Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በየዓመቱ አርባ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን እያስተዋወቀ መሆኑን ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱን የግብርና ልማት በምርምር የሚያግዙ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የማልማት፣ የግብርና ምርምር ሥርዓቱን የማስተባበር ተልዕኮ የተሰጠው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በዓመት አርባ የሚደርሱ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን እያስተዋወቀ መሆኑን ገለጸ፡፡

በየዓመቱ ከሦስት እስከ አራት ሺሕ የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችን እንደሚሠራ ያስታወቀው የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ አዳዲስ ዝርያዎች እያስተዋወቀ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ከግብርና ጋር የተያያዙ ቴክኖሎጂዎችን የማቅረብ ተልዕኮ የተሰጠው ኢንስቲትዩቱ፣ ከተመሠረተበት ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጊዜ ጀምሮ ከሦስት ሺሕ በላይ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቁን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቶ ኢስሞ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በየዓመቱ የተለያዩ አዳዲስ ዝርያዎች ላይ ምርምር አድርጎ ለአርሶ አደሩ እንደሚያቀርብ የተናገሩት ፈቶ (ዶ/ር)፣ አገሪቱ ትኩረት አድርጋ ከምትሠራባቸው ዝርያዎች በተጨማሪ መልመድ አለባቸው ተብለው በተለዩት የወይራ ዘይት፣ የፓልም ዘይትና ሌሎች ዝርያዎችን ከውጭ በማምጣት እየሞከረ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው፣ በየዓመቱ የተለያዩ ዝርያዎች ከውጭ ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ ከሁለት እስከ ሦስት ሺሕ የስንዴ፣ የበቆሎ፣ የምስርና ሌሎች የእህል ዝርያዎች፣ እንዲሁም አገር በቀል የሆኑ መዓዛማ ዕፀዋቶች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራን ነው ብሏል፡፡

ፈቶ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ግብርና በአራት ምሰሶዎች ላይ ተመርኩዞ ይሠራል፡፡ የመጀመሪው በምግብ ሰብል ራስን መቻል ሲሆን፣ ኤክስፖርትን ማሳደግ ሁለተኛው ምሰሶ ነው፡፡ ከውጭ የሚገቡ አንዳንድ የግብርና ምርቶችን በተኪ ምርቶች መተካት ሦስተኛው ሲሆን፣ አራተኛው የሥራ ዕድል መፍጠር ነው፡፡

ኢንስቲትዩቱ አራቱ ምሰሶዎችን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችንና ዕውቀቶችን ማፍለቅና ለኅብረተሰቡ ማድረስ ዓብይ ተልዕኮው መሆኑ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ገቢ ምርትን ለመተካትና ኤክስፖርትን ለማሳደግ ከሚሠሩ ሥራዎች የመስኖ ስንዴ አንዱ በምሳሌነት የሚገለጽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት የስንዴ ምርትና ምርታማነት ቀድሞ ከነበረበት በሔክታር 25 እና 26 ኩንታል ምርት፣ በአሁኑ ወቅት ከ32 እስከ 33 ኩንታል መድረሱን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በሔክታር የሚገኘው ምርት እንዲሻሻል የግብርና ምርምር የራሱ የሆነ ድርሻ ነበረው የተባለ ሲሆን፣ ዝርያ ከሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎች በበለጠ ለምርታማነት 50 በመቶ አስተዋፅኦ እንዳለውና ለዚህም የኢንስቲትዩት ድርሻ ጉልህ መሆኑ ተገልጿል፡፡

 በተያያዘም የግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩትና ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር “Shaping Agriculture for Greater Impact” በሚል መሪ ቃል አገር ዓቀፍ የግብርና ኮንፈረንስና ኤግዚቢሽን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) የመሰብሰቢያ አዳራሽ አዘጋጅተዋል፡፡

ለሁለት ቀናት የተዘጋጀው የግብርና ኮንፈረንስ በሰብል ልማት፣ በእንስሳት ልማት፣ በተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ዙሪያ በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት የተሰሩ ትልልቅ ሥራዎችንና የዘርፉን ማነቆዎች በጥልቅ የሚዳስስ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

እርሻን ከማዘመን አኳያ በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት ሜካናይዜሽን ላይ ሰፋፊ ሥራዎች እንደተሠራ የሚያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከእርሻ እስከ ማጨጃ እንዲሁም መጋዘን ላይ የተሠሩ ሥራዎችን ገልጸዋል፡፡

ግብርና ከማዘመን፣ ከአግሮ ኢንዱስትሪ ጋር የተያያዙ በርካታ ውጤቶች እንደተገኙ፣ ነገር ግን እነዚህ ስኬቶች በቂ ባለመሆናቸው በቀጣይ እንዴት የበለጠ መሠራት አለበት? የሚለውን ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት በማሰብ አገር አቀፍ የግብርና ኮንፈረንስ መዘጋጀቱን ማንደፍሮ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

በግብርና ኮንፍረንሱ ምርታማነት፣ ፋይናንስና ግብይት በተመለከተ በአገር አቀፍ ደረጃ የታዩ ክፍተቶችና በቀጣይ መሠራት በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ አሉ የተባሉ ምሁራን ተሰባስበው ወይይት የሚያደርጉ መሆናቸውንና በሥርዓተ ምግብ፣ በግብርና፣ እንዲሁም ‹‹የምሁራን ሚና በግብርና ትራንስፎርሜሽን ዙሪያ›› የሚሉ ሦስት ትልልቅ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች