ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ የነበረው ‹‹የቃቄ ውርድወት›› ትውፊታዊ ተውኔት በመጽሐፍ መልክ ቀረበ።
ትውፊታዊ ተውኔቱ ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመት በፊት ከጉራጌ ሕዝብ መካከል በመነሳት በሰላማዊ የትግል መንገድ የሴት ልጅን ሰብዓዊ ክብርና መብት ለማስከበር ጠንካራ እንቅስቃሴ በማድረግ ጉልህ ድርሻ ባላት የቃቄ ውርድወት ታሪክ ላይ ያተኮረ ነው።
በጉራጌ ባህልና ሥነ ቃል ላይ ያተኮረው ተውኔቱ በጫንያለው ወልደ ጊዮርጊስ ተጽፎ በዳግማዊ ፈይሳ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከሦስት ዓመታት በላይ እስከ ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲቀርብ 67 ሺሕ ሰዎች ተመልክተውታል።
ትውፊታዊ ተውኔቱ ከምዕት ዓመታት በፊት የነበረውን የጉራጌ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት፣ ሥነ ቃል፣ መልክዓ ምድርና የዕደ ጥበባት ገጽታን በሀገረሰባዊ ሙዚቃ እያዋዛ የሚያስቃኝ፣ ከ110 በላይ ባለሙያዎችን ያሳተፈ የሙሉ ጊዜ የመድረክ ተውኔት እንደነበረ ከብሔራዊ ቴአትር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ ዓምና በሚያዝያ አጋማሽ የታተመው መጽሐፉ ኅዳር 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በተመረቀበት መርሐ ግብር ላይ የተውኔቱ ቅንጭብ ቀርቧል፡፡