Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ሕጉ በተጨባጭ የማይተረጎምና ችግሮችን የማይፈታ ከሆነ ለሕገ መንግሥት ታማኝነት አይኖርም›› መድኅን ማርጮ (ዶ/ር)፣ የሥነ ማኅበረሰብ ልማት ፖሊሲ ጥናት ተመራማሪ

‹‹የወላይታ ሕዝብ የራሱ ክልል ይገባዋል፤›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ክላስተር የክልል አደረጃጀትን ሕገ መንግሥቱ አያውቀውም በማለትም በአንቀጽ 46 ላይ ሕዝቦች ወይም ብሔረሰቦች ማንነትን፣ ቋንቋንና የሕዝብ አሠፋፈርን መሠረት በማድረግ፣ የራሳቸውን የክልል አደረጃጀት ያቋቁማሉ ተብሎ በግልጽ መሥፈሩን ያጣቅሳሉ፡፡ ስለክልል ማቋቋም ሒደቱ በአንቀጽ 47 እና 48 ላይ የሠፈረውን በመጥቀስም የወላይታን ክልል የመሆን ጥያቄ የራስን መብት የማስከበር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ይከበር የሚል ነው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ በሐዋሳና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ያገለገሉት የሥነ ማኅበረሰብ ልማት ፖሊሲ ጥናት ተመራማሪው መድኅን ማርጮ (ዶ/ር)፣ በደቡብ ክልል የተለያዩ ብሔር አስተዳደሮች ያነሱት ክልል የመሆን ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው መሆኑን ነው የሚሞግቱት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩሳቱ እያየለ በመጣው በጉራጌ ዞን ቢሆንም፣ የክልልነት ጥያቄዎቹ ደቡብ ክልል ሲባል በቆየው አካባቢ፣ በአጠቃላይም በኢትዮጵያ የፈጠሩት ፖለቲካዊ ውጥረትን በተመለከተ ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ራስን በራስ የማስተዳደር ወይም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በኢትዮጵያ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

መድኅን (ዶ/ር)፡- ገና በዜሮ አካባቢ የሚዳክር ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳይ ሰፊና ከነፃነት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የዚህ መሠረታዊ አመላካች ጉዳዮች ከሚባሉት ደግሞ በመረጡት የመተዳደር ነፃነትን በውስጡ ታገኛለህ፡፡ እዚህ ውስጥ ደግሞ የመምረጥና የመመረጥ ነፃነቶች አሉ፡፡ የመምረጥና የመመረጥ ነፃነትን ስናነሳ ደግሞ መምረጥና መመረጥ ብቻ ሳይሆን፣ የመረጡት አካልም ሥራውን መሥራት አለመሥራቱን የመቆጣጠር ኃላፊነት አለ፡፡ የመረጥከው አካል በፈለግከውና በአግባቡ ነው ወይ የሚመራህ? የሚለውን መጠየቅ መቻል አለበት፡፡ በፈለግከው መንገድ የሚሄድና ከሰጠኸው ውክልና ወይም ሥልጣን ውጭ የሚሄድ መሆን አለመሆኑ መረጋገጥ መቻልም አለበት፡፡ በሰጠኸው ገደብ ውስጥ ካልተገኘ መጠየቅ አለብህ መባል አለበት፡፡ የተመረጡትም ወገኖች ቢሆኑ የመረጠኝ ሕዝብ የሰጠኝ ኃላፊነት አለና እሱን ኃላፊነት ተጠቅሜ ሕዝቡን ማገልገል አለብኝ ማለት አለባቸው፡፡ ይህ ሁሉ በዚህ ራስን በራስ ማስተዳደር ውስጥ ሊካተት የሚችል ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በአሀዳዊ ሥርዓትም ሆነ በፌዴራል መንግሥት ሥር ራስን በራስ ማስተዳደር የሚተገበርበት የራሱ መንገድ አለው፡፡ ሆኖም በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ ነፃነት ሊገደብ የሚችለው በሕግና በሥርዓት ብቻ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ ሥርዓት የተወሰነ ነፃነታችን ይገደብ ብለው ሰዎች ለመረጧቸው በፍላጎታቸው መብታቸውን አሳልፈው የሚሰጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ነፃነትን አሳልፎ መስጠትና በዚህ መንገድ ምራኝ ማለት የትም ያለ አሠራር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የነፃነት አገዳደብ በስምምነትና በሕግ የሚከናወን ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ኢመዋቅራዊ በሆነ መንገድ የሚከሰት የነፃነት መጓደል ነው፡፡ የከፋ ሊሆን የሚችለው የነፃነት ገደብም ይህ ነው፡፡ በሕግ ከተቀመጠው በላይ ወይም በታች ነፃነት ገደብ ሲኖረው የሚፈጠር ነው፡፡ ሰዎች የመረጧቸውን የመቆጣጠር መብት ሊያጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ በእኛ አገር ሁሌም ሲያጋጥም የምናየው ኢመዋቅራዊ የመብት ጥሰት ነው፡፡ እርግጥ ነው በአገራችን ሰው የፈለገውን የመምረጥ ነፃነትም የለውም፡፡ ተመራጮችም ቢሆኑ የመረጣቸውን ሕዝብ ሕግን ተከትለው ለማገልገል ሲቸገሩ ይታያል፡፡ ማገልገል ቢፈልጉም የሚችሉበት ዕድል ሲጠብ ይታያል፡፡ ብዙ ጊዜ ተመራጮች ታማኝነታቸው ለመረጣቸው ሕዝብ ሳይሆን፣ በተቀመጡበት ኃላፊነት ለሚያገኙት ጥቅማ ጥቅምና ገንዘብ ይሆናል፡፡ ተመራጮች ታማኝነታቸው ይህን ለሚያሟላላቸው አካል እንጂ ለሕዝቡ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ራስን በራስ ለማስተዳደርም ሆነ የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን በሕግ ብዙ ድንጋጌዎች ቢቀመጡም፣ በተጨባጭ በተግባር የሚተረጎሙበት አመቺ ዕድል የለም ነው የሚሉት?

መድኅን (ዶ/ር)፡- በተግባር አይተረጎሙም ነው የምለው፡፡ ግን ደግሞ በሕግም ቢሆን የተገደቡ ነገሮች አሉት፡፡ በሕግ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ሰጠሁ ትልና፣ ነገር ግን ገዳቢ የሆኑ የሕግ አንቀጾችን ልታወጣ ትችላለህ፡፡ ለምሳሌ ‹‹የቡድን መብት ይከበር›› ተብሎ በተለያዩ ብሔሮች ስም የክልል መዋቅር ወጥቷል፡፡ ነገር ግን በዚያ መዋቅር ሥር ያሉ አናሳዎች መብት ተገድቧል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች አናሳ የሚባሉት ወገኖች ራሱ ብዙኃን ሆነው ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የፈለገ ብዙኃን ቢሆኑም፣ በሕጉ መሠረት ራሳቸውን ለማስተዳደርም ሆነ ሌላ መብታቸው ይገደባል፡፡ ከተሞች ላይ ለምሳሌ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በቡድን መብት ማስከበር ስም ሲገደብ ይታያል፡፡ ብዙዎች የሚኖሩት በሕግና በመዋቅር መብታቸውን ተነጥቀው ነው፡፡ ክልሎቹ በስማቸው ከተሰየሙላቸው ብሔሮች ወይም ቡድኖች ውጪ በብዙው የኢትዮጵያ ክፍል መሠረታዊ መብቶቹን ተጎናጽፎ የሚኖር ዜጋም ሆነ ብሔር የለም፡፡ የክልሎቹ ባለቤት ከሆኑ ቡድኖች ውጪ በመረጡት ለመተዳደር፣ በቋንቋ ለመዳኘትም ሆነ ሌላ መብታቸውን ለመጎናጸፍ ተገድበዋል፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ በኢትዮጵያ የራስን ዕድል በራስ የመወሰንም ሆነ ራስን የማስተዳደር መብት በሕግ ቢቀመጥም፣ የማይተረጎመው በተግባር ነው ተብሎ ብቻ አይገለጽም፡፡ በሕግም የተገደበበት አጋጣሚ በመኖሩ ሁኔታው የተደበላለቀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በከተሞች አካባቢ የዚያው አካባቢ ተወላጅ ሆነህም ክልሉ በአንተ ብሔር ስም ካልተሰየመ በስተቀር፣ በቋንቋህ እንኳን አትዳኝም፡፡ ፍርድ ቤት የምትቀርበው ፋይልህን እያስተረጎምክ ነው፡፡ በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ የክልሎቹ ባለቤት የሆኑት አናሳ የሚባሉ ቡድኖች ናቸው፡፡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ብታየው በአስተዳደሩም፣ በአመራሩም፣ በዳኝነቱም ሆነ በሌላውም የክልሉን ሥልጣን የያዙት ነባር ብሔሮች ተብለው ክልሉ የተሰጣቸው ቡድኖች ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በኢትዮጵያ በክልሎችም ይሁን በከተሞች፣ በሕግም ይሁን በመዋቅሮች ችግር እየገጠመው ያለ መብት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በደቡብ ክልል ብዙ ወረዳዎች ወደ ዞንነት፣ እንዲሁም ብዙ ዞኖች ወደ ክልልነት ለማደግ የአስተዳደር ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ጥያቄ ለመመለስ መንግሥት ለምንድነው ሲቸገር የሚታየው?

መድኅን (ዶ/ር)፡- መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ያሠፈራቸውን የቡድን መብቶች ለማስፈጸም፣ ለሕዝብ በገባው ቃል እነዚህን መብቶች በተጨባጭ መሬት ላይ ለማውረድ ከሚችለው አቅም በላይ ሆኖበታል፡፡ ቡድኖቹ ራሳቸውን በራስ ማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ነውና ይችላሉ ይባላል፡፡ ይህንን መብታቸውን ለመጎናፀፍ ደግሞ ውስብስብ ነገር ሳይሆን የሚያስፈልጋቸው የጋራ ቋንቋ፣ ሥነ ልቦና፣ ባህልና አሠፋፈር ያለው ቡድን መሆን ብቻ ነው ተብሎ ተቀምጧል፡፡ በዚህ ቀላል መሥፈርት ተመርኩዘው ነበር፣ የቡድን መብቶችን የሚያስከብር ሕገ መንግሥት መሠረትን ያሉት፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ግን ቃል የገባው ተስፋ በተጨባጭ መስጠት የሚችለውን ያህል አልነበረም፡፡ ይህንን ሕገ መንግሥት የመሠረቱት ወገኖች በተጨባጭ ሕገ መንግሥቱ ያለበትን ጉድለት አጥተውትም አይደለም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ዜጋ አይደለም ከውጭ የመጣ ሰውም ቢሆን፣ ኢትዮጵያን በረገጠ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ መረዳት የሚችለው ችግር ነው፡፡ ሦስት ቀናት ያደረና አንድ ሦስት ሰዎችን ያናገረ የውጭ ሰውም ቢሆን፣ በተጨባጭ በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ለመረዳት አይቸግረውም፡፡

ሕገ መንግሥቱ ሲመሠረት ራስን በራስ የማስተዳደርም ሆነ፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የሚያስፈልጋቸው ቡድኖች በጣም ጥቂት ናቸው ተብሎ የታመነ ይመስላል፡፡ የእነዚያን ቡድኖች ፍላጎት ብቻ በማሟላት የሌሎችን መብትም ሆነ ሕግን ሳያስከብሩ ሥልጣንን አደላድሎ መኖር ይቻላል ተብሎ የታመነ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ሲጀመር ጀምሮ ሕገ መንግሥቱ የቡድን መብትንም ሆነ የአስተዳደር መዋቅርን በተመለከተ የገባው ቃል ለጥቂቶች ካልሆነ በስተቀር፣ በተጨባጭ ለሁሉም በተግባር የሚተረጎም አልነበረም ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከመነሻውም ሆነ በስተኋላ መንግሥት ለሕገ መንግሥቱ ያለው ታማኝነት የለበጣ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲጠነሰስም አንድ አምስት ቡድኖችን ይዤ፣ ሌላውን ግን በእነዚህ ሥር ጨምቄ ሥልጣኔን አደላድዬ መኖር እችላለሁ በሚል መንፈስ የተፈጠረ ይመስላል፡፡ በታማኝነት ሳይሆን በሸፍጥ የተደነገገ ይመስላል፡፡ የሌሎችን መብት ለማስከበር አላስጨነቀውም፡፡ መንግሥት አሁንም ይህንኑ ሕገ መንግሥት ይዞ ቀጥሏል፡፡ ይህ መንግሥት ራስን በራስ የማስተዳደር ነፃነትን ሳይሸራረፍ ወደ መሬት ለማውረድ የሚቸገርበት መሠረታዊ ምክንያት ነው፡፡

ሌላው ወደ መሬት ለማውረድ የሚገጥም ችግር ደግሞ ‹‹የክልልነት ጥያቄ ያነሳ ሁሉ ክልል ይሁን›› ከተባለ፣ በኢትዮጵያ ስንት ክልል ነው የሚኖረው? የሚለው ጥያቄ የሚፈጥረው ፈተና ነው፡፡ ቁጥሩ ጉዳይ ላይሆን ይችላል፣ ነገር ግን ቁጥሩ በጨመረ ጊዜ የአስተዳደር ራስ ምታቱም በዚያው ልክ ይጨምራል፡፡ መንግሥት የበዙትን ክልሎች የሚመራለት የራሱ የሆነ ታማኝ ኃይልን ለማፍራት መልፋት ይኖርበታል፡፡ የዛሬ ሦስት ወይ አራት ዓመት በደቡብ ክልል አንድ ታማኝ ሹም ማስቀመጥ ብቻ ይበቃ ነበር፡፡ ክልሉን ጠርንፎ ለመምራት አንድ ታማኝ ሰው በማስቀመጥ በእሱ ዙሪያ ታማኝ አስተዳደር ማዋቀር ይቻል ነበር፡፡ ክልሎቹ ቁጥራቸው ሲጨምር ግን መንግሥት ብዙ ታማኝ ካድሬና ብዙ ታማኝ መዋቅር መፍጠር ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ መንግሥት ክልሎች እንዲበዙ የማይፈልገው ምናልባትም በፖለቲካና በበጀት ጉዳዮች አሳሳቢነት ሊሆንም ይችላል፡፡ ሁለት ሕፃናትን የሚያስተምር ወላጅ የሦስተኛ ክፍሉን ታላቅ ልጅ የመዋዕለ ሕፃናት ተማሪ ወንድሙን እጅ ይዞ እንዲሄድ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ መንግሥትም የአስተዳደርና የበጀት ወጪዎችን ፍራቻ የተለያዩ ቡድኖችን ተቧድናችሁ ክልል ካልሆናችሁ ሲል ነው የምናየው፡፡ ማዕከላዊ መንግሥቱ እኔን በጀትም ሆነ ሌላ ወጪ አትጠይቁኝ፣ እዚያው ተቻቻሉ በሚል አንዱን በሌላው ላይ እየጫነ ክልል እንዲፈጠር መፈለጉ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ከመነሻው በነበረው ሕገ መንግሥታዊ ችግር ላይ የበቀለ ችግር ነው፡፡

ይህን መሰል ችግር መፈጠሩ ብዙም አይገርምም፡፡ ምክንያቱም እኔም በቦታው ብሆን የማደርገውና በከፊልም የነበርኩበት ነው፡፡ ዛሬ ያለው ከሁሉ በላይ ትልቅ ችግር ግን፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ አለመፈለግ ነው፡፡ ሕዝቡን ፀጥ አርጎ ለመግዛት ነው፡፡ ሕግ መጥቀስና ሕግ ተላለፍክ ማለት፣ ሕዝቡ ደግሞ ጥያቄ ሲያነሳና መብቴ ይከበር ሲል ሕጉ እንዲሻሻል ከማድረግ ይልቅ፣ ማምለጫ ምክንያቶች እያመጡ የመለጠፍ ችግር ነው ያለው፡፡ ይህም ቢሆን ለሕግ ታማኝ ካለመሆን ጋር ዞሮ የሚገናኝ ችግር ነው ብዬ ነው የምመለከተው፡፡

ሪፖርተር፡- የአንዳንድ ማኅበረሰቦች የክልልነት ጥያቄያቸው ሲመለስ ታይቷል፡፡ ሲዳማና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሆነዋል፡፡ ሌሎቹ የክልልነት ጥያቄ ያነሱ ግን ምን ስላላሟሉ ነው የክልልነት ጥያቄያቸው ያልተመለሰው?

መድኅን (ዶ/ር)፡- መንግሥት ለሕግ ታማኝ አይደለም ያልኩት ለዚህ ነው፡፡ ለሕግ ታማኝ ያልሆነ መንግሥትን ደግሞ የሚገዛው ጉልበት ነው፡፡ በተቃውሞ ጥያቄያቸውን ያነሱት ምላሽ አግኝተዋል፡፡ የሲዳማን ጉዳይ ማንሳት እንችላለን፡፡ መንግሥት ጥያቄውን ምላሽ ለመስጠት ፈልጎ ሳይሆን ተገዶ ነበር የመለሰው፡፡ ያውም መንግሥት ታገሱኝና በዚህ ቀን ልመልስ ብሎም ተቃውሞው ቀጥሎ ነበር፡፡ መንግሥት ለሕግ ታማኝ ቢሆን ኖሮ አመፅና ረብሻ እስኪፈጠር ምላሽ ለመስጠት ወደኋላ ማለት አልነበረበትም፡፡ ጉዳዩ እኮ እስከ አመፅና ረብሻ የሚወስድ አይደለም፡፡ በሕጉ የተቀመጡት ድንጋጌዎችም ለመተግበር አይከብዱም፡፡ በመሠረታዊነት ግን የክልልነት ጥያቄያቸው የተፈቀደላቸው ቡድኖች መብታቸው ነው፣ መፈቀድም የነበረበት ነው፡፡ ያልተፈቀደላቸውም ሊፈቀድላቸው ይገባል ነው የምለው፡፡ አንዱ ምን አሟልቶ ተፈቅዶለት? ሌላውስ ምን አጥቶ ሳይፈቀድለት ቀረ? ለተባለው ተገቢው ምላሽ መንግሥት ለሕጉ ታማኝ ስላልሆነ የሚል ነው፡፡

በአደባባይ ‹‹ለክልልነት ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል›› እየተባለ ውስጥ ለውስጥ ግን አንድ ላይ ተሰባስቦ በክልልነት መቆየትን እንዴት ማጠናከር እንደሚቻል ነበር ሲሠራ የቆየው፡፡ አንዱ ከወጣ ሌላው ይከተላል በሚል ፍራቻ ተከድኖ ነው የቆየው፡፡ ምሁራዊ ጥናት እየተባለ ብዙ ሲጎተት ቆየ፡፡ ሆኖም አመፁና ተቃውሞው ሲበዛ የሲዳማ ተመለሰ፡፡ ከሲዳማ ባልተናነሰ ለረዥም ዘመን ሲጠይቁ የኖሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎችም ተሰጣቸው፡፡ በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ከአስተዳደር አመቺነት ጋር በተያያዘ ብዙ ሲሰቃዩ ነው የኖሩት፡፡ ጥያቄያቸውም ረዥም ጊዜን ያስቆጠረ ነው፡፡ ሲዳማ ከወጣ በኋላ የቀሩትን አንድ ላይ ለማቆየት ሲሠራ እንደነበረው ሁሉ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያም ከወጣ በኋላ የቀሩትን በተለያዩ አደረጃጀቶች ጠርንፎ ለማቆየት መንግሥት የራሱን ሥራ ሲሠራ ነው የቆየው፡፡

በሁለት የክላስተር አደረጃጀት ሥር የቀሩትን ዞኖችና ወረዳዎች ሁለት ክልል ለማድረግም መንግሥት ዕቅድ አቀረበ፡፡ ደቡብ ኢትዮጵያ ብሎ ከወላይታ እስከ ደቡብ ኦሞ ባለው ክፍል ያሉ ማኅበረሰቦችን አንድ ላይ ለማድረግ ታሰበ፡፡ ከላይ በኩል ደግሞ የታቀደው የሸዋ ክላስተር ተብሎ ከሐዲያ እስከ ጉራጌ ያለውን አካባቢ በአንድ ለማካለል ነው፡፡ በዚህ መካከል ግን ጌዴኦ፣ ቡርጂና አማሮ የመሳሰሉት ነጠል ብለው የሚገኙ የብሔር አስተዳደሮች ምን ይሆናሉ የሚለው የሚያስገርም ነበር፡፡ በተለይም ጌዴኦ ወዴት ይሆናል? የሚለው ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ይህን የደቡብ ክልል ብሔረሰብ አስተዳደሮችን በክላስተር የማዋቀር ፕሮጀክትን ደግሞ በዋናነት ከላይ ሆነው የመሩት እነማን እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይህንንም ዕቅድ ቢሆን በብዙ ዞኖች ሕዝቡ ቢቃወምም፣ ነገር ግን አሁን ላይ ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ ወደ ሥራ ለማስገባት ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ በምርጫ ቦርድ ለጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዟል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ዕቅድ በጉራጌ ዞን ከባድ ተቃውሞ እንደገጠመው ይታወቃል፡፡ በሌሎች ዞኖችም ቅሬታዎች ሲስተጋቡ ይሰማል፡፡ በተጨባጭ በደቡብ አካባቢ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ዕቅዱን ወደ ተግባር ለማውረድ አመቺ ነው ወይ? መንግሥት ባሰበው መንገድ ዕቅዱን ያለ ችግር ተግባራዊ ለማድረግ የሚችልበት ዕድል አለ ወይ? እርስዎ የሚታዘቡት የሕዝቡ ስሜትና ሁኔታ ምን ይመስላል?

መድኅን (ዶ/ር)፡- ሕዝበ ውሳኔ መካሄዱ መዋቅሩን ውጤታማ አያደርገውም፡፡ መዋቅሩም ሆነ ሕዝበ ውሳኔው የሕዝብን ፍላጎት የተከተሉ ካልሆኑ በስተቀር ውጤታማ ናቸው ሊባል አይችልም፡፡ ሕዝበ ውሳኔው በምን ሁኔታ ነው የሚካሄደው? ምን ዓይነት አማራጮች ናቸው የሚቀርቡት? ለሕዝቡ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የተነገረው? ሕዝቡ ጥያቄውን ሲያነሳ ምክንያት የነበሩት ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ሕዝበ ውሳኔው ወይም መዋቅሩ እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎች ይመልሳሉ ወይስ አይመልሱም? የሚለው መገምገም መቻል አለበት፡፡ የመዋቅር ማለትም የክልልነት ጥያቄ የጠየቁት እኮ 11 ዞኖች ቢሆኑ ነው፣ ሁሉም አይደሉም፡፡ ለጥያቄያቸው ደግሞ ምክንያት ነበራቸው፡፡ አንደኛው ከእነሱ ጋር እኩል ወይም ተቀራራቢ የሕዝብ ቁጥር፣ የራሳቸው ቋንቋ፣ የአሠፋፈርና ባህል ኖሯቸው ክልልነት የተሰጣቸው ቡድኖች ስለነበሩ እኛም ይገባናል ብለው ነው፡፡ የሲዳማ የሕዝብ ብዛት ከወላይታ፣ ከጉራጌ፣ ከጋሞ፣ ከከምባታና ከሐዲያ ሕዝብ ብዛት አንፃር ያለው ልዩነት እጅግ ብዙ የሚባል አይደለም ተቀራራቢ ነው፡፡ ነገር ግን ሲዳማ ክልል ተሰጥቶት፣ ሌሎቹ የክልልነት ጥያቄያቸው ሊመለስ አልቻለም፡፡ ለዚህ ደግሞ አጥጋቢ ምክንያት እየቀረበም አይደለም፡፡

የክልልነት ጥያቄ ካነሱት ለምሳሌ ወላይታ ዞን ላይ ከተማውን ትተህ በገጠር ወረዳዎች ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ቤቶች እንዳሉ በግርድፉ ይገመታል፡፡ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ደግሞ እናትና አባትን ጨምሮ ስድስት ቤተሰብ ይኖራል ተብሎ ቢገመት፣ ይህን ቁጥር በቤቶች ቁጥር ልክ በማብዛት የወላይታ ሕዝብ ቁጥር ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን ይደርሳል የሚል አኃዛዊ ግምት ልታቀርብ ትችላለህ፡፡ ኢትዮጵያ ለሕዝብና ለቤቶች ቆጠራ ትኩረት ብትሰጥ ኖሮ፣ ከግምት ባለፈ ታች ወርዶ በመቁጠር የተጣራ አኃዝ ማቅረብ ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን የቀደሙ ቁጥሮችን፣ የዕድገት ትንበያዎችንና የአንዳንድ ተያያዥ መረጃዎችን ተመርኩዘን የምናገኘው ግምታዊ አኃዝ ከዚህ እንደማይራራቅ በግሌ እገምታለሁ፡፡ በዚህ መነሻነት ዘጠኝ ሚሊዮን ያልነው የወላይታ ሕዝብ ግምት ደግሞ እዚያው በዞኑ የሚኖር መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ በአንድ ዞን ውስጥ ዘጠኝ ሚሊዮን ወይም ተቀራራቢ ሕዝብ የሚኖርበት አካባቢ የት ነው የሚገኘው? አማራ ክልል ወይም ኦሮሚያ ክልል ዘጠኝ ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባቸው ዞኖች መኖራቸውን እጠራጠራለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ከሦስትና ከአራት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የያዙ ዞኖችን ማግኘት ይከብዳል፡፡

ስለዚህ እንደ ወላይታ ያሉ ዞኖች አስተዳደራዊም ሆነ ልማታዊ ምቹነት በሌለው መዋቅር ሥር ነው የኖሩት፡፡ በዚህ የተነሳም ብዙ የወላይታ ሕፃናት በድህነትና በችግር ከአካባቢያቸው ተሰደው አዲስ አበባን ጨምሮ በየከተሞቹ ለሥራ ይፈልሳሉ፡፡ በጉራጌም ሆነ በከምባታ ዞኖች በተመሳሳይ ሁኔታ ሥራ ፍላጋ የመፍለስ ዝንባሌ አለ፡፡ አንዱ ወደ አዲስ አበባ፣ ሌላው ደግሞ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረግ ካልሆነ በስተቀር፣ የክልልነት ጥያቄ ባነሱ ዞኖች አስተዳደራዊና ልማታዊ አመቺነት በሌለው መዋቅር አመጣሽ ድህነት ዜጎች ይፈናቀላሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ፣ በማላዊ፣ በሞዛምቢክና በኬንያ እስር ቤቶች የተረሱት ከእነዚህ ማኅበረሰቦች የወጡ ልጆች ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሲማስኑ የሚውሉትም ከእነዚሁ ማኅበረሰቦች ጉያ የወጡ ናቸው፡፡ አሁን ሕዝበ ውሳኔ ሊደረግ ቀጠሮ በተያዘላቸው ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች፣ ሕዝቡ ‹‹በአንድ ክልል ተሰባስቦ መኖርን ትፈልጋለህ›› ብቻ ተብሎ ሳይሆን፣ ራሱን ችሎ ክልል መሆን መፈለግና አለመፈለጉ አማራጭ ሆኖ ሊቀርብለት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ሕዝቡ በክላስተር መደራጀት መፈለግ አለመፈለጉ እንደተጠየቀ ይገልጻል፡፡ ታች ሕዝቡ ዘንድ በመውረድ መንግሥት የማኅበረሰቡን ፍላጎት ማስጠናቱንም ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

መድኅን (ዶ/ር)፡- የሕዝቡ ፍላጎት አልተፈተሸም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከጥቂት ዓመታት በፊት በክላስተር ለማደራጀት አስጠንተናል ያሉትን ነው ዛሬም ወደ መሬት እንዲወርድ እየሠሩ ያሉት፡፡ የሕዝቡ ፍላጎት ከሆነ ግን ለምሳሌ ከሁለት ዓመታት በፊት በወላይታ የወጣውን በክልል ልደራጅ የሚል ጥያቄ ያቀረበውን የሕዝብ ሠልፍ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ እኔ በግሌ ወላይታን ጨምሮ ደቡብ ኢትዮጵያ ተብለው በሚካለሉ ዞኖች ሊደረግ በታሰበው ሕዝበ ውሳኔ ግማሹ ሕዝብ እንኳ ወጥቶ ተሳታፊ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ያኔ ‹‹ክልል ይገባኛል›› ብሎ ድምፁን ለማሰማት የወጣው የወላይታ ሕዝብ እንደ አሁኑ አልተቀሰቀሰም፡፡ በራሱ ፍላጎት ነበር የጠየቀው፡፡ ይህን ዓይነት ስሜትና እንቅስቃሴ ነው ዛሬ በጉራጌ ዞን የምናየው፡፡ በወላይታ ያን ጊዜ ብዙ ግድያና እስራት ስለደረሰ ሕዝቡ በገጠመው በኃይል የመታፈን ዕጣ ዛሬ በፀጥታ ውስጥ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ሕዝበ ውሳኔ ለመካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት ጥያቄው ተመልሶ አይደለም፡፡ በጉራጌም ዛሬ የምናየውን እንቅስቃሴ አፍኖ መዋቅሩን ለመጫን ብዙ ጥረት ሲደረግ እየታዘብን እንገኛለን፡፡

ከምባታ ዞን ፀጥ ያለው ችግሩ ስለተፈታ ነው ወይ? ሐዲያ ላይ ያለው ወይም ጋሞ ጋር የሚሆነው ምንድነው? ብሎ መፈተሽም ተገቢነት አለው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ዝምታው የነገሠው፣ ችግር ሳይኖር ቀርቶ ወይም ጥያቄ ስለሌለ አይመስልም፡፡ በግሌ እንደምረዳው ለክላስተር ክልል ሕዝበ ውሳኔው ሲባል በእነዚህ አካባቢዎች በፖለቲካ ካድሬዎች በኩል የተለየ ጥርነፋና ቅስቀሳ አለ ተብሎ ይገመታል፡፡ ሕዝቡ በክላስተርም ሆነ በሌላ ጥርነፋ አልደራጅም ብሎ እንዲያማርር ከተገደደባቸው ምክንያቶች አንዱ የማዕከል ጥያቄ ነው፡፡ የክልልነት ጥያቄ እንዲነሳ ገፊ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ የክልሉ ማዕከል (ዋና መቀመጫ) የት ይሁን የሚለው አንዱና ዋና ጉዳይ ነው፡፡ በሐዋሳ ከተማ ለዘመናት ሀብታቸውን ያፈሰሱ ዞኖች በጉልበት ተነጥቀው ተባረዋል፡፡ ነገ ደግሞ ሌላው ላይ አፍስሰው ላለመባረራቸው ምን ዋስትና አላቸው? በአንዳንድ ዞኖች ይህንን በፖለቲካ በመቀመም ‹‹የክልል ማዕከል ልትሆኑ ነውና የክላስተር አደረጃጀቱን ተቀበሉት›› የሚል የካድሬ ቅስቀሳ መኖሩ በግልጽ ይታወቃል፡፡ ‹‹አርባ ምንጭ ማዕከል ልትሆን ነው›› የሚል፣ እንዲሁም ‹‹ሆሳዕና ማዕከል ልትሆን ነው›› የሚል ማባበያ በአንዳንድ ዞኖች ለክላስተር ክልል መዋቅሮቹ የፖለቲካ ድጋፍ ማግኛ ዘዴ እየሆነ ነው፡፡ ነገር ግን ይህም ቢሆን ጊዜያዊ መሸንገያ እንጂ፣ ችግሩን በዘላቂነት መፍቻ አይሆንም፡፡ ችግሩ አፍጦ ሲመጣ ውዝግቡ ማገርሸቱ አይቀርም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ እንዲህ ያሉ የአስተዳደርና የመዋቅር ጥያቄዎችን ለማዘግየት የሚያስገድድ አይደለም ወይ? በኢትዮጵያ አሁን ፋታ አያስፈልግም ወይ? በየቦታው የተነሱ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጥያቄዎችን ለመመለስ አሁን አመቺ ጊዜ ነው ይላሉ?

መድኅን (ዶ/ር)፡- የተጣደፈው መንግሥት እንጂ ሕዝቡ አይደለም፡፡ ይህ መንግሥታዊ ሽንገላ ነው፡፡ ጥያቄዎቹ በሰፊው በሚነሱበት ወቅት በኢትዮጵያ ጦርነት አልነበረም፡፡ አንድ ክልል ወጥቶ 55 ብሔሮች በጋራ መኖር ይችላሉ? ወይስ ሌላ አማራጭ ይቅረብ? ሲባል የነበረው ከግጭትና ከጦርነቱ በፊት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ግጭትና ጦርነት ውስጥ የገባችው ጥያቄዎቹ በስፋት መቅረብ ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡ መንግሥት መጀመሪያ ፋታ ስጡኝ ቢልም፣ ነገር ግን በቀውስና በጦርነት ውስጥም ሆኖ የሚፈልገውን ክልል መፍጠርና የራሱን መዋቅር ለመተግበር መንቀሳቀሱን በሰፊው ገፋበት፡፡ በየዞን ምክር ቤቶች ወርዶ የክላስተር አደረጃጀት ሕዝበ ውሳኔ ለማደራጀት የተጣደፈው መንግሥት እንጂ ሕዝብ አይደለም፡፡ መንግሥት ጊዜ ስላላገኘሁ ነው ታገሱኝ የሚለው ውሸት ነው፡፡ ሁለተኛው የሀብት ችግር አለ የሚለውም አሳማኝ አይደለም፡፡ አሁን ሊካሄድ ቀጠሮ በተያዘለት የክላስተር ክልል አደረጃጀት ሕዝበ ውሳኔ ራሱ ብዙ በጀት ይፈሳል፡፡ መንግሥት የሚያፈሰው ተጨማሪ ወጪ ሳይሆን፣ ለሕዝበ ውሳኔ በሚቀርበው አማራጭ ላይ ‹‹ለብቻህ ክልል መሆን ነው የምትፈልገው?›› ወይስ ‹‹ከሌሎች ጋር ተሰባስበህ ደቡብ ኢትዮጵያ በሚል መዋቅር ሥር መሆን?›› የሚል አማራጭ ለሕዝቡ እንዲቀርብና ሀቀኛ ፍላጎቱን ማወቅ ይቻላል፡፡ ተጨማሪ ወጪም ሆነ ሌላ ሎጂስቲክስ ሳያስፈልግ፣ የፖለቲካ ቅንነቱ መንግሥት ካለው የሕዝቡን ትክክለኛ ፍላጎት የሚለይ ጥያቄን ለሕዝበ ውሳኔው ማቅረብ ይችላል፡፡ ክላስተር አደረጃጀቱ መንግሥት የደገፈውና ሊያስፈጽም የተዘጋጀው ነው፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ ደግሞ በየዞን ምክር ቤቶች ፀድቆ ክልልነት እንፈልጋለንና ጥያቄያችንን አስፈጽሙልን ተብሎ ለቀደመው የደቡብ ክልል ምክር ቤት የቀረበው ጥያቄ ነው፡፡

ደቡብ ክልል ምክር ቤት ግን አቅመ ቢስ ስለነበር በወቅቱ የሲዳማን ብቻ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መርቶ የሌሎቹን ዞኖች ጥያቄ ተወው፡፡ ጉዳዩ ሲዘገይ በተወካዮች ምክር ቤትና በምርጫ ቦርድ በኩል፣ በይግባኝና በሌላም እየተባለ የብዙዎቹ ዞኖች ጥያቄ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ደርሷል፡፡ ክልልነት የጠየቁ ዞኖች ያቀረቡት ጥያቄ ከቀበሌ ጀምሮ ሁሉንም ቅደም ተከተል አልፎ የቀረበ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡም በየአደባባዩ እየወጣ ያስተጋባቸው ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የወላይታ ጉዳይን ብንመለከት ያ ሁሉ ሠልፍና ተቃውሞ የተደረገው በክላስተር ልደራጅ ለሚል ጥያቄ አይደለም፡፡ ብዙ ደምና መስዋዕትነት የተከፈለው ‹‹የራሳችን ክልል ይገባናል›› በሚል መነሻነት ነው፡፡ ሕዝቡ የጠየቀው በስሜ የሚጠራ ክልል ማግኘት እንደ ሕዝብ የሉዓላዊነት መገለጫዬ ነው፣ በቋንቋዬ ለመጠቀም፣ ባህሌን ለማሳደግ፣ ለመልማትና አመቺ አስተዳደር ለመፍጠር ክልል ያስፈልገኛል ብሎ ነው፡፡ ከሌሎች ጋር ተቀላቅሎ ለመደራጀት አልነበረም ጥያቄው የተነሳው፡፡

