Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሆላንድ ካር ድርጅትን በተዛባ የንግድ አሠራር እንዲከስር አድርገዋል የተባሉ ተከሳሾች ከዕዳ ነፃ ሆኑ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ክርክሩ ስምንት ዓመታትን ፈጅቷል

የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ ገጣጥሞ በመሸጥ ላይ እያለ፣ በፍርድ ቤት መክሰሩ ታውጆ ሥራ ያቆመው ሆላንድ ካር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ለኪሳራ የተዳረገው የድርጅቱ ባለቤቶች፣ ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ ድርጅቱ ለተቋቋመለት ዓላማና ጥቅም መሥራት ሲገባቸው እርስ በርስ በመሻሻጥ፣ ንብረት በመሰወርና ለግል ጥቅም በማዋል፣ እንዲሁም የተዛባ የንግድ አሠራር በመከተላቸው መሆኑን በመግለጽ ተመሥርቶባቸው ከነበረው ክስ በነፃ ተሰናበቱ፡፡ 

ላለፉት ስምንት ዓመታት ክሱን ሲመረምር የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ንግድና ኢንቨስመንት ችሎት፣ ኅዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ፍርድ እንዳብራራው፣ ሆላንድ ካር ጥር 7 ቀን 2005 ዓ.ም. የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍትሐ ብሔር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 200820 ‹‹ከስሯል›› ብሎ ፍርድ ከሰጠ በኋላ ንብረት ጠባቂ ተሾሟል፡፡

ለከሰረው ሆላንድ ካር የተሾመው ንብረት ጠባቂ (አቶ ግርማ ዓለሙ)፣ ከሁለት ዓመታት በኋላ ታኅሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በታደሰ ተሰማ (ኢንጂነር)፣ በካሶፒያ ካር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በአቶ ሰለሞን ታሪኩ፣ በዘመን ባንክና በቲኬ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ላይ ክስ መሥርቶ ነበር፡፡

ሆላንድ ካር ከበርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች የተሽከርካሪ ሽያጭ ፈጽሞ፣ ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ግብር አለመክፈሉና ተሽከርካሪዎቹን ሠርቶ ለማስረከብ ከግለሰቦችና ድርጅቶች ገንዘብ ተቀብሎ በውሉ መሠረት አለማስረከቡ የክሱ ዋና ዋና ፍሬ ነገሮች መሆናቸው በክሱ ተጠቅሷል፡፡

ለኩባንያው መክሰር በአንድነትና በተናጠል ኃላፊነት አለባቸው እንዲባሉ በዋናነት ክስ የተመሠረተባቸው የድርጅቱ ባለቤት ታደሰ ተሰማ (ኢንጂነር)፣ ካሶፒያ ካርና ሥራ አስኪያጁ አቶ ሰለሞን የተባሉት ተከሳሾች ከተሽከርካሪዎችና ከማሽነሪዎች ሽያጭ፣ እንዲሁም የተሟላ ጋራዥ ኪራይ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይና በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ይዞታዎች፣ በኮንቴይነር ታሽገው የነበሩ መገጣጠሚያዎችና ያልተሸጡ ተሽከርካሪዎች እንዲወሰንለት ንብረት ጠባቂው ባቀረበው ክስ ጠይቆ ነበር፡፡

ከቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶች ጀምሮ ለከሰረው ሆላንድ ካር ንብረት ጠባቂ እንዲወሰንና ተከሳሾች እንዲከፍሉ ዳኝነት በተጠየቀበት ክስ ላይ፣ በዋናነት ቀርበው ክሱን ለስምንት ዓመታት የተከራከሩት የድርጅቱ ባለቤት የነበሩት የካሶፒያ ድርጅት ከፍተኛ ባለድርሻ ታደሰ (ኢንጂነር)፣ ክርክራቸውን አድርገዋል፡፡

ክሱ የሕግም ሆነ የፍሬ ነገር መሠረት እንደሌለው ጠቅሰው፣ መነሻ መከራከሪያ ያቀረቡት ታደሰ (ኢንጂነር)፣ በአገራቸው የመኪና ማምረቻ በ30 ሚሊዮን ብር አቋቁመው ሲሠሩ መቆየታቸውን ጠቁመው፣ በአገሪቱ ከ1999 ዓ.ም. እስከ 2000 ዓ.ም. ባጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የብር ዋጋ 30 በመቶ በመውረዱ አንድ ተሽከርካሪ ገጣጥሞ ለማስረከብ 50,000 ብር ቀብድ ቢቀበሉም፣ እስከ በ100,000 ብር በሚደርስ በኪሳራ ማስረከባቸውንና ለኪሳራ መዳረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ ድርጅቱ ኪሳራ ስላጋጠመው ደንበኞች የተፈጠረውን የዋጋ ልዩነት እንዲከፍሉ በመስማማት፣ ክፍያውን በዘመን ባንክ በኩል ለዚሁ ተግባር በተከፈተ ሒሳብ ውስጥ እንዲያስገቡ ከደንበኞች በኩል በተቋቋመ ኮሚቴ አማካይነት እንዲፈጸም ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ ደንበኞቻቸው የጨመሩትም ገንዘብ ሊበቃቸው ባለመቻሉ ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑበትን ካሶፒያ ካር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በማስያዝ፣ ከዘመን ባንክ 22,000,000 ብር በመበደር 500 ተሽከርካሪዎችን ገጣጥመው ለደንበኞች ማስረከባቸውንም አስረድተዋል፡፡

ይህም የሚያሳየው ከሳሽ (የከሰረው ሆላንድ ካር ንብረት ጠባቂ) እንደከሰሰው ሸጠው ወደ ኪሳቸው አለማስገባታቸውን በማስረጃ ደግፈው መከራከራቸውን ፍርዱ ያብራራል፡፡

ቀብድ ከከፈሉት ውስጥ 120 ደንበኞች ሲቀሩ የተበደሩት ገንዘብ በማለቁና ከውጭ ያስጫኗቸው ዕቃዎችን ቀረጥ ከፍሎ ማስገባት ባለመቻሉ፣ ድርጀቱ ለኪሳራ በመዳረጉ፣ የመክሰር ውሳኔ እንዲሰጥ ለፍርድ ቤት በማመልከት የኪሳራ ፍርድ ማሰጠታቸውን ገልጸው ታደሰ (ኢንጂነር) መከራከራቸውን ፍርዱ ያስረዳል፡፡

በተለያዩ ቦታዎች የነበሩ ይዞታዎችንና ተሽከርካሪዎችን፣ የከሰረው ሆላንድ ካር ንብረት ጠባቂ እንዳቀረበው ክስ ተሸጠው ገንዘቡ በተከሳሾች የተወሰደ ሳይሆን፣ ዘመን ባንክ ላበደረው ገንዘብ ለመያዣነት የዋሉ መሆናቸውንም በክርክሩ ላይ በማስረጃ አስደግፈው ማቅረባቸውን ፍርዱ ያብራራል፡፡ ተከሳሾቹ ሰፋ ያለ መከራከሪያ ሐሳብና ማስረጃ ማቅረባቸውንና ከሳሽም የማብራሪያ መልስ መስጠቱን ፍርዱ ያብራራል፡፡

ችሎቱም ክርክሩን አዳምጦ ከጨረሰ በኋላ፣ ተከሳሽ ታደሰ (ኢንጂነር) ለሆላንድ ካር መክሰር ኃላፊነት አለባቸው ወይስ የለባቸውም? ሌሎቹም ተከሳሾች ኃላፊነት አለባቸው ወይስ የለባቸውም? የተያዙትን ንብረቶች ለከሳሽ ማስረከብ አለባቸው ወይስ የለባቸውም? ቲኬ ኢንተርናሽናል ድርጅት የከሳሽ ሰነዶችና ንብረቶች በእጁ ይገኛሉ ወይስ አይገኙም? የሚሉ ጭብጦችን ይዞ መመርመሩን ፍርዱ ያሳያል፡፡

ፍርድ ቤቱ እያንዳንዱን የክስ ዓይነት በሰነድና በምስክሮች መረጋገጥ አለመረጋገጡን ከመረመረ በኋላ፣ ከሳሽ (የከሰረው ሆላንድ ካር ንብረት ጠባቂ) ያቀረበው ክስ በማስረጃ ያልተደገፈ፣ አንዳንዱን ክስ ያልተቃወመና ራሱ ባቀረበው ሰነድ እውነት መሆናቸው በመረጋገጡ፣ ተከሳሾቹ ሆላንድ ካር በመክሰሩና ንብረቱ ዕዳውን ለመክፈል በቂ ባለመሆኑ ምክንያት ለሚመጣ ዕዳ ኃላፊነት የለባቸውም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሶች የሚያስረክቡት ንብረት ስለመኖሩ በማስረጃ አለመረጋገጡንም በውሳኔው ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች