Thursday, September 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የእጃቸውን ያግኙ!

ሰላም! ሰላም! ወገኖቼ እንደምን ሰነበታችሁ? መቼም ድብልቅልቅ ያለ የዓለም ዋንጫ ውድድር ስሜት ውስጥ እንደሆናችሁ አልስተውም፡፡ አንድ የእኔ ቢጤ ደላላ ወዳጄ በቀደም ዕለት፣ ‹‹አንበርብር እንዴት ነው ነገሩ?›› ብሎ ጆሮውን አሹሎ ተጠጋኝ፡፡ እኔ ደግሞ ምን ፈልጎ ነው ብዬ፣ ‹‹የቱ ነገር?›› ማለት፡፡ እሱ ትዝብት በሚመስል አስተያየት እየገረመመኝ፣ ‹‹አንተ ደግሞ ነገር አይገባህም? ወይስ ችግር አለብህ? የዓለም ዋንጫው ነገር እንዴት ነው…›› ሲለኝ፣ ‹‹አርፈህ ፉክክሩን ኮምክም…›› ከማለት ውጪ ሌላ የምለው አልነበረኝም፡፡ እኛ ለጊዜው ተመልካቾች እንጂ ተሳታፊዎች ስላልሆንን፣ በሌሎች ፉክክር እየተዝናን ነው መሰንበት ያለብን፡፡ አንዳንዱ ሰው እኮ ነገረኛ ከመሆኑ የተነሳ የማይገባንን ነገር እያዳወረ ትንተና ሊያሠራን ይቃጣዋል፡፡ ወገኖቼ ነገር በረድ ሲል ሴራ የሚጎነጎነው ስፖርትን ጭምር በመታከክ እንደሆነ መቼ ጠፋን፡፡ ለዚህም መሰለኝ ከሴራና ከሸር በስተቀር ሙያ የሌላቸው ክፉዎች አገራችንን ችግር ውስጥ የሚከቱት፡፡ ለማንኛውም እኔ አንበርብር ምንተስኖት ለአገሬ ሰላም ከመመኘት አልፌ፣ እሳት የሚጭሩባት ጠላቶቿ መቀመቅ ይገቡ ዘንድ ነው ቀንም ሌትም የማስበው፡፡ ይህ ደግሞ እንደሚሳካ አትጠራጠሩ እላለሁ፡፡ አገሬን እንደሆነ ፈጣሪ ጦር የሰበቁባትን እኩዮች ብቻ ሳይሆን፣ በአጉል ብልጠት ሴራ የሚሸርቡትን ጭምር እንደሚያሳፍራቸው አትጠራጠሩ እላለሁ፡፡ እውነትን የያዘ አያፍርምና!

ወደ መደበኛው ወጋችን ስንመለስ እነሆ ማንጠግቦሽ ባሌ ለምን ወጉ ይቅርበት ብላ ነው መሰል፣ በሬዲዮ ስሜን ጠርታ ‹ስምህን አውሰኝ› የሚለውን ዘፈን ጋበዘችኝ። በአንዴ የዝነኝነት መንፈስ ውርር አድርጎኝ ዙሪያ ገባዬን ቁልቁል ማየት ጀመርኩ። እንግዲህ አስቡት? በሬዲዮ ስሜ ተጠራ ብዬ አካባቢዬን ያቃለልኩ፣ ሕዝብ በድምፁ ተወካዩ አድርጎ ቢመርጠኝ ምን ልሆን እንደምችል? ለካ አንዳንዱ ወዶ አይደለም የመጣንበትን ረስቶ የምንሄድበትን የሚያቀዣብረን ብዬ ከራሴ ጋር አውርቼ ዝም አልኩ። እህ ለማን ይወራል ታዳያ ይኼ? ትርጉምና የነገር አፈታት እያስተዛዘቡን እያያችሁ እስኪ አሁን እንዲህ ያለ ጨዋታ ስትጫወቱ። የተጋበዝኩት ዘፈን ሳያልቅ የቀጠርኳቸው ደንበኞቼ እንዳይደውሉ ፈጣሪን ስማፀን ዘፈኑ ተቋረጠ። መብራት የጠፋ መስሎኝ በሞባይሌ ሬዲዮ ልከፍት ስጣደፍ አንድ ለዛ ሙጥጥ የሆነ የሁካታ ዘፈን ቀጠለ። ቅጥል አልኩ። በስንቱ ሞገደኛ እንቃጠል!

