Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያና የሩሲያ የንግድ ልውውጥ በጦርነቱ ምክንያት ማሽቆልቆሉ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፉት አሥር ወራት በኢትዮጵያና በሩሲያ መካካል የነበረው የንግድ ልውውጥ በጦርነቱ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ ተነገረ፡፡

ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው ሁለት ወራት በቀረው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ምክንያት ‹‹ስዊፍት›› ከተሰኘው ዓለም አቀፉ የክፍያ ሥርዓት የወጣችው ሩሲያ፣ እ.ኤ.አ. 2022 ከተጀመረ ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው የንግድ ልውውጥ በ66 በመቶ መውረዱን የተናገሩት፣ በአዲስ አበባ የሚገኙት የሩሲያ የኢኮኖሚ፣ ሳይንስ፣ ቴክኒካልና ንግድ ትብብር ኮሚሽን ልዑክ ሊቀመንበር አቭጌኒ ፔትሮቭ ናቸው፡፡

ከሦስት ዓመታት በኋላ ለስምንተኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያና የሩሲያ መንግሥታት የሳይንስ፣ የቴክኒክ፣ የኢኮኖሚና የንግድ ትብብር የጋራ ኮሚሽን ኮንፈረንስ ኅዳር 27 ቀን  2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መካሄድ የሚጀምር ሲሆን፣ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይቆያል ተብሏል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2021 በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ንግግድ ልውውጥ 225 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ቢሆንም፣ እየተገባደደ ባለው እ.ኤ.አ. 2022 ሩሲያ ከምዕራባውያኑ ጋር በገባችው የጦርነት እሰጥ አገባ ምክንያት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው የንግድ ለውውጥ 45 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

ከ50 በላይ የቢዝነስ ልዑካን ይዘው አዲስ አበባ የሚገኙት የቡድኑ መሪ እንደገለጹት፣ ሩሲያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በኢነርጂ፣ በጂኦሎጂ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን፣ በትምህርትና በጤና መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ መሥራት ትፈልጋለች ብለዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ ሩሲያ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር የቆየ ግንኙነት እንዳላት በመጥቀስ፣ ሩሲያ የምንጊዜም ወዳጅ በማለት አንቆለጳጵሰዋል፡፡ አክለውም ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው አስቸጋሪ ወቅቶች በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፣ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን የተጫወተችውን ሚና በማስታወስ፣ ኢትዮጵያ በሁለቱ አገሮች መካከል ባለው ግንኙነት ከፍተኛ የሆነ እርካታ እንደሚሰማት ተናግረዋል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የተደረገው የአገር በቀል ኢኮኖሚክ ሪፎርምና ግዙፍ የፖሊሲ ለውጥ አሁን እየታየ ላለው የኢኮኖሚ መነቃቃት መነሻ እንደሆነ ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያቀደቸውን ዘላቂ አረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማት ለማሳካት  በትክክለኛው መስመር ላይ በመሆኗ፣ የሩሲያ ባለሀብቶች በኢትየጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች