በደምሰው በንቲ
ቅድመ ታሪክ – ወ – ጣና
ጣና ሐይቅ በቀደሙት ጊዜያት ባህረ ጎጃም ይባል የነበረ ሲሆን፣ ቅዱሱ ሐይቅም በሚል ይታወቃል፡፡ ጣና ሐይቅ በጥንታዊ ቋንቋ (ግዕዝ) አገላለጽ ‹‹ጻና ሐይቅ›› ይባላል፡፡ ድንግል ማርያም በገዳሙ የነበራትን ቆይታ አጠናቃ ስትመለስ “ፀአና በደመና”፣ በደመና ጫናት የተባለው በጊዜ ብዛት ለአሁኑ የሐይቁ መጠሪያ ስም “ጣና” መሠረት ሆኖታል ነው የሚባለው።
በክርስቶስ ልደት ገደማ ስለግብፅ ብዙ ምርምር ያደረገው ስትራቦ፣ ዓባይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኝ ትልቅ ሐይቅ እንደሚነሳ ያውቅ ስለነበር የሐይቁን ስም “ሴቦ” ብሎታል፡፡ የሁለተኛው ዘመን የግብፅ መልክዓ ምድር ተመራማሪ ገላውዲዮስ ፕቶሎሚ ደግሞ “ኮሎ” ይለዋል፡፡
የጎጃም ስያሜ መነሻው ሃይማኖታዊ ሲሆን ይህም ከገነት ከሚፈስ ወንዝ ግዮን ጋር የተያያዘ ነበር። ይህ መጠሪያ የጎጃም ጥንታዊ መጠሪያ ነበር ይባላል። ግዮን ወይም ፈለገ ግዮን! ጎጃም ሰፊ አገር ሰፊ ግዛት ሲሆን ከጥንቱ ሜሮይ ድረስ በአሁኑ አጠራር እስከ ሱዳን ይደርስ ነበር። የጎዣም ልቡ ጣና፣ ዓባይ ደግሞ መቀነቷ ነው (1719 Mallet Map of the Source of the Nile, Ethiopia (Abyssinia) – Geographic’s – Nil-Mallet-1719.jpg)፡፡
የአቴናው ድራማ ጸሐፊ አስክለስ ‹‹መዳብ የተቀባው ሐይቅ የኢትዮጵያ ጌጥ›› ብሎታል፡፡ ባለቅኔው ሆሜርም ‹‹ከሌሎች የተለየና ጥርት ያለ የውኃ ባለቤት ነው፤›› ብሎ ጠርቶታል፡፡ ጣና ከኢትዮጵያ አንደኛና ትልቁ ሐይቅ ነው። 84 ከሎ ሜትር ረጅምና 66 ኪሎ ሜትር ሰፊ ነው። በአጠቃላይ 3,500 ካሬ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። ጣና በአጠቃላይ በውስጡ ከ37 በላይ ደሴቶች ሲኖሩት 27 ገዳማትን አቅፎ ይዟል። ገዳማት በ14ኛ ምዕት ዓመት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ባመነኮሷቸው ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› ተብለው በሚጠሩት ቅዱሳን አባቶች የተመሠረቱ ናቸው።
ጣና ሐይቅና የውኃ ላይ ትራንስፖርት ጅማሮ
በጣና ሐይቅ ላይ በእጅ ቀዘፋ የሚካሄድ የባህላዊ የውኃ መጓጓዥ አገልግሎት በታንኳ ከጥንት ጀምሮ ይዘወተር እንደነበር፡፡ ይሁንና ዘመናዊ የውኃ መጓጓዣ አገልግሎት ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. ከጣሊያን ወረራ ጋር ተያይዞ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በእነዚህ ዓመታት የጣሊያን ወራሪ ኃይል መቀመጫውን ጎንደር፣ መቆጣጠሪያ ጣቢያውን ደግሞ ጎርጎራ ላይ በማድረግ ጎጃምና ሌሎች ክፍሎችን በመቆጣጠር የወታደሮቹን ስንቅና ትጥቅ ለማጓጓዝ ጀልባ ይጠቀም እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡
የጣሊያን ወራሪ ኃይል ከኢትዮጵያ ተባርሮ ከወጣ በኋላ ጀልባዎችን ወደ ባህር አስጥሞና አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጎ ከመውጣቱ ጋር ተያይዞ፣ የጀልባ አገልግሎት ለተወሰኑ ጊዜያት ተቋርጦ ነበር፡፡ ይሁንና በ1940 ዓ.ም. አካባቢ ቡስኪ የተባለ ጣሊያናዊ ዜጋ ከመስመጥ በተረፉ ትንንሽና ከእንጨት በተሠሩ ሰውና ዕቃ በማጓጓዝ ዳግም የውኃ ትራንስፖርት ሥራውን ጀመረ፡፡ ቡስኪ ይህን ሥራ ሲጀመር ጎርጎራን ማዕከል በማድረግ ከጎርጎራ ባህር ዳር ምልልስ በማድረግ ነበር፡፡
ናቪጋ ጣና
በ1942 ዓ.ም. ጣሊያናዊያንና ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች ተሰባስበው የባህር ትራንስፖርት ድርጅት አቋቋሙ፡፡ ይህ ድርጅት ሲቋቋም ‹‹ናቪጋ ጣና›› የሚል ስያሜ ነበረው፡፡ ድርጅቱ ሥራውን እንዲሰፋ የሚያስችለው ዕድልና መረጃም ከእጁ ላይ ወደቀ፡፡ ይህም ጣሊያኖቹ ሲወጡ ካሰመጧቸው ጀልባዎች ሦስቱ ያሉበት መታወቁ ነበር፡፡ እነዚህ ሦስት ጀልባዎች አንጋራ ተክለሃማኖት ከሚባል አካባቢ 50 ሜትር ጥልቀት ካለው የሐይቁ ክፍል ውስጥ በድርጅቱና የመንግሥትም ዕገዛ ታክሎበት እንዲወጡ ተደረገ፡፡
የእነዚህ ሳንጆርጅ፣ ሳንታ ማርያና ማኒኩላ የተሰኙ ዘመናዊ ጀልባዎች መገኘት የባህር ትራንስፖርት ዘርፉን ይበልጥ አጠናከረው፡፡ የዚያ ዘመኗ ሳንጆርጅ አሁን ታጠቅ የሚል ስያሜ አግኝታለች፡፡ ሳንታ ማርያ ደግሞ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ዳኘው፣ አሁን ደግሞ ሊማሊሞ ትሰኛለች፡፡ ማኒኩላም ዞብልና አንድነት የሚሉ ሁለት ኢትዮጵያዊ ስያሜዎችን ተላብሳ የነበረ ሲሆን፣ አሁን በአንድነት ስያሜ ፀንታ እንደቆመች አለች፡፡
ናቪጋ ጣና የጥገና ማዕከሉን ጎርጎራ ዋና ጽሕፈት ቤቱን ባህር ዳር በማድረግ እስከ 1950 ዓ.ም. ብቸኛ የውኃ ትራንስፖር ድርጅት ሆኖ ቆየ፡፡ በ1950ዎቹ ናቪጋ ዘርፉን በብቸኝነት መምራት የሚያስችለውን ዕድል አጥቶ ከመንግሥት ጋር በአብሮነት መሥራት ጀመረ፡፡ በዚህ ሁናቴ የቆየውም እስከ 1967 ዓ.ም. ብቻ ነበር፡፡
በ1968 ዓ.ም. ናቪጋ ጣና በኢትዮጵያ የባህር ማመላለሻ ሥር ተዋቀረ፡፡ በ1970 ዓ.ም. የአትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሲቋቋም የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ሥራ ሙሉ በሙሉ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሥር ሆነ፡፡ ይህ አደረጃጀት በ1984 ዓ.ም. በአዋጅ እስከ ተዘጋበት ጊዜ ድረስ የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት የበላይ ተቆጣጣሪ ነበር፡፡ የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ለአንድ ዓመት ያህል ራሱን ችሎ ከተንቀሳቀሰ በኋላ፣ በ1985 ዓ.ም. የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ተረክቦ በክልሉ ትራንስፖርት ቢሮ ሥር አደረገው፡፡ ድርጅቱ ለሁለት ጊዜያት እንዲቋቋም ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ አሁን በክልሉ የመንግሥት ልማት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ሥር ተዋቅሮ እየሠራ ነበር፡፡
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የሰውና የዕቃ የውኃ ትራንስፖርት፣ የሆቴልና መዝናኛ፣ የጀልባ ግንባታና ጥገና፣ የወደብ ልማትና ኪራይ አገልግሎቶች ይገኙበታል፡፡ ድርጅቱ አሥር የሰውና የዕቃ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ጀልባዎች፣ አሥር ወደቦች፣ ዘጠኝ ሆቴልና የመዝናኛ ማዕከላት እንዲሁም አንድ ጀልባ መገንቢያና መጠገኛ ወርክሾፕ አሉት፡፡
ጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ወደ አዲስ ምዕራፍ
የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት ከኢትዮጵያ የባህርና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር በይፋ ተዋህደዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት (ኢባትሎአድ) በአገር ውስጥ የውኃ ትራንስፖርት ላይ መሰማራት ከተቋቋመበት ዓላማ አንዱ መሆኑ ለድርጅቱ ዕድል ቢሆንም፣ ለጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ደግሞ ከዕድልም በላይ ነው፡፡
ምክንያት
ጣና ከታሪካዊነቱ፣ ከሳቢነቱ፣ ከቅዱስነቱና ሊፈጥረው ይችል ከነበረው የቱሪዝም ዕድገትና ተጨማሪ የገቢና የሥራ ዕድል አንፃር ተገቢውን ድርሻ እያበረከተ አይደለም፡፡ ለአብነትም በጣና ሐይቅ ውስጥና አካባቢው ከፍተኛ የቱሪዝም ፍሰትና የንግድ እንቅስቃሴ አለ፡፡ ባህር ዳር ከተማ ለስብሰባ ማዕከልነትና ለመዝናኛነት ተመራጭ ከተማ እየሆነች መጥታለች፡፡ ጎርጎራ ወደብ በገበታ ለአገር ፕሮጀክት ለምቶ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑና የተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎችን የመጎብኘት ባህል ማደጉ፣ እንዲሁም በአካባቢው ከፍተኛ የግብርና ምርት በመኖሩ ምክንያት ድርጅቱ በዘርፉ ሊያበረክት ይገባ የነበረው አስተዋጽኦ እንደ ዋዛ የሚታለፍ አይደለም፡፡
በመሆኑም በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ የዘመነ የአመራር ዘዴን መከተል፣ በጣና ሐይቅ ላይ የአካባቢ ጥበቃ መርሆዎችን ጠብቆ በመሥራት የሐይቁን ደኅንነት እንዲጠበቅ ማድረግ፣ በጣና ሐይቅ ደሴቶቹ የሚገኙትን ቅርሶች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የጣና ሐይቅ አጠቃላይ የውኃ ጥልቀት ሁኔታ ቅኝት (Hydrographic Survey) እንዲደረግ፣ የጉዞ መስመር (Fair Way) እና የጉዞ ካርታ (Navigation Chart) እንዲዘጋጅ በማድረግ ደኅንነቱ የተጠበቀ የውኃ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
በውኃ ትራንስፖርት ላይ የዘመነ አገልግሎት በመስጠት የመንገደኛና የጎብኝዎች (Tourists) ፍሰት እንዲጨምር ማድረግ ያሻል፡፡ በአካባቢውም ሆነ በደንበኞች ላይ ሊመጣ የሚችል አደጋን የሚቀንሱ ሥራዎችን መሥራት፣ የቴክኖሎጂና የአሠራር ሥርዓት (System) እንዲኖረው ማድረግ፣ በጣና ሐይቅ ትራንሰፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ችግሮቹን ማቃለል እንደዚሁ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡ ዘመናዊ ጀልባዎችን በግዥም ሆነ በግንባታ በማሟላት የተሟላ የውኃ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዲሁም በተቻለ ፍጥነት ሊከናወን የሚገባው ተግባር ነው፡፡
ሁሉ አቀፍ የሆነ አገልግሎት በጣና ሐይቅ ላይ አገልግሎት በመስጠት በውስጡና በዙሪያው የሚገኙ ማኅበረሰቦችን ተጠቃሚ ማድረግ፣ የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት ጀልባ መገንቢያና መጠገኛ ማዕከልን (Workshop) ማሳደግ፣ ጀልባዎችን በመገንባት ለሌሎች በዘርፉ ለተሰማሩ ድርጅቶች ለገበያ ማቅረብ፣ የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት የጀልባ መዳረሻ ነባር ወደቦችን ማሻሻል፣ አዳዲስ ወደቦች መገንባትና በሁሉም ደሴቶች ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ፣ በውኃ ትራንስፖርት ላይ ለሚሠሩ ሠራተኞች ሥልጠና መስጠት፣ አዳዲስ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ሆቴልና ቱሪዝም እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ ከአዲሱና ጣና በአደራ ጭምር ከተረከበው የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሚጠበቁ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከተቋቋመበት ዓላማ አንዱ የአገር ውስጥ ትራንስፖርት መስጠት ነው፡፡ ለአሥር ዓመት በተቀመጠው ስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረት በጣና ሐይቅ ላይ የውኃ ትራንስፖርት ለመስጠት አገልግሎቱ ያሉበትን ውስንነቶች ለማሻሻልና ዕድሎችን ለመጠቀም የሚያስችል ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን መከተል ተገቢ ነው፡፡ ጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት ያለውን ዕምቅ ሀብትና ካፒታል ይዞ ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር ተዋህዷል፡፡ የዓለም አቀፍን ስምምነትን (IMO Recommendation) እና የአገሪቱን የማሪታይም ሕግ ተከትሎ ለመሥራት በፍጹም ተነሳሽነትና ዝግጁነት ላይ ነው፡፡
ከብሉ ኢኮኖሚ ዕምቅ የገበያ ዕድሎች አንፃር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንዲሁም፣ የአካባቢ ጥበቃ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በጥናቶች የታየ በመሆኑ ድርጅቱ በተለማቸው የትኩረት ከባቢዎች ላይ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት ይቻል ዘንድ የክልሉ መንግሥት ሙሉ ድጋፍ እጅጉኑ አስፈላጊ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በአዲስ ምዕራፍ ኢትዮ ፌሪስ ጣና በሚል ስያሜ የተቋቋመው ድርጅት አዲስ ተስፋና አዳዲስ ዕድሎችንና ድሎችን ይዞ እየመጣ ነው፡፡
ለዚህ ማሳያው ደግሞ ጣና ነሽ ሁለት እና መደመር የተሰኙ ዘመናዊ የሕዝብ ማመላለሻ ጀልባዎች ግዥ እየተፈጸመ መሆኑ ነው፡፡ የጣና ሚልኪ ለሌሎችም ሐይቆችና ጀልባዎች ዕድልንና ተስፋን ይዞ ይመጣል፣ አሜን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢባትሎአድ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው kerawud2016@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