በሐዋሳ ከተማነት ታሪክ ውስጥ ወላይታ ሁሌም በሐዋሳ ይኖር ነበር፡፡ በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ሥር ወላይታ ስለነበረ፣ ሐዋሳን እንደ ራሱ ቆጥሮ ይኖር ነበር፡፡ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ዋና መቀመጫውን ወደ ሐዋሳ ከማዛወሩ በፊት ይርጋለም በነበረ ጊዜም ወላይታ እንደ አንድ የግዛቱ አካል የሆነ ሕዝብ በዚያም ይኖር ነበር፡፡ ሐዋሳ የደቡብ ክልል መዲና ስትባልም ወላይታ ነበር፡፡ አሁን ወላይታ እያለ ያለው ግን ‹‹ቆንጥርና ጫካ መንጥሬ ያለማሁት ከተማ የአንተ አይደለምና ውጣ ተብዬ ተባርሬያለሁና የራሴ ማዕከል ያስፈልገኛል ነው››፡፡ የመንግሥት አካላት ሳይከላከሉልኝ ሀብትና ንብረቴን፣ እንዲሁም ሕይወቴን ተነጥቄ ካለማሁት ከተማ ስለወጣሁ የራሴ ማዕከል ይሰጠኝ እንጂ፣ ሌላ ጋ ሄደህ አልማ ልባል አይገባም ነው ወላይታ እያለ ያለው፡፡ መንግሥት አይከስርምም፣ አይጎዳም፡፡ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደርግ ሕዝቡ በክላስተር መደራጀት ወይስ የራስህ ክልል እንዲኖርህ ተብሎ ይጠየቅ፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ መንግሥትን ለወጪ የሚዳርግ ሳይሆን ከኪሳራ የሚያድን ነው፡፡ ምናልባትም ይህን ማድረጉ ወደፊት ሊመጣ የሚችል ውድመትንም ሊያስቀር የሚችል ነው፡፡ ይህንን የሕዝቡን የክልልነት ጥያቄ ማዳፈን ወደፊት ግጭትና ቀውስ እንደሚፈጥር መገመት ቀላል ነው፡፡ ግጭትን አስቀድሞ መከላከል ደግሞ የተሻለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩ በምን ይፈታ? ምን ዓይነት የመፍትሔ አማራጭ ይበጃል?

መድኅን (ዶ/ር)፡- አማራጭ የሌለው አማራጭ አለ፡፡ እሱም የሕግ የበላይነትን መቀበል ነው፡፡ ሕገ መንግሥትን መከተል አለብህ፡፡ ይህም በመሠረታዊነት ችግሩን ይፈታል፡፡ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ የምትሆነው በሁለት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው ሕገ መንግሥቱን ጠብቀህና በዚያው በምትጠብቀው ሕገ መንግሥት ራስህን አስገዝተህ ስትሄድ ነው፡፡ ሁለተኛው በሕገ መንግሥቱ በኢትዮጵያ ያሉ ተጨባጭ ችግሮችን የማይፈቱ ከሆኑ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ነው፡፡ ሁለቱም ዞሮ ዞሮ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ የመሆኛ መንገዶች ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ተቀምጦ ሕገ መንግሥቱ በማይፈቅደው መንገድ ችግሮችን ልፍታ ብለህ ከተነሳህ፣ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ አይደለህም፡፡ ሕገ መንግሥቱ በራሱ አቅም ያሉ ተጨባጭ ችግሮችን መፍታት ካልቻለ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል መሥራት ያለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝነትን ማሳየት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን መጣስ የለብህም፡፡ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ችግሮቼን መፍታት አልቻለምና ተጨማሪ አቅም ልስጠው ብለህ ነው የምታሻሽለው፡፡ ይህን ማድረግ ለመንግሥት፣ ለሕግ የበላይነትና ለሕገ መንግሥት መገዛቱን የሚያሳይ ነው፡፡ የክላስተር አደረጃጀት ተብለው ከሚሰበሰቡ ወረዳዎችና ዞኖች ውስጥ አንዳንዶቹ ብዙ ቁጥር ያለው ሕዝብና ሰፊ ጂኦግራፊ ያላቸው፣ ዞን የነበሩ፣ ለብቻቸው ክልልነትን የጠየቁ ናቸው፡፡ ከሌሎች ጋር ተሰባስባችሁ ክልል ሁኑ ሲባል ግን በሚደራጀው አዲስ ክልል ውስጥም ከዞንነት የተለየ መዋቅር አያገኙም፡፡ ወረዳ የነበሩ ደግሞ በዚህ መዋቅር ወደ ዞንነት ከፍ ያለ አደረጃጀት ያግኙ እያልክ ነው፡፡ በክላስተር አደረጃጀት ሥር ይግቡ የተባሉ ወረዳዎችና ዞኖች ጥያቄዎቻቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ የሁሉንም ጥያቄ በየራሱ አግባብ እንደ አመጣጡ መፈታት ካልቻለ፣ አንድ ላይ በክላስተር በማሰባሰብ ብቻ ችግሮቻቸው እንዴት ይፈታል? ይህ ሁኔታስ ወደ ተወሳሰበ ችግር አያመራም ወይ? የሚለው መታየት አለበት፡፡

ትልልቆቹ ክልሎችም ቢሆኑ በነባሩ መዋቅር መቀጠል መፈለጋቸውና አለመፈለጋቸው ተጠይቆ አያውቅም፡፡ በአማራ ክልል ብዙ ጥያቄ አለ፡፡ በኦሮሚያ ክልልም ብዙ ጥያቄ አለ፡፡ ‹‹የዘገነም፣ ያልዘገነም እኩል ያዝናል›› እንደሚባለው ተረት፣ ብዙ የመዋቅር ጥያቄዎች በነባሮቹ ክልሎችም ቢሆን ሲጉላላ ነው የምናገኘው፡፡ ሁለት ሰዎች በጨለማ እየሄዱ ምንነቱ የማይለይ ጠጠር ያገኛሉ፡፡ አንዱ ተራምዶ ሲያልፍ ሌላው ግን ዘግኖ አለፈ፡፡ ብርሃን ላይ ሲደርሱ የዘገነው መዳፉን ቢመለከት ጠጠሩ ወርቅ ሆነ፡፡ ወይኔ ብዙ በዘገንኩ ብሎም አዘነ፡፡ ሌላው ደግሞ ባለመዝገኑ አዘነ፡፡ የዘገነም ያልዘገነም እኩል አዘነ የሚለው ሐሳብ ከዚህ የመጣ ሲሆን፣ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ አገር የሚያህል ክልል የያዙ ክልሎችን፣ እንዲሁም ወረዳ፣ ዞንና ክልል እንሁን እያሉ መዳፍ የምታህል መሬት ላይ የሚታገሉ ብሔሮችን ታሪክ የሚገልጽ ጥሩ ምሳሌ ይመስለኛል፡፡ ትልልቆቹ ክልሎች ‹‹ሁለት ወይም ሦስት ክልል እንሁን›› ቢሉ የሚፈቅድ አሠራር አለን ወይ? ሕጉ ቋጥሮ ነው ሁሉንም ያስቀራቸው፡፡

ኦሮሚያ ክልል ውስጥ አሁን የምናየው ቀውስ ክልሉ ይከፈል ከሚል ጥያቄ ጋር አለመያያዙን፣ ወይም በአማራ ክልል ያለው ችግር የራስ ክልል ከመመሥረት ጋር አለመገናኘቱን ያጣራ የለም፡፡ ችግሩ ቢፈጠርስ ለአስተዳደርና ለልማት አመቺነት በሚል የቀረበ ነውና ይፈታ ተብሎ በቀናነት ይታያል ወይ? የሚለውም መነሳት አለበት፡፡ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች በነባር ክልሎች ቢቀርቡ አማራን ለማፍረስና ኦሮሞን ለመበታተን በሚል ቁጣ የሚቀሰቅሱ ነው የሚመስሉት፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በደቡብ ክልሎች ሲፈጠር ግን እንደ ግዴታ መንግሥት የራሱን አማራጭ ለመጫን ሲነሳ ነው የምናየው፡፡ አሁንም ቢሆን አማራጭ የሌለው አማራጭ ሕጋችን፣ መንግሥትን ጨምሮ በእኩል መንገድና ሁኔታ ሁሉም ላይ ተፈጻሚ መሆን አለበት ነው፡፡ ሕግ በተጨባጭ የማይተረጎምና ችግሮችን የማይፈታ ከሆነ ለሕገ መንግሥት ታማኝነት አይኖርም፡፡

ሪፖርተር፡- ሥነ ማኅበረሰብ ጥናት ላይ የቆዩ ባለሙያ እንደ መሆንዎ፣ የማኅበረሰቡ ስሜትና አመለካከትን ለመገንዘብ ቅርብ ስለሆነ በዚህ ላይ የሕዝቡ ስሜት ምንድነው?

መድኅን (ዶ/ር)፡- የነበረው መዋቅር ሕዝቡ ከነበረበት ፈቅ እንዲል የሚያስችል አለመሆኑን ለረዥም ጊዜ በቅርበት ዓይቻለሁ፡፡ አንዳንዴም መዋቅሩ ወደ ባሰ ችግር ሕዝቡን ሲከተው ዓይቻለሁ፡፡ ግራ ቀኙን በበሰለ ሁኔታ መመልከት የሚችሉ የማኅበረሰቡ አዋቂዎች (ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና የማኅበረሰብ መሪዎች) ሕዝቡ በዚህ መንገድ ቢሄድ ያዋጣዋል ብለው የሚያቀርቡትን ሐሳብ ግን መንግሥት በጥርጣሬ ነው የሚመለከተው፡፡ መንግሥት ይህን የሚያደርገው ደግሞ ለማኅበረሰቡ አስቦ ሳይሆን፣ እኔ ከመረጥኩት አሠራርና አካሄድ ውጪ የሆነ ለአመራሬና ለአስተዳደሬ ችግር ይፈጥርብኛል በሚል ዕሳቤ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ማኅበረሰቡን ተጨባጭ ፍላጎት ለመፍታት መንግሥት እየተጋ አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር አፈታት ከዚህ ቀደም ግጭትን ነው ያመጣው፡፡ ደቡብ ክልልን ህልውናው እንዲያበቃ ያደረገው ይኼው ችግር በአግባቡ አለመፈታቱ ነው፡፡ ዛሬም በክላስተር አደረጃጀት ክልል ሁኑ እየተባሉ ያሉ አካባቢዎች የዞንና የክልልነት ጥያቄ በማንሳታቸው በብዙዎቹ አካባቢ ግጭት ተፈጥሮ ያውቃል፡፡ ያለፈውን ችግር ዛሬ እንዲደገም ለማድረግ መንቀሳቀስ ደግሞ ለማኅበረሰብ ከማሰብ የሚመነጭ አይመስለኝም፡፡

የወላይታን ጉዳይ ማሳያ ማድረግ ይቻላል፡፡ ወጋጎዳ የሚባለው እንቅስቃሴ ጊዜ ከፍተኛ ብጥብጥ የተፈጠረው አንድ ላይ በዞን ተሰባስበን አንኖርም በሚል ጥያቄ ነበር፡፡ በደቡብ ክልል ሥር ዞን ሆነው እንዲደራጁ ቀርቦ የነበረው አማራጭ ነበር በወቅቱ እነዚያን ማኅበረሰቦች ያጋጨው፡፡ ዛሬም ልክ እንደዚያው ሁሉ በክላስተር ክልል ሥር ተሰብስቦ መደራጀት ለመልማትም ሆነ ለአስተዳደር አመቺ አይደለም ብለው የሚጠይቁ ማኅበረሰቦች አሉ፡፡ እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ በግድ ተሰብስበው ክልል ካልሆኑ ማለት ነገ ተመሳሳይ ቀውስ ላለመፍጠሩ ምንም ዋስትና የለም፡፡ የተለያዩ ማኅበረሰቦች በስማቸው የሚጠራ ክልል አግኝተው ብዙዎችን በአንድ ላይ ሰብስቦ ጅምላ ስም መስጠቱ፣ በራሱ የሚፈጥረው ሥር የሰደደ የክብርና የማንነት ጥያቄ አለ፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የአስተዳደር መዋቅር በብዙ መንገዶች አላስፈላጊ ፉክክርና ግጭትን የሚፈጥር ዓይነት ነው፡፡ ደቡብ ምዕራብ ክልል ውስጥ የማዕከል ጥያቄ ብዙ ችግር ሲያስነሳ ዓይተናል፡፡ ከተሞች በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የሥልጣኔ፣ የባህልና የፖለቲካ ማዕከላት ናቸው፡፡ ይህ ጥያቄ በማኅበረሰቦች መካከል ጥርጣሬና ፉክክር ብሎም ግጭት ይፈጥራል፡፡ ከአንድ በላይ ማዕከላዊ ከተሞችን መፍጠር እንደ መፍትሔ አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን ይህ አዋጪና ችግር ፈቺ ነው ወይ የሚለው አልታሰበበትም፡፡ ለምሳሌ እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት ከተገደደችባቸው ምክንያቶች ውስጥ የማዕከልና የጋራ ቋንቋ ጥያቄ ወሳኙ ነበር፡፡ ከአንድ በላይ ቋንቋ ተብሎ አውሮፓዎችን ለማግባባት የሚወጣው የአስተርጓሚ ወጪ እንዳከሰራትና እንደከበዳት እንግሊዝ ተናግራለች፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች