በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የሚመለከተው የመውጫ ፈተና በበይነ መረብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናው ከመደበኛ ተማሪዎች ባሻገር የማታና የርቀት ተመራቂ ተማሪዎችን እንደሚመለከት የጠቆሙት ሳሙኤል (ዶ/ር)፣ ፈተናው በመንግሥትና በግል ዩኒቨርሲቲዎች ለሚማሩ የቀን፣ የማታና የርቀት መርሐ ግብር ተመራቂዎች እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ከዘንድሮ ጀምሮ በመንግሥትና በግል ዩኒቨርስቲዎች ተግባራዊ የሚደረገውን የመውጫ ፈተና በበይነ መረብ ለመስጠት መታቀዱንና ተቋማቱም የመሠረተ ልማት አቅሞቻቸውን ከወዲሁ በማረጋገጥ ለፈተናው ዝግጅት እንዲያደርጉም ጠቁመዋል።
የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የመውጫ ፈተናው የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ ባሻገር የተማሪዎችንና የተቋማቱን ብቃት ለማሳደግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የከፍተኛ ትምህርት አገራዊ ቅድመ ምረቃ የመውጫ ፈተናን በአግባቡ ለመምራትና ለማስተዳደር የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና ማስፈጸሚያ መመርያ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. መጽደቁ ይታወሳል፡፡
በፍትህ ሚኒስቴር ተመዝግቦና ፀድቆ ለትግበራ ይፋ የሆነው መመርያ፣
በመውጫ ፈተና ዝግጅት ሊካተቱ የሚገባቸውን አገራዊ ዝቅተኛ የትምህርት ብቃት መመዘኛዎች፣ የሙያ ሥነ ምግባር ደንቦችና ተቋማት ሊከተሏቸው የሚገቡ የአሠራር ሥነ ሥርዓቶችን አካቷል።
በመመርያው ዝግጅት ሒደት ውስጥ በሥርዓተ ትምህርትና ፈተና ዝግጅት ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ የሙያ ማኅበራት ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ግብዓት እንደሰጡበት መመርያው በጸደቀበት ወቅት መገለጹ አይዘነጋም፡፡