ከተጀመረ ሦስተኛ ወሩን ባስቆጠረው የ2015 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በአፋርና በጋምቤላ ክልሎች ትምህርት ቤት መገኘት ከነበረባቸው ተማሪዎች መሀል፣ ትምህርት ቤት የገቡት 42 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ቀሪዎቹ 58 በመቶ የሚሆኑት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ሁለቱ ክልሎች ግጭት፣ ጎርፍና ድርቅ በከፍተኛ ሁኔታ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ከመሆናቸው የተነሳ የተመዘገበው የተማሪ ቁጥር አንስተኛ መሆኑን የገለጹት፣ በትምህርት ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ መዝገቡ ቢያዝን ናቸው፡፡
ከተመዘገቡት ተማሪዎች መካካል በአፋር ክልል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ከታቀደው 39,170 ውስጥ 13,568፣ ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል 320 ሺሕ ታቅዶ 135 ሺሕ፣ እንዲሁም በጋምቤላ ክልል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ከታቀደው 225 ሺሕ ውስጥ 6,900፣ እንዲሁም ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ ይጠበቅ ከነበረው 129 ሺሕ ውስጥ 54 ሺሕ ብቻ በትምህርት ላይ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ምክንያት ከወደሙ 1,335 ትምህርት ቤቶች መካከል፣ በ2014 ዓ.ም. 200 ትምህርት ቤቶችን በልዩ ሁኔታ ለመገንባት ዕቅድ መያዙን ተነግሯል፡፡
ይህ የተገለጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ የሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትምህርት ሚኒስቴርን የ2015 ዓ.ም. ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ኅዳር 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በገመገመበት ወቅት ነው፡፡
የትምህርት ዘርፉን ለመደገፍ በ2015 የበጀት ዓመት በመንግሥትና በልማት አጋሮች ከሚደረገው ደጋፍ በተጨማሪ፣ ከሕዝብ በገንዘብና በዓይነት 13 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ለማሰባሰብ መታቀዱን የገለጹት አቶ መዝገቡ፣ በሩብ ዓመቱ 7.3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ማሰባሰብ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት የበጀት ወጪያቸውን አሥር በመቶ የሚሆነውን በውስጥ ገቢያቸው የሸፈኑ ዩኒቨርሲቲዎች ብዛት፣ ከአጠቃላይ 47 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አሥር በመቶዎቹ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በየደረጃው ያለው የትምህርት ጥራት አሳሳቢ መሆን በመድረኩ የተነሳ ሲሆን፣ ለአብነት ያህል ብቁ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው የሁለተኛ ደረጃ ርዕሰ መምህራን ብዛት 34 በመቶ ብቻ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ለደረጃው ብቁ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው መካከለኛ ደረጃ ወይም ከ7ኛ እስከ 12ኛ ከፍል መምህራን ብዛት 50.2 በመቶ ብቻ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡
በተመሳሳይ በሙያ ፈቃድ ምዘና የሚያልፉ የትምህርት ቤት አመራሮች 29 በመቶ፣ የተማሪዎች የመመረቅ ምጣኔ 74 በመቶ፣ የተማሪዎች መውጫ ፈተና የማለፍ ምጣኔ 38 በመቶና የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች የመቀጠር ምጣኔ 58 በመቶ፣ እንዲሁም የተማሪዎች የማጠናቀቅ ምጣኔ 86 በመቶ ላይ እንደሚገኝ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሌላ በኩል ስታንዳደርዱን የጠበቀ መሠረተ ልማት ያላቸው ትምህርት ቤቶች 55 በመቶ መሆናቸው ተገልጿል፡፡