ዋሊያዎቹ ከፊል ዝግጅታቸውን በሞሮኮ ያደርጋሉ
አልጄሪያ በምታዘጋጀው የአፍሪካ አገሮች ሻምፒዮና (ቻን) ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ቅድመ ዝግጅት አሠልጣኙ ውበቱ አባተ ለ42 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አሠልጣኙ በፕሪሚየር ሊግ ላይ እየተጫወቱ ከሚገኙትና ከመረጧቸው 42 ተጫዋቾች መካከል 28 ተጫዋቾች እንደሚለዩ ገልጸዋል፡፡
በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ደቡብ ሱዳንን 1 ለ 0፣ እንዲሁም የሩዋንዳ አቻውን በአጠቃላይ ውጤት 2 ለ 1 የረታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ሻምፒዮናው ማለፍ ችሏል፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር እስከ ታኅሣሥ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. እየተካሄደ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን፣ ከታኅሣሥ 18 ቀን ጀምሮ ብሔራዊ ቡድኑ ቅድመ ዝግጅቱን እንደሚጀመር ታውቋል፡፡
በአገር ውስጥ ሊግ ላይ የሚሳተፉ ተጫዋቾችን ብቻ የሚያሳትፈው ውድድሩ፣ ከጥር 5 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በአልጄሪያ ይከናወናል፡፡ ዋሊያዎቹ በምድብ አንድ ከአስተናጋጇ አልጄሪያ፣ ሞዛምቢክና ሊቢያ ጋር ተደልድለዋል፡፡
ብሔራዊው ቡድኑ የአገር ውስጥ ዝግጅቱን ካገባደደ በኋላ፣ በሞሮኮ በከፊል ዝግጅቱን እንደሚያደርግ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከተቻለ የአቋም መለኪያ ጨዋታን ሊያደርግ እንደሚችል ተሰምቷል፡፡
በአልጄሪያ አራት ከተሞች ላይ የሚከናወነው ሰባተኛው የቻን ውድድር 18 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ፡፡ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የ2020 እና 2021 ዓ.ም. ውድድሮች ሳይከናወኑ መቅረታቸው ይታወሳል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2009 የጀመረው ሻምፒዮናው ሞሮኮና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሁለት፣ ሁለት ጊዜ ዋንጫ በማንሳት ስኬታማ መሆን የቻሉ ብሔራዊ ቡድኖች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በ2014 በደቡብ አፍሪካ በተሰናዳውና በ2016 በሩዋንዳ የተዘጋጀውን ጨምሮ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ መሳተፍ ችላለች፡፡
ዋሊያዎቹ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ከሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደርጋሉ፡፡