በበቀለ ሹሜ
ካለፈው ሳምንት የሚቀጥለውን ጽሑፌን በሁለተኛው ምሳሌዬ እጀምራለሁ፡፡ ሁለተኛው ምሳሌዬ እኛኑ ኢትዮጵያውያንንና የኢትዮጵያን ሕይወት የሚመለከት ነው፡፡ በእኔ ነፍስ ያወቀ ዕድሜ ውስጥ አፄያዊው ባላባታዊ ሥርዓት፣ የደርግ ወታደራዊ ገናዥ ሥርዓት፣ በኋላም የተከተለው የኢሕአዴግ ጠርናፊ ሥርዓት ሕዝብን ምን ዓይነት ሕይወት ውስጥ እንዳዛከሩ ኖሬ አውቀዋለሁ፡፡ በሦስቱም ሥርዓቶች ውስጥ ሕይወት የየሥርዓቱን ምንነት ከእነ የመልኩና ውስጠ ወይራው በኑሮ እንድንቀምሰው አድርጋለች፡፡ ሕይወት አደራጅታ ሰልቃ እየሳቀችም፣ እያሽሟጠጠችም፣ እያዘነችም በእኛ ኑሮ አማካይነት ትጽፈው የነበረውን ስንክሳር የየጊዜው የፈጠራ ደራሲያን ነን ባዮች፣ ዘጋቢዎችና የታሪክ ሰዎች ማንጋጠጥና መመራመር ሳያሻቸው በራሳቸውና በሰዎች ኑሮ ውስጥ ሲሆን ያዩትን ጽፈውት ቢሆን ኖሮ፣ በየገጠሩና በየከተማው በአለቃና ምንዝር በሹምና በባለ ጉዳይ ግንኙነት የተካሄደው ራሱ በራሱ ድራማውን ያዋቀረ የክንውኖች ግትልትል፣ ሕይወት የምትባለው ወይዘሮ ምን ያህል የረዥምና የአጫጭር ታሪኮች ደራሲ፣ ምን ያህል አሽሙረኛና ኃያሲ፣ ምን ያህል የታሪክና የፖለቲካ ተንታኝ እንደሆነች በታየ ነበር፡፡ እኔ ባሳለፍኩት ዕድሜ ሕይወት ከጓዳ እስከ አደባባይ በተጠላለፈ ኑሮዬ የጻፈችውን በትኩስ በትኩስ መዝግቤው ቢሆን ኖሮ እንኳ፣ ስንት ነገር ለትውልድ ባቆየሁ ነበር፡፡ በጣም አጫጭር ማስታወሻ እየያዝኩ ያስቀመጥኳቸውን ብዙ ነገሮች ከረዥም ጊዜ በኋላ አውጥቼ ለመጻፍ ስሞክር፣ የተረዳሁት ነገር ልክ የሞተ ሰው እርጥበቱ በንኖ ሥጋው አልቆ የአጥንት ውልቅላቂ እንደሚተርፈው ዓይነት፣ በአዕምሮዬ ያስቀመጥኩዋቸው የነገሮች ትውስታዎች ከእነ ስሜታዊ አሻራዎቻቸውና ዝርዝራቸው መትነናቸውን ነበር፡፡
የየኑሮ ዋና ዋና ስንክሳሮቻችንን ዕለት በዕለት የመመዝገብ ልምድ በእኛ ትምህርት ቀመሶች ዘንድ ቢኖር ኖሮ (ለመመዝገብ ሲሞክር፣ ለነባራዊ ይዘትና ለስሜት ንካታችን መታመን አነሰም በዛ ግድ ነውና)፣ እውነታዊ የሆኑ ብዙ የጽሑፍ ቅርሶች ይኖሩን ነበር፡፡ የእኛ ትምህርት ቀመሶች ብዙዎቹ ቆይ ነገ እጽፈዋለሁ እያሉ ትልልቅ የሕይወት ታሪኮችን በትውስታቸው ታቅፈው እንደ እኔ መለኪያ ጨብጠው ማታ ማታ ሲያንጫልጡ፣ ከረንቦላ ሲወረውሩ ይኖሩና በመጨረሻ ትውስታቸው በቆረፈደ ርጋፊ ይቀራል፡፡ ወይም በአገራቸው እውነታ ላይ ላዩን እየተመላለሱ አንጋጠው ወይም ማዶ ማዶ እያዩ ከፈረንጅ አገር ኑሮና መጽሐፍ ከተቃረመ ነገራ ነገር ጋር ወዝወዝ የሚሉ ሆነው ያልፋሉ፡፡
ከቴዎድሮስ ጥረት አንስቶ በምኒልክና በተፈሪ መኮንን/አፄ ኃይሌ ሥላሴ ቅድመ ፋሺስት ጣሊያን ዘመን ድረስ በነበረው ጊዜ ውስጥ፣ በጃፓኖች መንገድ ኢትዮጵያን ለማሠልጠን የሚያስችል የነባራዊ እውነታ ምቹነቱም ሆነ በአገዛዙና በለውጥ ናፋቂ ትምህርት ቀመሶች ረገድ የመቀናበር ቁርጠኝነቱና አሥልቶ አቃጅነቱም ጎድሎ እንደነበር ቀደም ብለን ነካክተነዋል፡፡ ከ1953 ዓ.ም. የታኅሳስ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወደዚህ እያደገ ከመጣው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ተራማጅ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የመጣው ለውጠኝነትም፣ የኢትዮጵያን እውነታ በቅጡ አንብቦና አውቆ የሚጨበጥ መፍትሔ በመፈለግ ላይ ያተኮረ አልነበረም፡፡ ርዕዮተ ዓለሙም፣ ፖለቲካውም፣ ግቡም፣ የትግል ሥልቱም ‹‹እኔም አይቅርብኝ›› ባለ ጮርቃነት ከውጭ የተቀዳና ምኞታዊነት ያጠቃው ነበር፡፡ በአፄያዊ ባላባታዊ ሥርዓት ውስጥ በኖረ የባላገር (የአርሶ አደርና የአርብቶ አደር) አፈር ላይ ሶሻሊዝምን ሊገነባ ያቀደ ነበር፡፡ የ1960ዎቹ አብዮታዊያን እርስ በርስ ተባልተው ቢወድቁም፣ ደርግ በወታደራዊ ማርሽና ጡጫ የገነባው ‹‹ሶሻሊዝም›› ያው የእነሱኑ ቅዠት የሚወክል ነበር፡፡ ከኅብረ ብሔራዊ ተራማጅነት መሰባበር በኋላ በደርግ ዘመን በተወሰኑ አካባቢዎች የተፈለፈለውም ኢትዮጵያ ‹‹አገሮች ሊሆኑ የሚችሉ ብሔሮችን የያዘች ኢምፓየር›› የሚል የአተያይ ጀርባ ያለው በብሔረሰባዊ ሠፈር ላይ ያተኮረ ‹‹የሃርነት/የነፃነት ትግል›› ‹‹የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መነጠል›› የሚሉ ድምፆች የነበሩት የትጥቅ ትግልም፣ ያው አገዳ አስተሳሰቡ በውጭ ኮራጅነትና ምኞታዊነት የተሞላ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ማኅበረሰባዊ ዥንጉርጉርነት ውስጥ ያለውን የተወራረሰ ባህርይ ያልተገነዘበው ምኞታዊነቱ፣ ኢትዮጵያን ‹‹ቅኝ ገዥ››፣ ‹‹ብሔር›› የተባለውን ማኅበረሰብ ቅኝ ተገዥ አድርጎ ልብ ወለድ ታሪክ እስከ መፈልሰፍ ድረስ የተስፈነጠረ ጫፍ ነበረው፡፡ በብሪታኒያ ኢምፓየር ውስጥ ኢንግላንድ ካለው ቦታ ጋር የኢትዮጵያን ሸዋ ማስተያየት፣ ‹‹በኢምፓየሩ›› ውስጥ የአማራ ሕዝብን በሌሎች ሕዝቦች ብዝበዛና ጭቆና የተጠቀመ አድርጎ ማሰብም ‹‹በብሔር ነፃ አውጪዎች›› ዘንድ (ሕወሓት ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊትም) ፈዞ የቆየ ሐሰተኛ ‹‹ግንዛቤ›› ነበር፡፡
ከ1960ዎች እስከ ሕወሓት ኢሕአዴግ ድረስ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ተጭነውት የቆዩት አወቅን ባዮች ምን ያህል ከእውነታ ይልቅ ለምኞት የተገዙ አንጋጦ አሳቢዎችና ተጓዥዎች እንደነበሩ፣ የ1984 ዓ.ም. ቻርተርና የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ከእነ አሸናሸኑ ብቻውን በቂ ምስክር ነው፡፡ ከዴሞክራሲና ከሕዝብ እውነተኛ የድምፅ ወሳኝነት ውጪ በሕዝብ ላይ የተጫነ ስለመሆኑ ተብሎ ያለቀ ነውና እንተወው፡፡ ጥቂቶች የወሰኑበት ቢሆንም፣ በተለይም ሕወሓት ‹‹ኢትዮጵያን ገዝቶ ሲበቃው ትግራይን ይዞ ዘወር ለማለት እንዲያመች ኦነግን ታኮ አድርጎ የቀየሰው ቻርተርና ሕገ መንግሥት ነው›› የሚባለውን ይዘን፣ ሁለቱ ቡድኖች በየፊናቸው እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ የሚበጅ ውሳኔ ወስነው ነበር? ብለን ብንጠየቅ እንኳ መልሱ የዕብድ ውሳኔ የመሆኑን ሀቅ አይቀይረውም፡፡ በታሪክ ውስጥ ኦሮሞ በአራቱም ማዕዘን ተሠረጫጭቶ በማኅበራዊ መላላስ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተናጋሪ ሆኖ፣ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተናጋሪ የነበሩም ኦሮሚኛ ተናጋሪ እየሆኑ ከተገነባችው ‹‹ኦሮጵያ›› ልትባል ከምትችል ሰፊ አገሩ ኦሮሞን መበለት ኦሮሞን ከኦሮሟዊነት የመቁረጥ ዕብደት ነው፡፡ ኦሮሞ በታሪክ ውስጥ እስከ ሰሜን ድረስ ተሠረጫጭቶ የገነባትን አገር ደርሶ እንዲበትናት የሚያደርግ ምን ሎጂክ አለ? ሥልጣን ጓጉተው ያላገኙ አራጆች ካልተነጠልክ ሞተን እንገኛለን ስላሉ?
የኢትዮጵያ ግንባታና ሥልጣኔ ተጋሪ የሆነው የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት የታሪክ ቅርሱ ጋር ተጣልቶ ትግራይ ብቻ መሆንን የሚያስመርጠው ሎጂክ ምንድነው? የረባ ልማት ያላመጡለት የሕወሓት አኩራፊዎች መነጠልን ከኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣን የመውረዳቸው መበቀያ ስላደረጉት? ወይስ መሬት ተሰርቆለት የትግራይ ሕዝብ ቢነጠል በኢትዮጵያ ዓውድ ውስጥ ካለው በሰላም የመልማት ዕድል የተሻለ ዕድል ውስጥ ስለሚገባ? የባሰ አቅም ማጣት ውስጥ መግባት፣ በድርብ ወደብ አልባነት ውስጥ መታጠር፣ በመሬት ወሰድክብኝ ግጭትና ጦርነት ውስጥ መዳከር፣ ከዚህ ሁሉ ጋር የዓባይን ጥቅም ያለተጋሪ መቆጣጠር በሚሹ ኃይሎች አጣምዶና አዳቆ የማቆየት ፖለቲካ መጫወቻ መሆን ነው የሚገጥመው፡፡
ይህ ትግራይን በተመለከተ የደረደርነው ሁሉ ልክ ለመሆኑ፣ ከ2010 ዓ.ም. በኋላ የሆነው ሁሉ ምስክር ነው፡፡ ገና መነጠል ሲከጀል ከውስጥ እስከ ግብፅ ድረስ ምን ያህል ተንኮል፣ ጣልቃ ገብነትና ጠመንጃ እንዳነቃነቀ ማስተዋል አይከብድም፡፡ በገና የታየው የእነ ግብፅ መስለክለክ ሞክሮ ማየት የሚያሻው አይደለም፡፡ የዓባይና የቀይ ባህር የጥቅም ስስት ከፋፍሎ የማዳቀቅ መንጋጋውን ከፍቶ በሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲያፋሽክ እንዳየነው ሁሉ፣ ትንሽ ስንጥቅ ካገኘ መመለሻ የሌለውን ሰላም የለሽነትና ብተናን ለመፍጠር የማይተኛ ነው፡፡ የዚህንም አበሳ በሁለት ዓመታት የውጊያ ጊዜ ዓይተነዋል፡፡
ዓባይንና ቀይ ባህርን ለብቻ መቆጣጠር የሚሹ ኃይሎች ለምን መበታተናችንን መባላታችንን ይሻሉ? ለምን ኢትዮጵያ የምትባል ትልቅ አገር መሆናችንን ይፈሩታል? መበታተን፣ መባላታችን፣ መብታችንንና ጥቅማችንን ማስከበር የማንችልበት አዘቅት ውስጥ መግባት ስለሆነ፣ ትልቅ አገር መሆን ደግሞ በተቃራኒው ጠንካራ ሆኖና ታፍሮ ጥቅምንና መብትን የማስከበር አቅም ስለሚያስገኝ ነው፡፡ ዛሬ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚታገሉንን ጠላቶቻችንን እኛም ያለማወላወል የምንታገላቸው፣ መበታተን መጥፊያችን መሆኑን በመረዳት ላይ አንዳችም ጥርጣሬ ስለሌለን ነው፡፡ በዚህ የሁለት ወገን ትግል ውስጥ በእኛ ውስጥ ያሉ የብተናና የብጥስጣሽ ፖለቲካ ኃይሎች ምን ያህል ለኢትዮጵያ የጭቃ እሾህነት ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ ልብ ማለት አይከብድም፡፡ ይህንን የጥፋት ሚና ሳያውቁት የጀመሩትም ገና በፊት የብጥስጣሽ ብሔርተኛነትና ‹‹የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል›› የሚል መፈክር ተሸካሚዎች ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ መነጠል፣ መነጣጠል ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን የሚያስችል ሳይሆን ራስን የማጥፋት መንገድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ዕድል ተጨባጭነት የሚያገኘው ከሁሉ በፊት አንድ ላይ እንደ አገር በመቆም ነው፡፡ እንደ አገር መቆምም ብቻውን፣ አሁን ባለው ዓለማዊ አዝማሚያ፣ የትም አያደርስም፡፡ ቀደም ብለን እንዳልነው በማኅበረሰባዊ ማንነት የተያያዙት የኢትዮጵያ ድንበርተኛ አገሮች እንደ ቀጣና አንድ ላይ መቆም ግድ እያላቸው ይመስላል፡፡
ይህንን አጠቃላይ እውነታዊ ሥዕል ይዘን ወደ ቅዠታሙ ብሔርተኛ አስተሳሰባችንና ወደ ሕገ መንግሥትና ወደ ክልል አቀዳደዱ እንመለስ፡፡
ቻርተሩና ሕገ መንግሥቱ ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል እስከ መገንጠል›› በሚል ‹‹መብት›› መሠረት የፈጠራቸው ክልሎች የጊዜው ብሔርተኛ ልሂቃን አስተሳሰብና የኢትዮጵያ ኅብረተሰባዊ እውነታ እንዳልተግባቡ የሚያሳይ ምስክር ነው፡፡ አንደኛ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ክልል በሚል የየራስ አጥር ውስጥ መግባት የማይችል (ተበጭቆ፣ ተዛንቆ፣ ተሰባጥሮ በሌሎች ሥፍራዎች መገኘት አጠቃላይ የማኅበረሰቦች ባህርይ መሆኑ አግጦ ወጥቷል፡፡ ሁለተኛ በርከት ያለ ክምችት ባለበት እንኳ፣ በክልል መንግሥትነት የራስን በጀት ችሎ መተዳደር ለብዙዎች ብሔረሰቦች የማይቻል መሆኑ ታይቷል፡፡ ሦስተኛ ሕገ መንግሥቱ በሰጠው መብት 80 ምናምን የብሔረሰቦች ክልል ልፍጠር ቢባል የሚገኘው ውጤት ጠቅላላ የማደግ አቅም የሌላቸው የብጥስጣሾች ክምችት መሆኑ ወዲያውኑ የታየ ነው፡፡ አራተኛ የእከሌ የእከሌ ብሔራዊ ክልል የተሰኘው አጠራር ማኅበረሰቦችን አዋውጦ ብሔር የመፍጠር ምኞትን እንጂ፣ እውነታን የሚገልጽ አይደለም፡፡ አምስተኛ እያንዳንዱን ብሔረሰብ ክልላዊ መንግሥት ላድርግ የሚል ሙከራ የማይሠራ መሆኑ (ኅብረ ብሔራዊ ስብስብ የማይመለጥ እውነታ መሆኑ) በሕገ መንግሥቱ ቀያሾች ዘንድ ተጢኖና ተቀባይነት አግኝቶ ቢሆን ኖሮ፣ አስተዳደራዊ ሽንሻኖው ቢያንስ የመልማት አቅምንና ለአስተዳደር መመቸትን ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ በሆነ ነበር፡፡ ‹‹የደቡብ ሕዝቦች›› አንድ ላይ እንዲታጎሩ ተደርገው ‹‹ብሔራዊ ክልል›› የሚል አጠራር ባልተለጠፋባቸው ነበር፡፡ ስድስተኛ የአንድ ብሔረሰብ ሕዝብ ከአንድ በበለጠ ቦታ ተበጭቆ ተዛንቆ/ተሰባጥሮ መገኘት የኢትዮጵያ ዋና እውነታ መሆኑ ተቀባይነት አግኝቶ ከነበረም፣ በየብሔር የተበጣጠሰ አስተሳሰብን (ተቀዳሚ ወገናዊነትና ተቆርቋሪነት ለየብሔር/ብሔረሰብ ባይነትን) የአዕምሮ ማሟሻ አድርጎ ማባዛት ጥፋት መሆኑ በተጤነ ነበር፡፡ ክልሎች የአንድ ወይም የአንድ ሁለት ብሔረሰቦች ማንነትን በሚገልጽ ስም ባልተጠሩ፣ የተወሰኑ ማኅበረሰቦች ‹‹ባለቤት/ነባር›› ተብለው ሌሎች ባይተዋር ባልተደረጉ፣ ‹‹ባለቤት›› ከተባለ ብሔር/ብሔረሰብ የተቀናበረ ፓርቲ ገዥ፣ ሌሎቹ ተገዥ ባልሆኑ ነበር፡፡ ሰባተኛ በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ ማኅበረሰባዊ እውነታ ጋር በሚላተሙ (ኢትዮጵያዊ የምሆነው ስፈልግ ነው፣ ስፈልግ ክልል መሆን ስፈልግ ከኢትዮጵያ መለየት እችላለሁ በሚሉ) ቅዠታም ብሔርተኛ አስተሳሰቦች ሕገ መንግሥቱ ማኅበረሰቦችን ስለቃኘ አዕምሮን አቃዥቷል፣ አገራዊ አስተዋይነትን አደብዝዞ ክፍልፋይነትን አባዝቷል፡፡ አንጓላይና ተንጓላይ ፈጥሮ ማኅበረሰብ ገብ መሸካከር አራብቷል፡፡ ዛሬ ድረስ እንደ አበሳ የምንቆጥረው የዚህ ሁሉ መዘዝ እያዳፋን ነው፡፡ ከ1960ዎች የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የወጣ የጮርቃዎች ቡድን የጠመንጃ ትግል ሁሉ ሆኖና የመንግሥት ሥልጣንም ይዞ ጮርቃ እንደሆነ ባረጀ አስተሳሰቡ የአንድ ትውልድ ዕድሜ ያህል አዳክሮንም፣ በጥላቻ ወፍፎ ጨካኝ አራጅነትን በየዓይነቱ አድርሶብንም ‹‹ልሂቃኖቻችን›› ከዚህ ቅጣት ገና በአግባቡ አልተማሩም፡፡
እያልኩ ያለሁት ‹‹እኔ ብቻ ነኝ ልክ፣ የእኔን እንጂ ከእኔ በተቃራኒ ያሉ ልሂቃን የሚሉትን አትስሙ›› አይደለም፡፡ እስካሁን አንድ ሁለት እያልኩ የደረደርኩት ሁሉ እኔ ልክ ነው የምለውን እምነቴን አይደለም፡፡ ከእኔ አዕምሮ የፈለቀ አንድም አልተናገርኩም፡፡ ያተትኩት ሁሉ በኢትዮጵያ እውነታ ውስጥ ፍንትው ብሎ የወጣውን ‹‹የልሂቃን›› እንጭጭ ምኞታዊነትና የነባራዊ እውነታችንን መጣላት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የተሰቃየ ሕይወታችንን ነው መልሼ የተረኩላችሁ፡፡ የሕይወታችንን እንፋሎትና ወላፈን፣ ጣጣቴና ረመጥ ነው የዳሰስኩት፡፡ ሰላሳ ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ምድር የተላወሰው ብሔርተኛ አስተሳሰብ ዕይታን በማኅበረሰባዊ ሠፈር ጎነዳድሾ ሰዎችን ሲያበላልጥ፣ የእኔ ብሎ ሲያቀርብና ባይተዋር አድርጎ ሲገፋ ስለመኖሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስተምረውና የሚያስረዳው ይሻል? ‹‹ክልል›› የሚለው ስያሜ ‹‹አማራ››፣ ‹‹ኦሮሞ›› እና ‹‹ሐረሪ››፣ ወዘተ ከሚል መጠሪያው ጭምር ባለቤትና ባዕድ አድርጎ ዜጎችን የሚለይ ስለመሆኑ፣ ‹‹ጋምቤላ››፣ ‹‹ወሎ››፣ ‹‹ባሌ››፣ ወዘተ የሚለው አጠራር ግን ሰዎችን የማይለይ መሆኑን ለመረዳት የኢትዮጵያ ሕዝብ የእኔን ተንታኝነት ይሻል? አንዱ ‹‹ክልል›› ውስጥ ‹‹ባለቤት›› ተደርጎ የታየ ሰው ሌላ ‹‹ክልል›› ውስጥ መጤ ተደርጎ መታየት የሚገጥመው መሆኑን የማያውቅ ሰው በኢትዮጵያ ምድር አለ? የኢትዮጵያ የኑሮ ልምድ ከ1984 ዓ.ም. አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ያለፍንበት የአንጓላይና ተንጓላይ፣ የአፈናቃይና ተፈናቃይ የኑሮ ልምድ፣ የተያዘውን የፖለቲካ አስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ብልሽት ሲናገር አልኖረም? መታረም መስተካከል ያለበትን በመከራ ሲመክርና ሲያስተምር አልኖረም? በመጨረሻውስ የዝቅጠት ልምድ መውሰድ ያለብንን ትምህርትና ማስተካከያ፣ እሳትና ስለት በሚወድ ጭካኔ ዋ ችላ ብትሉ! እያለ አላስጠነቀቀንም? ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያን መራራ ልምድ ከእነምክሩ ማንበብ ከባድ ነው? በአስተሳሰብ፣ በፓርቲ አደራጃጀት፣ በአስተዳደር አሸናሸንና በሕገ መንግሥት ደረጃ መደረግ ያለባቸውን ማሻሻያዎች በጥቅሉ የልምድ እውነታችን የጻፈልን ስለመሆኑ ሐሰት የሚል አለ? የሕወሓት ጦረኞች ከጥምቅት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. አንስቶ ስንቴ በኢትዮጵያ አገርነት ላይ ወራራ ከፈቱ? ለዚህ ጥያቄ መልሱ አያመራምርም፡፡ ሒደቱን የተከታተለ ማንም ሰው ሦስቴ መሆኑን መናገር አያስቸግረውም፡፡ እውነታ ይህን ያህል ትምህርቱን ሁሉ አቅልላና ከቻችማ ሰጥታናለች፡፡ እኔና እኔን መሰሎች ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የምንለው ነገር እኛን ብቻ ስሙ ሳይሆን፣ ከእኛም ሆነ ከማንም አወቅሁ ባይ በላይ፣ ሰላሳ ዓመታት የኖራችሁበት የመከራ ልምድ የሚመክራችሁን አዳምጡ፣ ልምዳችሁ የሚመክራችሁን እመኑ ነው፡፡ የጋራ አገራዊ ምክክር ስታደርጉ፣ ሕገ መንግሥት ስታሻሽሉ ሁሉ ማሻሻያ አንቀጾቻችሁን ልምዳችሁ ከሰጣችሁ ምክር ምዘዙ ነው የምንለው፡፡
ጤነኛ የሚመስሉ ግን ጤነኛ ያልሆኑ፣ ያፈጀ ያረጀ አቋማቸውን መቀየር (ከልምድና ከእውነታ መማር) ሃይማኖትን እንደ መካድ የሆነባቸው፣ የእውነታ ምክር ወደ ህሊናቸው ተሰርቆ ገብቶ ሃይማኖታቸውን እንዳያስቀይራቸው በማንጋጠጥና በምኞታዊነት ዋሻ ውስጥ ራሳቸውን የዘጉ፣ ነጋ ጠባ የእውነታ ንፋስና ጨረር ወደ ዋሻቸው እንዳይገባ በቡትቶ ትልታይ ቀዳዳ ሲጠቀጥቁ (የብሔር ፓርቲን፣ የብሔር የራስን ዕድል ወሳኝነትን ሲያነበንቡ) ውለው የሚያድሩ ባህታዊ ብሔርተኞች አሉ፡፡ በዛሬው የ21ኛ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ እውነታ ውስጥ ሆነው ምኒልክንና ጎበናን ሲገላምጡና ሲነዘንዙ ውለው የሚያድሩ፣ በታሪክ የሚያውቋትን ከምኒሊክ ጥቅለላ በፊት የነበረችን ሚጢጢ የአካባቢ መንግሥት ዛሬ ለመትከል የሚቃዡ አሉ፡፡ በክስረት ማቅለል፣ ማላገጥና መሳቅ የማያልቅባት ታሪክ አታሳየው የላት፣ በአሜሪካ ውስጥ ራስ ፀጉራቸውንና ፂማቸውን አንዠርግገው ‹‹ምኒልክና ጎበና መጡባችሁ! ግደሉ እረዱ!›› የሚል ድቤ የሚመቱ፣ በጥላቻና በአረመኔያዊ በቀል የተደፈነ ልባቸው በአገረ ‹‹ኦሮጵያ›› ለውጥና የልማት ተዓምር መለኮሱን ከማስተዋል የከለከላቸው፣ እንዲያውም ‹‹ዋቄፈታ ያልሆነ ኦሮሞ ሙሉ ኦሮሞ አይደለም/የሰለሙና ክርስቲያን የሆኑ ኦሮሞነታቸው ጎዶሎ ነው›› በማለት ጉም ላይ ተቀምጠው የሚፈርዱ ጉዶችንም ጎልታልናለች፡፡ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ኦሮሚያ ውስጥ የተቀጣጠለው ልማት የማይታያቸው በዚያ ፈንታ የምኒልክ ዛር ወርዶ ኦሮሚያን ሲያስገብር (ጎበና ዳጬ ኦሮሚያን ሲያስገዛ) የሚታያቸው፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊነት ኢምፓየርነት ሆኖ የሚነበባቸው ሕወሓትና ሸኔ እንዳይሞቱ ሲፀልዩና አሜሪካ በማዕቀብ ዓብይን እንዲጥልላቸው ሲቁለጨለጩ የነበሩ ፖለቲከኞችን እዩ እያለች ታሪክ ስቃለች፡፡
ታሪክ ጉደኛዋ የሕወሓት የጦር አበጋዞች በአፋርና በአማራ ላይ ዘምተው የሠሩት ግፍ ደሙ ከእጆቻቸው ሳይደርቅ፣ ‹‹እኛ ከአማራና ከአፋር ጋር ጠላትነት የለንም ወገናችን ነው›› ብሎ እስከ ማለት ‹‹ብልጠታቸው›› ሲነሆልል አሳየችን፡፡ ከብተና አደጋ ይልቅ የዓብይን መንግሥት መጣል የበለጠባቸው ዱሽ ‹‹ፖለቲከኞችም›› ታይቶናል ከትግራይ ጦረኞች መሣሪያ አቀባብለው የመጡት አማራን ሊስሙ እንጂ ሊጎዱ አይደለም እያሉ ሲቀሰቅሱ አሳየችን፡፡ ንፁኃን በማንነታቸው በተደጋጋሚ መጠቃት አንገበገበን ያሉ አዲስ መጥ ብሔርተኞችም ነጉላቸው ወጥቶ በጥንታዊው ደምን በደም የመመለስ ዘይቤ ውስጥ ዘቅጠው የንፁኃንን ግድያ በንፁኃን ግድያ ‹‹ሊታገሉት›› ሲሞክሩ አሳየችን፡፡ እምዬ ታሪክ፣ በየትኛውም ሠፈር ተመፃዳቂ እንዳይኖር አድርጋ፣ የሁሉንም ሠፈር ብሔርተኛነት በተለያየ ጊዜ እያነጎለች በሰብዕና ላይ ጨካኝ ግፍ ሲሠራና በሰው ደም ሲታጠብ አሳየችን፡፡ የብሔርተኝነት መጨረሻ ፀፀት የማያውቅ አረመኔያዊነት ድረስ እንደሚሄድ፣ ‹‹ለሕዝቤ እታገላለሁ›› ባዮቹን ሰዎች መተፋታቸውን ያላመኑ ኮሚኮች እስኪመስሉ ልብሳቸውን አሶልቃ፣ ዋሽቶ ማምታታትና ነፍዞ መቀላመድ ልዩነቱ እስኪጠፋቸው ድረስ ሁለትና ሦስት ምላስ እያስቀባዠረች ከማዋረድ በላይ ታሪክ ልታግዘን አይጠበቅባትም፡፡ ከዚህ ሁሉ ልምድ ተነስቶ ራሳችንን በአግባቡ ማገዝ የእኛ ፈንታ ነው፡፡
እነሱና እኛ በመባባል ተከፋፍሎ ላለመናጨት ኅብረ ብሔራዊ አስተሳሰብ፣ ኅብረ ብሔራዊ የፓርቲ አደረጃጀት፣ ኅብረ ብሔራዊ የአስተዳደር ይዞታ ቅንብር፣ ኅብረ ብሔራዊ የፀጥታና የሲቪል ቢሮክራሲ ጥንቅር መድኃኒት መሆኑን የሰላሳ ዓመታት ያህል ኑሮ በመከራ ሲያስተምረን ኖሯል፡፡ ከዚህ የጋራ ትምህርት በተጨማሪ የጉራጌ ማኅበረሰብ እንደ አማራና ትግሬ ሁሉንም አከባቢ ቤቴ ብሎ በመላ ኢትዮጵያ ተበትኖና ተላልሶ የሚኖር ሆኖ ሳለ፣ ኅብረ ብሔራዊ አስተሳሰብን ተቀብለናል ብለው ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ሲዋቡ የነበሩ አወቅን ባዮች ጭምር የጉራጌ ሕዝብ ብቻውን ክልል መሆን አለበት የሚል ጠባብነትን የውሳኔ አቋም ሲያደርጉ ምን ይባላል! የጉራጌ ሕዝብ በመላ ኢትዮጵያ ተበትኖ መኖሩንና የብቻ ክልልነት መፈለግን እንዴት ሊያስታርቀው? እንዲህ ያለ ጓጓላ አስተሳሰብን ሕዝብ ጆሮ እንዳይሰጠው፣ ኢትዮጵያ በ30 ዓመታት አበሳዋ የሰጠችውን ምክር እንዳይለቅ ለማስታወስ ነው ደጋግመን የምንጮኸው! አወቅን ባይ የልሂቅ ጠባቦችማ ስህተትን ዓይቶ ከመታረም ይልቅ እነ እንትና ለብቻ ክልል ከሆኑ እኛስ ለምን ይቀርብናል ብሎ እስከ መከራከር ምንተፍረት ሲያጡ አስተውለናል፡፡ ስህተቶችን በሒደት ወደ ማረምና ወደ መቀነስ በመሄድ ፈንታ ሌሎች ከተሳሳቱ እኛስ ከእነሱ በምን አንሰን ነው የማንሳሳተው!? አንዳንዶቹ እንዲህ ያለውን ፉክክር የፍትሕ ጉዳይ አድርገውታል፡፡ ልብ መባል ያለበት፣ በአወቃቀራችንና በአስተሳሰባችን ውስጥ ገና ብዙ አንከኖች እንዳሉ፣ ከልምድ ለመማርና ከብሔርተኛ እስረኝነት ለመላቀቅ ገና መፍጨርጨር መጀመራችን መሆኑ ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ የአካባቢ አስተዳደሮች ቅንብር ልነጠል ባይ እንቅስቃሴን ማክሸፊያም መሆኑን ቀስመናል? የሥራ ከፈታን ብሔረ ብዙ የባለቤትነት ጥንቅርና ብዙ አካባቢን የማዳረስ/የማሳደግ አድማስ እንዲኖረው እስካላደረግን ድረስ፣ ‹‹መጤ/የእኛን አካባቢ እያለበ የከበረ›› የሚል አስተሳሰብን እንደማናመክነው ተረድተናል? የልማት አቅማቸው ተመጣጥኖ የፈካ ብዙ የአካባቢ አስተዳደሮችን የማጎልበት ዕቅድ፣ ከተወሰኑ ማስተካካያዎች ጋር መለስተኞቹን ይዞ በትልልቆቹ ውስጥ ያሉ ‹‹ዞኖች››ን ገምግሞ ወደ ዋና ዋና የልማት ማዕከልነት መቀየርን አይፈልግስ ይሆን?
ወጣም ወረደ ወደፊት የሚሻሻሉ ብዙ ብዙ ነገሮች እንደሚኖሩ፣ ልምድ የሰጠንን ትምህርት በአግባቡ እያነጠርን የኑሮ አደረጃጀታችንን እንደምናሻሻል ጥርጥር የለውም፡፡ እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር የሚያስደፍረን ዛሬ ጨርቶና ዕይታው አጥሮ የምናየው ‹‹ልሂቅነት›› እንደነበር አይቀጥልም፡፡ ዛሬ የሚርመሰመሰው ግልብልብና ካብ አይገቤ ሁሉ መራገፉ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጓት ከትናንት ተምረው ዛሬን ለማቃናት የሚሠሩ፣ በትናንት ቂምና ጥላቻ ሳይታሰሩ ‹‹የትኛውንም የኢትዮጵያ ቅርስ እንወቅ/ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪ እንሁን›› የሚሉ ወጣቶች በኢትዮጵያ ይፈላሉ፡፡ ሒደቱንም እያስተዋልነው ነው፡፡ ምንም ነገር ሳይሸብበው ግዕዝን የተማረውና ብዙ ቋንቋ የሚናገረው ሮባ ጴጥሮስ የአዲስቷ ኢትዮጵያ ወጣት ልሂቃን ተምሳሌት ነው፡፡
‹‹ኢትዮጵያውያን በክፉ ጊዜ አብሮ ተነባብሮ መሞትን እናውቅበታለን ችግራችን አብሮ መኖር ነው›› የተሰኘው የወጣቱ ሮባ አባባል አጭር ሆኖ ጆሮ የሚማርክ በመሆኑ እንዳለ እንዳይዋጥ ትንሽ ላቃናው፡፡ በልሂቃኖቻችን አካባቢ በተለይም ከ1960ዎች ወደ እዚህ አብሮ የመኖር ችግር አለ፡፡ በሕዝብ ረገድ ግን እጅግ የከፋ የበደል ሥርዓት በነበረበት ጊዜ እንኳ ተሳስቦ መኖር ተችሏል፡፡ ዛሬም ስንት መተራረድ በታየበት ጊዜ አብሮ ተላቅሶ መኖር መቻሉን እያሳየን ነው፡፡ ልጄን እንደ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ አንድም ቀን ከሁሉ ሰው ጋር ፍቅር ሁን ብዬ ሰብኬው አላውቅም፡፡ በእኩያ ባልንጀርነት ያልተወሰነና ለማመን የሚያቅት ፍቅርና መንሰፍሰፍ ያለበት፣ ከእኛ ከወላጆቹ እኩል ልጃችን የሚሉት ዘመዶች ከክርስቲያንም ከሙስሊምም አፍርቶ ዓይቻለሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የአምባጓሮ ሥፍራ በነበሩበት ጊዜ፣ የኮሌጅ ትምህርቱን የተከታተለው በአንድ የኦሮሚያ ከተማ ውስጥ በአንድ ኦሮሞ ቤተሰብ ውስጥ ‹‹እማ አንቺ›› ብሎ በከፊል እየኖረ ነበር፡፡ የሮባና የልጄን መሰል ወጣት ልሂቃን በኢትዮጵያ ውስጥ በተገማሸሩ ጊዜ ደግሞ መኗኗር የሚችለው ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን፣ ልሂቃኑም እርስ በርሳቸው ይሆናሉ፡፡ ያኔ ታዲያ ምን የማይሻሻልና የማይታረም የአሮጌ አመላከከት ግትቻ ይኖራል! ኅብራዊ ገጽታ ያለውና ከብዙ ጋር የተሳሳረ ወጣት የማነፅ እርሿዊ ሒደትም ተጀምሯል፡፡ እርሾው እስኪባዛም ትልቅ ክፍተት እንዲኖር መፍቀድ አይኖርብንም፡፡ የእነ ሮባ ዓይነቶች በግትር አስተሳሰብ ያልተሸበቡ ወጣቶች ባላቸው አቅም የሕዝብን የኑሮ ፍላጎትና የእውነታ ትምህርት በደንብ እያዳመጡ፣ በአሮጌ አመለካከትና ዓላማ ውስጥ ራሳቸውን የከረቸሙ ልሂቅ ተብዬዎች የሕዝቦችን የጋራ መግባባትና የአብሮ መኖር አቀነባበር እንዳይጎዱ መታገል ይገባቸዋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