Saturday, December 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት ምንጭ፣ በዚህ ዘመን ያ ምንጭ የደፈረሰበት ምክንያት መታወቅ ይኖርበታል፡፡ አንዳች ጉዳይ ሲያጋጥም እስኪ እንነጋገርበት የሚለው የአስተዋዮች ባህል ጠፍቶ፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል መንቻካነት የተንሰራፋበት ምክንያት መዳሰስ ይኖርበታል፡፡ ከራስ በፊት አገርንና ሕዝብን ማስቀደምና ለዚህም ሲባል እስከ መስዋዕትነት መክፈል ድረስ የተከናወነባት ድንቅ አገር፣ በዚህ ዘመን ለምን አይረቤ ነገሮች በዝተው ትውልዱን ደም ያቃቡታል የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ማነጋገር አለበት፡፡ ማስተዋል የጎደላቸው፣ ከራሳቸውና ከተቧደኑበት ጎራ ፍላጎት በላይ አገር መኖሯን መገንዘብ የማይፈልጉ የበዙትስ ለምን ይሆን ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ እጅና እግሯን ታስራ መቀጠል ስለማትችል፣ ለዘመኑ ትውልድ ሞጋች ጥያቄዎች ቀርበው በቅደም ተከተል መነጋገር አለበት፡፡ ጥራዝ ነጠቅነት ለአገር ስለማይጠቅም ጥልቅና ሰፋ ያለ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ ምሁራንና ልሂቃን ከጎራ ሽኩቻ ወጥተው ለአገር ህልውና፣ ሰላምና ዘላቂ ዕድገት ሲሉ በቅንነት ይነጋገሩ፡፡ ከአስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይልቅ ችግሩ ያለው እነሱ ዘንድ ነውና፡፡

ከጥንት ጀምረው ለአገራቸው ዕድገት በየመስኩ የለፉ፣ ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ለማስከበር መስዋዕትነት የከፈሉና በማንኛውም የአየር ንብረት ሆነ የመሬት ገጽ ላይ ተንቀሳቅሰው የተሰጣቸውን አደራ በብቃት የተወጡ ኢትዮጵያውያን ገድል ሲታወስ፣ የዚህ ዘመን ትውልድ በአንክሮ ማስተዋል ይኖርበታል፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት ስማቸው በክብር የሚነሳ ኢትዮጵያውያን ምንም ዓይነት ዘመናዊ ትምህርት ባይኖራቸውም ራሳቸውን በሥነ ምግባር የገሩ፣ ጨዋዎች፣ ኩሩዎችና አስተዋዮች እንደነበሩ ታሪካቸው ይመሰክራል፡፡ የብሔር ማንነትና የእምነት ልዩነት ሳይበግራቸው እርስ በርስ ተከባብረውና አገራቸውን በጋራ ጠብቀው ያለፉት፣ በዘመናዊ ትምህርት በመታገዝ ባገኙት ዕውቀት ሳይሆን በተፈጥሮ በተጎናፀፉት አርቆ አሳቢነት እንደነበረ ማንም አይስተውም፡፡ ችግሮች ሲገጥሟቸው ወደ ዘለፋና የኃይል ድርጊት ውስጥ ከመግባት ይልቅ፣ ለዘመናት ባዳበሯቸው የግጭት አፈታት ሥልቶችና በሽምግልና በመዳኘት ለውጭ ጠላት ቀዳዳ ሳይከፍቱ ኖረዋል፡፡ እነዚህ ያልተማሩ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ከአውሮፓ ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር በመጋፈጥ፣ ለአፍሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት በመሆን ደማቅ ታሪክ ጽፈዋል፡፡

በዚህ ዘመን ዘመናዊውን ትምህርት የቀመሰው ትውልድ ራሱን ከቀድሞዎቹ ጋር ሲያነፃፅር፣ ብዙ የሚያፍርባቸው የታሪክ ምዕራፎች እንዳሉት ማንም ሊክድ አይችልም፡፡ በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ በተለያዩ ዕርከኖች ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ዲግሪዎችን የተጎናፀፈው ወገን፣ በኢትዮጵያ ያለፉት ሃምሳ ዓመታት ጉዞ ውስጥ የነበረውን ሚና ሲያሰላስል በአዕምሮው ውስጥ ብዙ ነገሮች ይመላለሳሉ፡፡ አገሩን ከባላባታዊ ሥርዓት አላቆ በሶሻሊዝም አማካይነት የእኩልነት ምድር ለማድረግ ታግያለሁ ከሚለው፣ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት አስከብሬ አዲስ ታሪክ እጽፋለሁ እስካለው ድረስ፣ እንዲሁም ከሁለቱም ሳይሆን መሀል ላይ ሆኖ ሲታዘብ እስከቆየው ብዙ አስተዛዛቢ ነገሮች ታይተዋል፡፡ ለዘመናት አብረው የኖሩትን አስተዋይ ኢትዮጵያውያንን ሊወክሉ የማይችሉ ጀብደኝነቶች፣ አስመሳይነቶችና አድርባይነቶች የተሸራረቡበት የምሁራኑ ውሎ ያተረፈው ነገር ቢኖር እርስ በርስ መገፋፋትና መጫረስ ነበር፡፡ በነፃነት፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ማስከበር ስም ኢትዮጵያውያን ለድህነትና ለተመፅዋችነት ተዳርገዋል፡፡ አገራቸውም ለታሪካዊ ጠላቶች ጣልቃ ገብነት ተዳርጋለች፡፡

እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ኢትዮጵያ በድሮዎቹ ትውልዶች መስዋዕትነት እዚህ የደረሰች ብትሆንም፣ ይህ አርዓያነት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ አገር የመጠበቅ ባህሉ መቀጠል መቻሉ አስገራሚነት ነው፡፡ ነገር ግን ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሥልጣን የሚይዙ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ማሰቃየታቸውም አይዘነጋም፡፡ በየዘመኑ የተነሱ ገዥዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ መከራ ማድረሳቸው፣ ሕዝቡም በጋራ የገፈቱ ተጋሪ እንደነበር አይረሳም፡፡ ይህ ታሪካዊና አስተዋይ ሕዝብ ግን በአገሩና በገዥዎች መካከል ያለውን ልዩነት በሚገባ ይገነዘብ ስለነበር፣ እርስ በርስ በመጋባትና በመዋለድ ጭምር ማኅበራዊ መስተጋብሩን እያጠናከረ አገሩን በጋራ ይጠብቅ እንደነበር ማንም አይስተውም፡፡ ይህ እውነታ በገቢር ባይታይ ኖሮ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ምድር ብቸኛዋ በቅኝ ያልተገዛች አገር ተብላ አትንቆለጳጰስም ነበር፡፡ አፍሪካውያንም በኩራት የነፃነታችን እናት እያሉ በአደባባይ አይናገሩም ነበር፡፡ ይህ ትውልድ ይህን አኩሪ ታሪክ የማስከበርና የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ አገር በጥራዝ ነጠቆች ፕሮፓጋንዳ መጠልሸት የለባትም፡፡

የጥንቶቹ አስተዋይ ኢትዮጵያውያን ሲሳሳቱ ይቅርታ ለመባባልና ስህተቶች እንደገና እንዳይከሰቱ ሲሉ፣ በየማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ የሽምግልና ሥርዓቶችን በመጠቀም ራሳቸውን ያርሙ ነበር፡፡ አሁንም በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ጭምር በንግድ ሥራም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች የሚጋጩ ሰዎች ይዳኙባቸዋል፡፡ በሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ውስጥ ለሽምግልና የሚሰጠው ክብር ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ ማንም ተፈላጊ ሰው አክብሮ ሄዶ ለዳኝነት መቀመጡ የተለመደ ነው፡፡ ይህንን ሥርዓት ንቆ የቀረ ደግሞ ለውግዘት ስለሚዳረግና ስለሚናቅ፣ በተቻለ መጠን ራሱን አደብ አስገዝቶ ሽምግልናው ላይ መገኘት የተለመደ ተግባር ነው፡፡ በዘመናዊ ምሁራኖቻችን ሠፈር በአብዛኛው የሚታየው ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ እንኳንስ ራስን ለሽምግልና ሥርዓት ለማስገዛት ሕግ ለማክበር ፍላጎት አይታይም፡፡ በዚህ ዘመን አንዳች ችግር ሲያጋጥም የሚቀድመው የብሔር ወይም የእምነት ሰሌዳ ለጥፎ ወደ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች በመሄድ፣ አርቆ ማሰብ የጎደላቸው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን ከቢጤዎች ጋር ማቀጣጠል ነው፡፡ ጥራዝ ነጠቅነት በመብዛቱ ከመተራረም ይልቅ መሰዳደብና ጦር መማዘዝ እየቀለለ ነው፡፡

አገራቸውን ለምንም ነገር አሳልፈው መስጠት ሞት የሚሆንባቸው አዕላፍ ኢትዮጵያውያን ሲታሰቡ፣ ከራሳቸውና ከቡድናቸው ጥቅም በፊት አገር ምንም ብትሆን ደንታ የማይሰጣቸው ግብዞች በዚህ ዘመን መከሰታቸው ከማስገረም አልፎ ያሳዝናል፡፡ የጥቂቶችን ሥልጣንና ጥቅም ለማደላደል ሲባል በሕዝብ ስም እየተነገደ፣ ጦርነትን የሚያህል አውዳሚ ነገር ተከስቶ በብዙ መቶ ሺዎች ማለቃቸውና ሚሊዮኖች ለስደትና ለመከራ መዳረጋቸው ሲታሰብ የዘመኑ ምሁራንና ልሂቃን ጉዳይ ማነጋገሩ አይቀሬ ነው፡፡ ችግር ሲያጋጥም ረጋ ብሎ መነጋገርና በጋራ መፍትሔ መፈለግ የምሁሩነት ወግ መሆን ሲገባው፣ ራስን ከሕዝብና ከአገር በላይ አድርጎ ዕልቂትና ውድመት መደገስ ያሳፍራል፡፡ ከራስ ፀጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ ድረስ የድህነት ማጥ ውስጥ የተዘፈቀች አገርን እሳት ውስጥ ከቶ፣ በሕዝብ ስም መመፃደቅም ሆነ የራስን ክብርና ዝና አግዝፎ ለማሳየት የተኬደበት ምሁራዊ ድንቁርና ይህንን ትውልድ ቁጭት ውስጥ ሊከተው ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጥራዝ ነጠቅነት የሚኮራበት ሳይሆን፣ በመጪው ትውልድና ታሪክ የሚያስረግም ዕብደት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ስለዚህም ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...