- ለ26 ሚሊዮን ዜጎች 3.6 ቢሊዮን ዶላር ለሰብዓዊ ዕርዳታ ያስፈልጋል
ለስድስተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የአፍሪካ ኅብረት ዓመታዊ ኮንፈረንስ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የተገኙት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ፣ ከሁለት ዓመታት ጦርነት በኋላ ሰላማዊ ንግግር አድርገው ውሳኔውን በማስፈጸም ላይ የሚገኙት የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት ታጣዊዎች የጀመሩት እንቅስቃሴ ፍሬ እስኪያፈራ ማንኛውም ዓይነት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናገሩ፡፡
ዋና ጸሐፊው ኅዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተካሄደው የሁለቱ ተቋማት ዓመታዊ ኮንፈረንስ በተጨማሪ፣ በጉበኝታቸው ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ መሐማት ጋር የነበራቸውን ቆይታ አስመልክተው በዕለቱ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የተመድ ዋና ጸሐፊ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ጋር በመሆን በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በሰጡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት ለደረሱበት የሰላም ስምምነት ከፍተኛ የሆነ አድናቆት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ይህ ጅማሮ በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን ተቋማቸው አደራዳሪውን የአፍሪካ ኅብረትንም ሆነ ሁለቱን ወገኖች ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን፣ የአፍሪካን ችግርን አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ የአፍሪካ ኅብረት በበላይነት በጀመረው አመራር ላይ ከፍተኛ እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
‹‹አፍሪካ ሰላምን ትሻለች ሥር የሰደዱ ጦርነቶች እየፈተኑን ነው፤›› ያሉት ዋና ጸሐፊው አክለውም፣ ‹‹ሰላምን ማምጣት ቀላል ባይሆንም፣ ሰላም ምንጊዜም አስፈላጊ ነው፤›› ብለው፣ በተጀመረው ጥረት ሕዝቡ የሰላምን ትሩፋት እንዲያገኝ ማድረግና የተጀመረው ጥረት የኑሮ ሁኔታውን ሊያስተካክል የሚችል መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ከሰላም ውጪ ሌላ የተሻለ መፍትሔ ባለመኖሩ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የሰላም ሒደት ለማጠናከር፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተቻለውን ሁሉ ዕገዛ እንዲያደርግ ‹‹ከፊት ሆነን እንቀሰቅሳለን፤›› ብለዋል፡፡
በመንግሥት በኩል ከሚቀርበው ድጋፍና በአውሮፕላን እየደረሰ ካለው ዕርዳታ በተጨማሪ ወደ ትግራይ ክልል 550 የጭነት ተሽከርካሪዎች የተለያዩ ዓይነቶች የሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ጭነው መላካቸውን፣ የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ ኅዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በኒውዮርክ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ አንድ ወር በቀረው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 26 ሚሊዮን ዜጎች 3.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አክለው ገልጸዋል፡፡