ለመጪው ዓመት የምርት ዘመን ጥቅም ላይ የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከተፈጸመ በኋላ፣ ከሞሮኮ ወደብ ተጭኖ ወደ ጂቡቲ መጓጓዝ መጀመሩ ተገለጸ፡፡
በዚህ ዓመት ከተገዛው ማዳበሪያ ውስጥ 218,894 ሜትሪክ ቶን ወይም 2,188,940 ኩንታል የሚሆነው ኤንፒኤስ (NPS) የተባለው ማዳበሪያ ሲሆን፣ 568,658 ሜትሪክ ቶን ወይም 5,686,580 ኩንታል የሚሆነው ደግሞ ኤንፒኤስ ቦሮን (NPSB) የተባለው የአፈር ማዳበሪያ ዓይነት መሆኑ ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን በአጠቃላይ 7,875,520 ኩንታል የኤንፔኤስ ማዳበሪዎችን ግዥ መፈጸሟን፣ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለሪፖርተር አረጋግጧል፡፡ የዩሪያ ማዳበሪያ ግዥ በአሁኑ ወቅት በሒደት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአፈር ማዳበሪያ ግዥን በብቸኝነት ፈጽሞ በአገር ውስጥ የሚያሠራጨው የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹ለቀጣዩ የምርት ዘመን እንዲውል ታስቦ ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 29,045 ሜትሪክ ቶን ወይም 29,450 ኩንታል ኤንፒኤስ ቢ (ቦሮን) ከሞሮኮ ወደብ መጫን ጀምሯል፤›› ብለዋል፡፡
እንደ ቀዳሚው ዓመት ሁሉ የሞሮኮው ‹‹ኦሲፒ›› ኩባንያ የኤንፒኤስ ማዳበሪያን ለኢትዮጵያ ማቅረቡ የተገለጸ ሲሆን፣ የመጀመሪዋ መርከብ ከሞሮኮ ወደብ የማዳበሪያ ጭነቱን አንስታ ማጓጓዝ እንደጀመረች አቶ ጋሻው አረጋግጠዋል፡፡
የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ባለፈው ዓመት፣ ለ2013 እና 2014 ዓ.ም. የሰብል ዘመን የሚያገለግል 12,876,623.5 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙ ይታወሳል፡፡
መንግሥት ባለፈው ዓመት ከውጭ ለተገዙ የኤንፒኤስ (NPS)፣ ኤንፒኤስ ቦሮን (NPSB)፣ እንዲሁም የዩሪያ ማዳበሪያ የትራንስፖርትና ሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎች ሳይጨመሩ፣ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ማውጣቱን፣ በተጨማሪ ለመርከብ ማጓጓዣ፣ ለከረጢትና ለአስተዳደራዊ ወጪዎች ከ14.5 ቢሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙን ኮርፖሬሽኑ ለሪፖርተር አረጋግጦ ነበር፡፡
ለ2015 ዓ.ም. እና ለ2016 ዓ.ም. የምርት ዘመን ለሚያገለግለው የማዳበሪያ ግዥ፣ እስካሁን መንግሥት ምን ያህል ወጪ አውጥቷል? ለሚለው ጥያቄ አጠቃላይ ግዥው ተከናውኖ ሲጠናቀቅ የሚገለጽ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡
ግዥው ከተጠናቀቀው የማዳበሪያ ግብዓት የመጀመሪያው ዙር ባለፈው ሳምንት የሞሮኮ መጫኛ ወደብ መድረሱ ታውቋል፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አራት መርከቦች 218 ሺሕ ቶን ኤንፒኤስ ማዳበሪያ ጭነው ጂቡቲ ወደብ እንደሚደርሱ፣ የባህር ትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ከዓለም አቀፍ የማዳበሪያ ዋጋ መናርና ከሩሲያና ከዩክሬን ጦርነት ምክንያት ለ2014 እና 2015 ዓ.ም. የሰብል ዘመን ጥቅም ላይ የሚውል ማዳበሪያ ግዥ ፈጽሞ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ በብርቱ ተፈትኖ የነበረው መንግሥት፣ ካለፈው የግዥ ሒደት ተሞክሮ በመውሰድ ለመጪው የሰብል ዓመት የሚያገለግል የአፈር ማዳበሪያ በጊዜ ለማቅረብ ከሁለት ወር በፊት ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱን፣ የግብርና ሚኒስትር ደኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ባለፈው ዓመት ከማዳበሪያ ግዥ ጋር በተገናኘ ያጋጠመውን መስተጓጎል በተያዘው ዓመት እንዳያጋጥም መንግሥት አስቀድሞ ግዥውን ለመፈጸም ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ጨረታ ማውጣቱን በወቅቱ የተናገሩት ሶፊያ (ዶ/ር)፣ የማዳበሪያ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ከውጭ ከማስገባት ይልቅ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያዘጋጅና ሌሎች በአገር ውስጥ ካሉ ግብዓቶች መዘጋጀት የሚችሉ ፈሳሽ ማዳበሪያዎችን (በተለይም ዩሪያን በተወሰነ ደረጃ መተካት የሚችሉ) በስፋት እንዲጠቀም የማድረጉ ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላል ብለው ነበር፡፡