Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኤችአይቪ/ኤድስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለጸ

በኤችአይቪ/ኤድስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለጸ

ቀን:

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኤችአይቪ/ኤድስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለጸ፡፡ በቫይረሱ የተያዙ አብዛኛዎቹ የማኅረበሰብ ክፍሎች አድልኦና መገለል እየደረሰባቸው መሆኑን፣ ኔትዎርክ ኦፍ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ኢን ኢትዮጵያ የተሰኘ ድርጅት አስታወቀ፡፡

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ባይሳ ጫላ ዓርብ ኅዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ተቋሙ በቅርቡ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ፣ በኢትዮጵያ በኤችአይቪ ኤድስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና በቫይረሱም የተያዙ አፍላ ወጣቶችና ሴቶች አድልኦና መገለል እየደረሰባቸው ነው ብለዋል፡፡

በቅርቡ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ የተደረገው ጥናት፣ በኢትዮጵያ አብዛኛውን ኤችአይቪ/ኤድስ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች፣ በማኅበራዊ ኑሯቸውም ላይ ሆነ ጤና ተቋማት ሲሄዱ አድልኦና መገለል ይደርስባቸዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የኤችአይቪ/ኤድስ ሥርጭትን ለመቀነስና በቫይረሱ የተያዙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የአድልኦና የመገለል ችግር እንዳይገጥማቸው፣ ከዚህ በፊት የነበሩ ፖሊሲዎችን እንደ አዲስ መከለስ ትልቅ አማራጭ እንደሆነና ይህም በመንግሥት ደረጃ በቀጣይ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ጥናቱ ሲደረግ ከፍተኛ የኤችአይቪ/ኤድስ ሥርጭት በነበረባቸው 265 ወረዳዎች መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ጥናቱም ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ባለ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጭምር የተደረገ ነው፤›› ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

ኤችአይቪ/ኤድስ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሰዎች መድኃኒት ለማግኘት እንኳን ወደ ሕክምና ተቋማት በሚሄዱበት ጊዜ በጤና ባለሙያዎች እንደሚገለሉ የገለጹት አቶ ባይሳ፣ በዚህም የተነሳ በርካታ ሕሙማን ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ተናግረዋል፡፡

ተቋሙም በአገር አቀፍ ደረጃ በሚገኙ 300 የሕክምና ተቋሞች ላይ የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በመጠቀም፣ የኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት መጠቀም ያቆሙ ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር በተገኘ ከፍተኛ ችግር እንዳለ፣ በተለይም በጦርነቱ ወቅት የአቅርቦትና የተጠቃሚዎች ቁጥር ሊመጣጠን አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያሳው፣ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ15 እስከ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል ከሚገኙት ውስጥ 69 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በቫይረሱ እየተያዙ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኤችአይቪ/ኤድስ የተያዙ መሆናቸውን፣ ይህም ከታሰበውና ከተገመተው በሦስት እጥፍ ከፍ ያለ መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡

ከ15 እስከ 24 የዕድሜ ክልል ላይ በሚገኙ ወንዶች 39 በመቶ የሚሆኑት የቫይረሱ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶችን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ፣ 24 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችም በቂ ዕውቀት እንዳላቸው ተገልጿል፡፡

የዓለም ኤድስ ቀን ‹‹ፍትሐዊና ተደራሽ የኤችአይቪ ኤድስ አገልግሎት›› በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ ኅዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ተከብሮ ውሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...