና ውድመት በዚህ ከቀጠለ ማቆሚያው ይቸግራል፡፡ አሁንም ደጋግመን የምንጠይቀው መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ምን አዳገተው የሚለውን ነው፡፡ ችግርን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እየተቻለ ንፁኃንን የሚጨፈጭፉስ ምን ይጠቀማሉ? በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳብ ተለዋውጦ ችግሩን መፍታት አንድ አማራጭ መሆን ሲገባው፣ አገሪቱን የደም ምድር ማድረግ ለታሪካዊ ጠላቶች ካልሆነ በስተቀር ማንንም እንደማይጠቅም ይታወቃል፡፡ የንፁኃን ደምና ዕንባ ስለሚፋረድ አጥቂዎች ከድርጊታችሁ ተቆጠቡ፡፡ መንግሥትም ተቀዳሚ ኃላፊነቱ ንፁኃንን ከአጥቂዎች መከላከል እንደሆነ ይወቅ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...

የጋራ ድላችን!

ከፒያሳ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ለበርካታ ደቂቃዎች ሠልፍ ይዘን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...