የገጠመኝን ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስነግረው በእሱ ቤት ማሾፉ ነው፣ ‹‹የተቃወሚዎችህ ሴራ ነው እባክህ…›› አይለኝ መሰላችሁ? ታዲያ እኔም ስልኬ ካልጮኸ ከነበርኩበት ሥፍራ መንቀሳቀስ ስለማልችል፣ ያ ሞዛዛ የሁካታ ዘፈን ሰባት ደቂቃ ደልቆ እስኪያልቅ ብክንክን ብዬ አስጨረስኩት። ድሮስ ምን ምርጫ አለህ አትሉኝም? ውበትና ሙዚቃ እንደ ተመልካቹ ነው ባዮች መሆን አለባችሁ። መቼም እንዲህ ስትሉ ካርል ማርክስ ቢሰማችሁ መደብና ኪነት ምንም ቢሆን ምን ተነጣጥለው አያውቁም። ኪነት ሁሉ የወከለው መደብ ማሳያ ነው እያለ ቅጽ በቅጽ ላይ የጻፈበትን ዘመን ታስረግሙት ነበር። ግን እንዴት ነው የእኛ የውበት፣ የእውነትና የኪነት ብስለት ከመደቡም፣ ከአተያዩ ማዕዘንም ሆነ ከምኑም ከምኑም የሌለበት መሰለሳ? ለእኔ ብቻ ነው? መቼም ነገር በማስረጃና በምሳሌ ነውና የሚያምረው እስኪ የደላላ ስልኬ እስኪጮህ ትንሽ ላብራራላችሁ። ተንታኝ በበዛበት ዘመን እኔስ ባብራራ ምናለበት!

ይኼውላችሁ ዘመኑ እንደምታዩት ሥር ነቀል ለውጥ ያለ ሥር ሰደድ መረጃና ዕውቀት እያመጣብን ተቸገረን። የት ነን? የት ነበርን? ወዴት ነን? መሰል ጥያቄዎች አፍ እስኪያሲዙ ድረስ ሁሉም ተናጋሪ፣ ሁሉም አዋቂ፣ ሁሉም ፈራጅ፣ ሁሉም ነብይ… ሆነ። በበኩሌ ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ መብት እጄንም እግሬንም አውጥቼ ብታገልም፣ በመዘባረቅና ሐሳብን በነፃነት በመግለጽ መካከል ሰፊ ልዩነት ያለ ይመስለኛል። ይኼንን ስል ያ ቦጅባጃ ተለማማጅ የአስረሽ ምቺው ሙዚቃ ዘፍኖ እንዳበቃ፣ ስለሙዚቃ በተለይ ስለአገራችን ሙዚቃ ከእኔ በላይ ላሳር ያሉ ወጣቶች አየሩን ተቆጣጠሩት። ገና ከመጀመራቸው አንደኛው፣ ‹‹እዚህ አገር ለጥበብ ክብር የሚሰጥ ሰው የለም…›› ብሎ በጠቅላላው ወቃን። እንዲህ በጅምላ መፈረጅ የለመዱ ናቸው እኮ በጅምላ ሊፈጁን ሲያደቡ የኖሩት፡፡ የእጃቸውን አያጡም!

