Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ለ40 ዓመታት የሚዘልቅ የመሬትና የሼድ ኪራይ ውል ተፈራረመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ለ40 ዓመታት የሚዘልቅ የመሬትና የሼድ ኪራይ ውል ከሦስት ድርጅቶች ጋር ተፈራረመ፡፡

ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል የፈጸሙት ኩባንያዎች ዋርቃ ትሬዲንግ፣ ሎንግ ማርች ኤሌክትሪካል ኢኪዩፕመንት ማኑፋክቸሪንግና ኤንኬ ወርልድ ሜዲካል ኢኪዩፕመንት ማኑፋክቸሪንግ ናቸው፡፡ ድርጅቶቹ ዓርብ ኅዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢንተር ሌግዥሪ ሆቴል ከኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

የዋርቃ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ተወካይ አቶ ዮሴፍ ምስጋና ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ 5,500 ካሬ ሜትር ሼድ በመከራየት የተለያዩ ዓይነት ክሮችን ለማምረት ድርጅቱ ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጓል፡፡

ለሼዱ ኪራይ በወር አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚከፍሉና በቅርቡ ሥራ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በርካታ ቢሆኑም ለግብዓትነት የሚጠቀሙት ክር በገበያው ውስጥ እጥረት መኖሩን የገለጹት አቶ ዮሴፍ፣ ድርጅቱ ሥራ ሲጀምር በቀን ከአምስት እስከ አሥር ቶን ለማምረት ማቀዱን አስረድተዋል፡፡

ወደፊት ደግሞ በቀን ከ200 እስከ 300 ቶን ክር በማምረት ለገበያ የማቅረብ ዕቅድ እንዳላቸው ተወካዩ ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የክር ምርቱን ለማቅረብ ማለሙን አቶ ዮሴፍ አክለዋል፡፡

በቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ አንድ ሔክታር የለማ መሬት የተረከበው ኤንኬ ወርልድ ሜዲካል ኢኪዩፕመንት ሲሆን፣ አላቂ የሕክምና ግብዓቶች ለማምረት ስምምነት ፈጽሟል፡፡

ኤንኬ ወርልድ ሜዲካል ኢኩዩፕመንት ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ተወካይ ኑአማ ቢፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከኮርፖሬሽኑ ጋር የሕክምና ግብዓቶችን ለማምረት ለ40 ዓመታት የሚቆይ ውል መፈጸማቸውን አስረድተዋል፡፡

እንደ ኑአማ (ዶ/ር) ገለጻ፣ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ አንድ ሔክታር መሬት የኪራይ ክፍያው በዓመት እስከ 20 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

ሌላው የቻይና ኩባንያ ሎንግ ማርች ኤሌክትሪካል ኢኪዩፕመንት ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 3,000 ካሬ ሜትር ሼድ በመከራየት 240 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት ማድረጉ ታውቋል፡፡

ድርጅቱ የኤሌክትሪክ ቆጣሪና ግብዓቶችን በማምረት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ መሆኑን፣ ለ250 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚያስገኝ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

ስምምነት የተፈራረሙት ሦስቱ ድርጅቶች ከ448 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት ያስመዘገቡ መሆናቸውን፣ ለ540 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ያስገኛሉ ተብሏል፡፡ 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ 13 የኢንዱስትሪ  ፓርኮች ከ125 በላይ የውጭና የአገር ውስጥ አምራቾች እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

የኪራዩ ሁኔታም የለማ መሬት ሲሆን ውሉ እስከ 38 ዓመታት የሚዘልቅ መሆኑን፣ ቀሪው እስከ አሥር ዓመታት የሚቆይ ነው ብለዋል፡፡ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል የፈጸሙት ሦስት ድርጅቶች ጋር ግን የ40 ዓመታት ስምምነት ፈጽመዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በሚቀጥለው ሳምንት ከአራት የተለያዩ አምራች ድርጅቶችም የሼድና የመሬት ኪራይ ውል ይፈጸማል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች