በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀበት በስፋት እየተመናመነ መምጣቱንና ይህም የአገሪቱን ኢኮኖሚ የበለጠ ሊጎዳው ይችላል የሚል ትልቅ ሥጋት እንዳለ ተገለጸ፡፡ በፍጥነት ዕርምጃ ካልተወሰደም የተወሰነው የአገሪቱ የቆዳ ስፋት ወደ በረሃነት ሊቀየር እንደሚችል፣ እንዲሁም በርካታ የመሬት ክፍል ምርታማነት ሊያቆም እንደሚችል ጥናቶች እንደሚያሳዩ ባለሙያዎች አሳስበዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻናራና በግብርና ፋይናንስ ላይ ያተኮሩ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎችን፣ እንዲሁም አንድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለበትን ሁኔታ የሚገልጽ መጽሐፍ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ባለፈው ሐሙስ ኅዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ያቀረበ ሲሆን፣ በጥናታዊ ጽሑፎቹ ያነሷቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይትም ተካሄዶ ነበር፡፡
በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ቴክኒክ ኮሚቴ ኃላፊና የኢትዮጵያ ደን ልማት መሥሪያ ቤትን በመወከል የመጡት አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር)፣ በውይይቱ በርካታ ሐሳቦችን ያነሱ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ተሠርተው የነበሩ ጥናቶችን በማጣቀስ የተፈጥሮ ሀብት ኢትዮጵያ ውስጥ አሳሳቢ ደረጃ እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡
ወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት (World Recourse Institute) የተባለ ተቋም ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ላይ ያጠናውን ጥናት በማጣቀስ፣ የኢትዮጵያ ግማሹ የቆዳ ስፋት የሚሆነው (54 ሚሊዮን ሔክታር) መሬት በተለያየ ደረጃ በተፈጥሮ ሀብት መመናመን ላይ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ከ54 ሚሊዮን ሔክታር ውስጥ 11 ሚሊዮን ሔክታር በቶሎ መፍትሔ ካልተሰጠው ወደ በረሃነት ሊቀየር እንደሚችል ተናግረው፣ 18 ሚሊዮን ሔክታር ደግሞ መካከለኛ ደረጃ እንክብካቤ ካልተሰጠው እሱም ወደ በርሃነት ሊቀየር እንደሚችል አሳስበዋል፡፡
‹‹የመሬት ሀብት እየተመናመነ ነገር ግን የሕዝብ ቁጥር እጅግ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከጥንት ከአክሱም ሥልጣኔም ጀምሮ እስካሁን ድረስ የቀጠለው የፖለቲካና መሰል ጥፋቶች በመሬት መመናመንና አዲስ መሬት ከመፈለግ የሚከሰት ነው፤›› ሲሉ በቀረቡት ጥናቶች ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በግብርና ፋይናንስ ኢንሹራንስ ዘርፍ ላይ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት የማኅበሩ አባል ኃይሉ ኤልያስ (ዶ/ር)፣ ለግብርና የሚደረገው የፋይናንስ ተደራሽነት እጅጉን ትንሽ እንደሆነና ከ20 እስከ 25 በመቶ መሆኑን በጥናታቸው እንደደረሱበት ተናግረዋል፡፡ የፋይናንስ ተቋማትም ለትርፍ የተቋቋሙ እንደመሆናቸውና አትራፊነትን መሠረት በማድረጋቸው ብዙም የግብርና ፋይናንስና ለኢንሹራንስ አገልግሎት እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡ በግንዛቤ እጥረትና መሰል ጉዳዮችም አርሶ አደሮች ለእርሻቸው ኢንሹራንስና መሰል የፋይናንስ አገልግሎት እንደማይገቡ ጠቅሰዋል፡፡
በማስቀጠል ‹‹የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ለዘላቂ ኢኮኖሚ ልማት በኢትዮጵያ!›› በሚል ሌላ ጥናት ያቀረቡት አበበ በየነ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ እሳቸውም በአረንጓዴ አሻራ ዙሪያ ላይ ያሉ በርካታ ተግዳሮቶችና ስኬቶችን የጥናታቸውን ውጤት ሲያቀርቡ ተናግረዋል፡፡