ከዚያ ወዲያው ይኼንን ብሎ እንዳበቃ፣ ‹‹እንዲያውም አንዴ የሆነ ጋዜጣ ላይ ስለጥበብ ያለንን ውስን ዕውቀትና የማቃለል ስሜት የሆነ ጽሑፍ አንብቤ ነበር…›› አለና አረፈዋ። አስቡት እንግዲህ። ዕውቀቱ ይሁን። ግን ‹ለጥበብ ክብር የሌለበት አገር ነው› ብሎ በጅምላ የሚወቃን ደፋራችን እዚያው ላይ የጋዜጣውን ስም፣ ያነበበውን ጽሑፍ፣ ታትሞ የወጣበትን ቀን፣ እንዲያው እሱ እንኳ ቀርቶ የጸሐፊውን ማንነት ሳይጠቅስ ‹የሆነ… የሆነ…› ብሎ ሲያቃልለው ስትሰሙ ትዝብት አያጭርም? እንግዲህ ተተቺውና ተተቺው እንዲህ በተምታቱበት አገር፣ መምታቱ ሳያንስ አየሩን የተቆጣጠሩት አዋቂዎቻችን ከሦስት ዓረፍተ ነገር ሁለቱን ‹አክችዋሊ፣ ኢቬንቹዋሊ፣ ክሪቲካሊ…› እያሉ በመግባባት ናፍቆት እያንከራተቱን ስትሰሙና ስታዩ፣ ቅድም እንዳልኳችሁ ምን ላይ ነበርን? የት ነን? ወዴት ነው የምንጓዘው? ብሎ ጥያቄ ምን እርባና ምንስ ትርጉም ኖሮት ይጠየቃል? አገኛችሁኝ? በእርግጥም ተግባብተናል!

ዛሬ እንዲህ መዓት በማውረድ የተወጠርከው ሚስትህ የጋበዘችህን ዘፈን ስላቋረጡት ነው ስትሉኝ ሰማሁ መሰል? ሽሙጡስ ሽሙጥ ነው። መቼስ ‹አጥብቆ ጠያቂ የእናቱን ሞት ይረዳል› በሚል፣ አጥብቆ መጠየቅን በመርዶ ጠሪና መከራ ናፋቂ አስተሳሰብ ተርጉሞ በሚረዳ ወገን መሀል ነኝና ለግዜው ይኼን ልተወው። ምክንያቱም ደንበኞቼ ወዲያው ደወሉና እኔም ከተመጥኩበት ተነስቼ ሄድኩ። ደንበኞቼ ሻጮች ናቸው። የሚሸጡት የወንድማቸውን ታታ አውቶብስ ነው። የአውቶብሱን ጥሬነት ሳይና ከገበያው አነስ ባለ ዋጋ ሊሸጡት እንዳሰቡ ስረዳ በወሬ በወሬ አወጣጣቸው ጀመር። ‹‹ምን እባክህ ምን እንዳስነኩት አናውቅም…›› አለኝ አንደኛው። ያኔ ነው የወንድማቸው ንብረት መሆኑን የተረዳሁት። ኋላ አፍታተው ሲነግሩኝ ይኼ ምናምን አቅምሰውት አበደብን ያሉት ወንድማቸው አስተዳደጉንና ጭምትነቱን በሚቃረን ሁኔታ የማይጠየቁ ጥያቄዎችን እየጠየቀ፣ ማኅበረሰቡ ደፍሮ የማይናገራቸውንና ሲነገሩም የሚፀየፋቸውን፣ ፆታዊና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን እየጠየቀና በድፍረት አቋሙን እየሰበከ ማኅበራዊ ሕይወቱ ተጎሳቁሎ ኖሯል። ሰው ደግሞ ማኅበራዊ ኑሮው ከተጎሳቆለ፣ ወዳጅ ቤተሰብ እየፈራው እየተጠራጠረው ከመጣ ባያብድም ያው አበደ ነው በእኛ ፍረጃ። እንደወረደ ነው የምንፈርደው!

ብቻ ነገሩ ጥርት ሳይልልኝ እንዲሁ ስለማላውቀው ሰው ስብሰለሰል ሰነበትኩ። ውሎ አድሮ ያ አውቶብስ ጆሮውን ተባለ። እኔም ኮሚሽኔ እጄ ገባ። ግን ነገሩ እየከነከኝ ውሎ ሲያድር ለባሻዬ ልጅ አጫወትኩት። እሱም፣ ‹‹እንደ ዋዛ ጉዱ ካሳን ሆኖባቸው ይሆናላ…›› ብሎኝ አለፈው። ‹አገሬን የአገሬ ሰው ካስለቀቀኝ እኮ ቆየ› ብሎ ለሰብለ ወንጌል የነገራት ትዝ አለኝ። ነው ወይስ እናንተም ምን የረባ ያወራል ብላችሁ አትጠይቁኝም? እኔም ካልተጠየቅኩ አልናገርም ብዬ ተዘግቼ ቀረሁ እንዳለው ሆኖ፣ የዚያም ሰው ነገር የሚናገረውን የሚያዳምጠው፣ የሚጠይቀውን በአግበቡ የሚመለስለት አጥቶ ይሆን ብዬ አሰብኩ? የምሬን እኮ ነው። ከገበያው እኩል ሰው የአዕምሮ በሽተኛ የበዛው፣ እንዲሁ ስታስቡት የሚናገረውን የሚሰማው የሚጠይቀውን የሚመልስለት ብስል እየጣ አይመስላችሁም ግን? አንዳንዴ መጠርጠር ጥሩ ነው!

ብቻ እኛ አውቶብስ ተቃጥሎ ወይ ተገልብጦ ወይ በሌላ ነገር የእንጀራ ገመድ ሲዘጋ ካልሆነ በቀር፣ እንዲህ ባለው ነገር አንድ ሰው ኑሮው ሲቃወስ አገር የሚቃወስ አይመስለንም። ማስመሰል ተክነን የማይመስለን ነገር ብዛቱን ስታስቡት ደግሞ ሌላው ጉድ ነው። ጉድ እኮ ነው።  ታዲያ እኔና አዛውንቱ ባሻዬ መቼ ዕለት እንዲሁ የባጥ የቆጡን እያነሳን እየተጫወትን ሳለ በቴሌቭዥን ምን እናያለን? የአንድ የአገራችን ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ምሁር ስለፍቅር እስከ መቃብር ሲተነትኑ። ባሻዬ በዘመኔ ከቅዱሳን መጻሕፍት ሌላ አንድ ብቻውን ተመስጨ ያነበብኩት የፈጠራ ድርሰት እያሉ መጽሐፉንና ደራሲውን ያሞካሻሉ። ከምሁሩ አንድ ትምህርት እንቀስማለን ብለን አሰፍስፋናል። ይናገራሉ ንግግራቸው ግራ ነው። በአማርኛ ጀምረው በእንግሊዝኛ ይጨርሱታል። ጉራማይሌ!

‹‹የጉዱ ካሳ ማድነስ?›› ሲሉ ምሁሩ፣ ባሻዬ ‹‹ማድቤት ማለቱ ነው?›› ይሉኛል ወደ እኔ ዞረው። ‹‹እኔ ምን አውቄ?›› እመልሳለሁ። ‹‹ኢንተለክቹዋሊ ስታስበው በፍቅር እስከ መቃብር ድርሰት ውስጥ ያሉት ካራክተሮችና ስቶሪው ጭምር ከዘመኑ አድቫንስድ ነው…›› ሲሉ ምሁሩ ባሻዬ፣ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር ብሎ የጻፈ ፈረንጅ ይኖር ይሆን?›› ይሉኛል። ያው ትከሻዬን ሰብቄ ዝም እላለሁ። ምሁሩ ሲያደናብሩን ባሻዬ ወደ እኔ እየዞሩ በጥያቄ ሲያፋጥጡኝ፣ እንዲሁ የጓንጉቸር ትርዒት እያየን ምሁሩ ስለትንተናቸው ተመስግነው ዝግጅቱ አለቀ። ኋላ ባሻዬ ቆዝመው ቆይተው፣ ‹‹እኔ ምልህ?›› አሉኝ። ‹‹እርስዎ የሚሉኝ?›› ስላቸው፣ ‹‹እንዲያው ከስልሳዎቹ አንስቶ ወደ ውስጣችን እያየን ውስጣችን ያዳፈነብንን ብርሃን ከመለኮስ፣ እንዲህ በረንጅ አፍ መፍቻና በፈረንጅ ቅብ ሀተታ ነገር ዓለሙን የምናጨመላልቀው ምን ነክቶን ነው?›› ሲሉኝ ዝም አልኩ። በልቤ ግን እንዲህ ብያለሁ፣ ‹ጉዱ ካሳ እንደገና በምፀቱ ሲያጫውተን ይሆናላ!› ድንቄም ምሁርነት አትሉም፡፡ ወቸ ጉድ ያሰኛል!

በሉ እንሰነባበት! የሚያተርፈው አትርፎ የሚከስረው ከስሮ በብቅል ጭማቂ የትካዜ አምሮቱን፣ የጨዋታ ጉጉቱን ሊወጣ የሰርክ መቃጠሪያችንን ግሮሰሪ ደርሰናል። አስቴር አወቀ ‹አገሬ ኑሪ… አገሬ ኑሪ…› ትላለች። አድማጭ፣ ‹እንዲያ በይ…› እያለ ይወዛወዘል። ‹ሀብታም ደሃ ሳይል ሁሉን አስተካዡ…› ስትል ጋባዥና ተጋባዥ ብርጭቆውን እኩል እያነሳ ይቻረሳል። የባሻዬ ልጅና እኔ ጥጋችንን ይዘን በትዝብት ስንቁለጨለጭ አንድ የማናውቀው ሰው ጠጋ ብሎ፣ ‹‹መታዘብ ክልክል ነው!›› ብሎ ጆሯችን ላይ ጮኸ። የባሻዬ ልጅ ጠጋ ብሎ በጆሮዬ፣ ‹‹በዓለም ላይ የእኛ ሰው ብቻ እንደሆነ ታውቃለህ ከሰኞ እስከ ሰኞ የሚጠጣው?›› ይለኛል። ‹‹ተው እባክህ!›› አልኩት ደንግጬ። ጉድ ፈላ በሉ!

‹‹ህሊናና ሆድ አላረጅ እያሉ ዕድሜ ፍሬን እንደ በጠሰ መኪና ቁልቁል ወደ ማብቂያው ሲገሰግስ ስታይ፣ አንዳንዴ አንተም ብትሆን እኮ መተንፈሻ ያምረሃል…›› አለኝ፡፡ ደግሞ ሌላው ብድግ ብሎ፣ ‹‹አንዱ እኮ ነው፣ ስም አልጠራም። ደግሞ እኮ አብሮ አደጌ ነው። ምጥ እንደ ያዛት ሴት በጭንቅ በጥብ እግሬ ላይ ወድቆ ቤትህን አስይዘህ ገንዘብ ካልተበደርክልኝ አለኝ። በወር በሁለት ወር ካልመለስኩልህ ከምላሴ ፀጉር አለ። በአብሮ አደግ ይጨከናል?›› ሲል አድማጩ በተማሪ ቤት ድምፅ፣ ‹አይጨከንም!› ይላል። ‹‹እኔም አልጨከንኩም። በወሩ ምን ሰማህ አትሉኝም?›› ሲል አሁንም ጀማው ‹ምን?› ይለዋል። ‹‹አሜሪካ ገብቷል ለካ? እኔና ቤቴ ለሐራጅ ወጥተናል ለካ?›› ሲል የሐዘን ማጉረምረም ተከተለው። እኔና የባሻዬ ልጅ ተያይተን በሐዘኔታ አንገታችንን ነቀነቅን። በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸመውን ክህደት፣ ደባ፣ ሸርና ክፋት ሳስብና በየቤቱ የሚሰማውን እሮሮ ለማሰብ ስሞክር አገሬ ድቅን አለችብኝ፡፡ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙባት ደባዎች ሳይበቁ፣ አሁን ደግሞ ጡቷን የነከሱ ሴረኞችን ድርጊት ሳስብ ራሴ ሊፈነዳ ደረሰ፡፡ ለማንኛውም የእጃቸውን ያገኛሉ ብዬ ተፅናናሁ፡፡ በእርግጥም የእጃቸውን ያገኛሉ፡፡ መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት