Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ሥራ ከሰሞነኛነት ይላቀቅ!

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አንድ የኒዶ ምርት ዓይነት የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈ በመሆኑ ሸማቹ ይህንን ምርት እንዳይጠቀም ሰሞኑን በመገናኛ ብዙኃን አሳስቧል፡፡ 

ባለሥልጣኑ እንዲህ ያለውን መረጃ እንዲህ ባለ ሁኔታ ለሕዝብ በማሳወቅ ጥንቃቄ እንዲደረግ በማስታወቁ ምሥጋና ሊቸረው ይገባል፡፡ ሌሎች ተቋማትም በኃላፊነታቸው ልክ ሸማቾችንም ሆነ ተገልጋዮችን ሊጎዱ የሚችሉ ምርቶችን በመለየት እንዲህ ያለውን መረጃ በመስጠት ከአደጋ የመታደግ ልምድ ማዳበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ 

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕዝብን ለአደጋ የሚያጋልጡ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርቶች በርካታ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ባለሥልጣኑ እንደ ሰሞኑ ዕርምጃው ሌሎች ምርቶችም ይፈትሽ ማለት ተገቢ ነው፡፡ 

ምክንያቱም ዛሬ በተለያየ የገበያ ሥፍራዎች፣ እንዲሁም ትልልቅና ዘመናዊ በሚባሉ ሱፐር ማርኬቶች ሳይቀር የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶች በሽ ናቸው፡፡ የመገልገያ ጊዜያቸው ተደልዞና ተስተካክሎ የሚቀርቡ ምርቶችም ቤት ይቁጠራቸው በኮንትሮባንድ የሚገቡ ምርቶችም በተለያዩ መደብሮች ሼልፎች ላይ ከመታየታቸው አንፃር ኅብረተሰቡን የመታደጉ ሥራ ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑን ያሳያል፡፡ 

ምርቱ የተመረተበትን ቀንና የመገልገያ ጊዜውን የሚያመለክተውን ጽሑፍ በመደለዝና በረቀቀ ዘዴ በማስተካከል ለሸማቹ የሚቀርቡ ምርቶች በአብዛኛው ምግብ ነክ ስለመሆናቸው ይነገራልና እንዲህ ያሉ ውንብድናዎችን ለመቆጣጠር አቅም ካልተፈጠረ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በኋላ ላይ ለመቆጣጠር ከባድ እንደማይሆን ማሰብ ይገባል፡፡ 

ሥራዬ ተብሎ ቢፈለግ ጥቂት የማይባሉ ምርቶችን እንዲህ ባለው መንገድ በማዘጋጀት ገበያ ውስጥ የሚለቁ ወንጀለኞች በርካታ ናቸው፡፡ 

ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን ለገበያ ከማቅረብ አንፃር ከሚፈጸሙ ወንጀሎች አንዱ በእነዚህ ጥራት በሌላቸው ምርቶች ላይ የሚታወቁ ብራንዶችን ምልክት ማተም ነው፡፡ ሰሞኑን እንኳን ፖሊስ በልሙጥ የጣሪያ ቆርቆሮ ላይ ፎርጂድ ማኅተሞችን እያኖሩ ለበያ ሲያቀርቡ የነበሩ ወንጀለኞችን መያዙ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበትን ምርት ብቻ ሳይሆን አስመስሎ የሚሠሩ ምርቶችን ለመቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ 

በሕገወጥ መንገድ የሚቀርቡ ምርቶች ወይም ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን ለመለየት የማይችል ሸማች ምርቶቹን እንዲገዛ ሲገደድ ጥራት ለሌለው ምርት ያልተገባ ዋጋ መክፈሉ ብቻ ሳይሆን በዚያ ዕቃ በመገልገላቸው የሚኖርባቸውን ጉዳት መታደግ የሚቻለው በአግባቡ የቁጥጥር ሥራውን መሥራት ሲቻል ነው፡፡ 

ከአምስትና ስድስት ሺሕ በላይ ምርቶች ወደ አገር የሚገቡት እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ምርቶች ተመርተው ወደ ገበያ የሚሠራጩበት አገር ውስጥ እንደመሆናችን መጠን እነዚህን ምርቶች የጥራት ደረጃና ለጤና እክል የሌላቸው ስለመሆኑ ማረጋገጥ የሚቻልበት አቅም ካልተፈጠረ በስተቀር በእነዚህ አዋኪ ምርቶች የሚጎዳው የኅብረተሰብ ክፍል እየጨመረ መሄዱ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ ጉዳቱ ብዙ ነው፡፡ የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችንና አጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት ምን ያህሉን ተቆጣጥረዋል ካልን ግን መልሱ ሊያስደነግጠን እንደሚችል ያለ ጥርጥር መናገር ይቻላል፡፡ 

በተለይ ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶች የጥራት ደረጃ በይበልጥ ያሳስባል፡፡ በሕጋዊ መንገድ ካስገቡት ውጪ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ የምግብ ምርቶች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ እንደሆኑ የሚታመን ስለሚሆን እነዚህ ምርቶች ላይ ትኩረት ማድረጉ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሌሎች ምርቶች ላይም ያለው ችግር የሰፋ በመሆኑ የሰሞኑ ባለሥልጣኑ ክልከላ ያደረገበትን ምርት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተመሳሳይ ምርቶችንም መፈተሽ ወቅትዊ ተግባሩ መሆን ይገባል፡፡ 

ባለሥልጣኑም ሆነ ሌሎች ተቆጣጣሪ አካላት ከደረጃ በታች የሚገቡ ምርቶች እጅግ በርካታ ስለመሆናቸው ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ዛሬ በፋርማሲዎች ከሚገኙ ምርቶች ምን ያህሉ ሕጋዊ መስመሩን የጠበቁ ስለመሆናቸው ቢፈተሽ ራሱ ብዙ ጉድ ሊወጣ ይችላል፡፡ 

የውበት መጠበቂያ ምርቶች ጉዳይም አብሮ የሚታይ ነው፡፡ በየጉራንጉሩ ግልጋሎት በሰጡ መያዣዎች እየተሞሉ ለገበያ እየቀረቡ የውበት መጠበቂያ የሚባሉ ቅባቶች፣ ቫዝሊኖች፣ ፓውደሮችና የመሳሰሉ ምርቶች ስለዚህ በየመደብሮች ውስጥ ያሉ ምርቶች ምን ያህል ትክክለኛው የሚለውን ቁጥጥር ማድረግ ጭምር የሚጠይቅ በመሆኑ ሕዝብ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ከመሯሯጥ ልክ እንደ ሰሞኑ ሕዝብ እንዲጠነቀቅ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ መረጃ መስጠቱ ብቻ ሳይሆን የድርጊቱ ፈጻሚዎችን በሕግ መጠየቅ የዕርምጃው አካል ሊሆን ይገባል፡፡ 

ዛሬ በየሰፈሩ የተለያዩ ምርቶች ማሸጊያዎችን የሚሰበስቡ ሰዎች የሚገዙትን ዕቃ የሚያስረክቡት ተመሳሳይ የሆኑ ምርቶችን ሞልተው መልሰው ለገበያ ለሚያቀርቡ ሕገወጦች ስለመሆኑ ለመገመት አያዳግትም፡፡ 

ስለዚህ ባለሥልጣኑም ሆነ እንዲህ ያለውን ነገር ለመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጣቸው ተቋማት ተከታትሎ ሕዝብ ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት መረጃ እንዲሰጠው ሁሉ ሕዝብ ላይ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ ሌሎች እንዲሁም ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ምርቶችን ተመሳስለው የቀረቡ ምርቶችን በመፈተሽ ሕዝብ የማዳን ተልዕኮዎችን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት