Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኳታር ዓለም ዋንጫና ፖለቲካዊ አንድምታው

የኳታር ዓለም ዋንጫና ፖለቲካዊ አንድምታው

ቀን:

በውዝግቦች ታጅቦ የጀመረው የኳታር ዓለም ዋንጫ ወደ ጥሎ ማለፉ የሚገቡ ብሔራዊ ቡድኖች እየተለዩ ነው፡፡ ድራማዊ ክስተቶችን እያስተናገደ የሚገኘው የዘንድሮ ዓለም ዋንጫ፣ ለዋንጫ የታጩ ቡድኖች ወደ አገራቸው የተሰናበቱበትን ትዕይንት አስመልክቷል፡፡ በአዘጋጇ ኳታር ላይ ሲያርፍ የነበረ የምዕራባውያን የሚዲያ ጫና ጋብ ብሎ በፖለቲካዊ ክስተቶች ታጅቦ ቀጥሏል፡፡

ኳታር በስታዲየም እንዲሁም በመሠረተ ልማት ግንባታ ወቅት ሠራተኞችን በድላለች፣ ሰብዓዊ መብትንም ጥሳለች የሚሉ ክሶች ሲቀርቡ ቢከርሙም፣ ከአንድ ሳምንታት በላይ መዝለቅ አልቻሉም፡፡ ከሳምንታት ቀደም ብሎ የአውሮፓ ፓርላማ፣ ስታዲየሞችና መሠረተ ልማቶች በሚገነቡበት ጊዜ አደጋ ለደረሰባቸው ስደተኞች ካሳ እንዲከፈል ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡ ጥሪው የቀረበው የዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የሠራተኞቹ ቤተሰቦች፣ የእግር ኳስ ማኅበራትና የፖለቲካ መሪዎች ጫና ማድረጋቸውን ተከትሎ ነበር፡፡

ሆኖም በመሠረተ ልማት ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት አብዛኞቹ ሠራተኞች፣ «በተፈጥሮ ምክንያት ነው የሞቱት፤›› የሚል፣ ምላሽ በመስጠት እንግዶቿን ማስተናገዷን ቀጥላለች፡፡ የዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ አስቀድሞ ጫናው እያየለበት የመጣው ፊፋ ለብሔራዊ ቡድኖቹ ‹‹እግር ኳስ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጉ›› የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ደብዳቤ ለመላክ ተገዶ ነበር፡፡

የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በመክፈቻው ዋዜማ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኛ ሠራተኞች የአገሪቱን አዳዲስ አስደናቂ ስታዲየሞችን ግንባታ እንዲሳካ በማድረግ ሒደት ውስጥ ትልቅ አሻራ ማኖራቸውን አስታውሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፕሬዚዳንቱ ለአንድ ሰዓት የዘለቀ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ በተለይ ኳታር አሁን ትችት ከሚሰነዘሩ የአውሮፓ አገሮች በበለጠ፣ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሏን መስክረዋል፡፡

በአንፃሩ ከሳምንት በላይ ያልዘለቀው የምዕራባውያን ነቀፌታ ተረስቶ፣ ዓለም ዋንጫው ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ የሚራመድበት መድረክ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ኳታር ሰብዓዊ መብትን ጥሳለች ብለው ከተቃወሙ አገሮች መካከል አንዷ ጀርመን ነበረች፡፡ በዚህም የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የምድቡን የመጀመሪያ ጨዋታ ከጃፓን ለማድረግ ወደ ስታዲየም ከገባ በኋላ፣ ተጫዋቾቹ አፋቸውን ከድነው በመያዝ አዘጋጇን አገር ተቃውመው ነበር፡፡

በተቃራኒው ጀርመን ‹‹ዓይኔን ግንባር ያድርገው›› በሚመስል ዓይነት ትናንት ሰብዓዊ መብት ጥሳለች ብላ ስትከሳት ከከረመችው ኳታር ጋር ለ15 ዓመታት የሚዘልቅ ውል ማሰሯ በርካቶችን ያስደመመ ክስተት ሆኗል፡፡ ስምምነቱ ሌላዋ ኳታርን ስትተች የነበረችው አሜሪካ ተጠቃሚ ማድረጉ አግራሞትን ጭሯል፡፡

በሌላ በኩል በኳታር ዓለም ዋንጫ እግር ኳስ ጨዋታ ድራማዊ ትዕይንቶች በዘለለ፣ በስታዲየሞች ላይ የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ መልዕክቶች የበርካቶችን ቀልብ ገዝተዋል፡፡ በተለይ አይጥና ድመት የሆኑት አሜሪካና ኢራን የዓለም ዋንጫ ጨዋታ አንደኛው ጉዳይ ነበር፡፡ 

በኳታር የኢራን ብሔራዊ ቡድንን ለመደገፍ የተገኙት ኢራናውያን በአገራቸው እየተከናወነ ለሚገኘው ሕዝባዊ ተቃውሞ ድምፅ ከመፈለጋቸውም በዘለለ፣ ብሔራዊ ቡድኑም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርግ ይፈልጉ ነበር፡፡ ብሔራዊ ቡድኑም የምድብ ጨዋታውን ለማከናወን ወደ ስታዲየም በገባበት ወቅት፣ ብሔራዊ መዝሙር ከመዘመር በመቆጠብ፣ በአገሩ ላለው ፖለቲካዊ ተቃውሞ ድምፅ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ተመልካቹም ቢሆን፣ ‹‹በኢራን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይቁም!›› እና ‹‹ሴቶች ስታዲየም ገብተው ኳስ እንዲመለከቱ ይፈቀድ!›› የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ድምፃቸውን ሲያሰሙ ተስተውለዋል፡፡

በፖለቲካ ጠላትነታቸው የሚታወቁት አሜሪካና ኢራን ጨዋታ ከማድረጋቸው አስቀድሞ፣ የአሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢራን ኢስላሚክ ሪፐብሊክ ዓርማ የሌለውን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለአጭር ጊዜ በመለጠፍ በርካቶችን አስቆጥቶ ነበር፡፡ በዚህም ‹‹ድርጊቱ የተደረገው በኢራን ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎችን ለመደገፍ ታስቦ ነው፤›› የሚል ምላሽ ከአሜሪካ በኩል ቀርቧል፡፡ የቴህራን መንግሥት በበኩሉ፣ የአገሪቱ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ መለያ የነበረውን የፈጣሪያቸውን ምልክት አሜሪካ ማንሳቷን ኮንነዋል፡፡

በሌላ በኩል የኳታር ዓለም ዋንጫ በሌሎች የፖለቲካ ጉዳዮች መወጠሩ አልቀረም፡፡ በተለይ የ2018 ዓለም ዋንጫ ማሰናዳት የቻለችው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በገጠመችው ጦርነት ከዘንድሮ ዓለም ዋንጫ መታገዷ፣ በአሜሪካ የጅምላ ተኩስ መበራከቱና በቻይና ድንገተኛ የተቃውሞ ሠልፎች መከሰታቸው ከዘንድሮ ዓለም ዋንጫ ጋር በተዘዋዋሪም ቢሆን መያያዙ እንዳልቀረ የሚናገሩ አሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር በኳታር ዓለም ዋንጫ ብሔራዊ ቡድኖቻቸው ባይካፈሉም፣ የእስራኤልና የፍልስጤም ግጭት የቀጣናው ፖለቲካዊ ስሜቶች ጎልተው መውጣታቸው ተነግሯል፡፡

በኳታር የፍልስጤም ሰንደቅ ዓላማና የፍልስጤም ደጋፊዎች ጎልተው መታየታቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ በአንፃሩ የእስራኤል ሚዲያዎችና ደጋፊዎች በዓረቡ ዓለም ተቀባይነት ስለሌላቸው ትኩረት መነፈጋቸው ተወስቷል፡፡

በሌላው የዘንድሮ ዓለም ዋንጫ አነጋጋሪ ጉዳይ፣ በምድብ አምስት የተደለደሉት የሰሜን አፍሪካዋ ሞሮኮና የአውሮፓዋ ቤልጂየም ጉዳይ ነበር፡፡ ሞሮኮ ከፍተኛ ደረጃ የተቀመጠችውን ቤልጂየም ማሸነፏን ተከትሎ፣ በቤልጂየም ከተሞችና በኔዘርላንድስ ውስጥ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር፡፡ በተለይ በቤልጀየም ኑሯቸውን ያደረጉ የሰሜን አፍሪካ ስደተኞች ማኅበረሰቦች ደስታቸውን መግለጻቸው ሁከቱን ማባባሱ ተነግሯል፡፡

በርካታ ንብረት በወደመበት ሁከት፣ ‹‹ሁከቱን የፈጠሩት ደጋፊዎች ሳይሆኑ፣ ሁከት ፈጣሪዎች ናቸው፤›› ሲል የአገሪቱ መንግሥት ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በኳታር ጎዳናዎች ከተለያዩ የዓለም አገሮች የዓለም ዋንጫውን ለመታደም የመጡ ተመልካቾች፣ በየአገራቸው የሚስተዋለውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ  ሲቃወሙ ተስተውለዋል፡፡ ከዚያም ባሻገር የተለያዩ መልዕክቶችን ያነገቡ መፈክሮችን ይዘው ወደ ሜዳ ዘለው በመግባት መልዕክታቸውን ያስተላለፉ በርካቶች ነበሩ፡፡

ሆኖም ኳታር፣ ‹‹ውሾቹም ይጮሃሉ፣ ግመሎችም ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፤›› በሚመስል መልኩ እንግዶቿን እያስተናገደች ቀጥላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...