- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ሰላም ሰላም … ተቀመጥ!
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር! ቀድሜ ቀጠሮ እንዲያዝልኝ ስጠይቅ እንደገለጽኩት በተቋሙ ሠራተኛ ተወክዬ ነው የመጣሁት።
- እንዴ? አንተ የእኛ ተቋም ባልደረባ አይደለህም እንዴ?
- ነኝ ክቡር ሚኒስትር!
- ታዲያ በየትኛውን ተቋም ሠራተኛ ነው የተወከልከው?
- በዚሁ በእኛው ተቋም ሠራተኛ ነው የተወከልኩት ክቡር ሚኒስትር።
- እንዴት? በቀጥታ ከሠራተኛው ጋር የምገናኝበት መድረክ እያለ አንተን መወከል ለምን አስፈለገ?
- የሠራተኛውን የኑሮ ሁኔታ የሚመለከት ስለሆነ በዕድሜም በልምድም አንተ ብታነጋግራቸው ይሻላል ብለው ስለወከሉኝ ነው።
- ምንድነው ጉዳዩ?
- ክቡር ሚኒስትር ሠራተኛው በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው።
- እሱ የሁላችንም ችግር ነው … በአገር ጭምር የመጣ ነው።
- ክቡር ሚኒስትር የመንግሥት ሠራተኛው ግን የከፋ ችግር ውስጥ ነው ያለው። በተለይ ተቋማችን …
- ለተቋማችን ተለይቶ የመጣ ችግር ነው እንዴ?
- አይለደም። ግን የችግሩን ጥልቀት የሚረዳልን አጥተናል።
- ምን ማለትህ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር እኛ ተቋም ውስጥ ያለውን ሁኔታ ቢያዩ የችግሩን ጥልቀት ይረዱታል። በቀን አንዴ ብቻ የሚመገቡ ባልደረቦቻችን እየተበራከቱ ነው።
- እና ምን ይደረግ ነው የምትለው? ለዚህ ተቋም ብቻ የሚወሰን ነገር እንደማይኖር አታውቅም?
- እሱን እገነዘባለሁ። በሠራተኛው የተወከልኩትም እርስዎ መፍትሔ እንዲሰጡን አይደለም።
- እና ለምንድነው?
- ከፍተኛ የመንግሥት አመራር እንደመሆንዎ መጠን የሚመሩት ተቋም ሠራተኞችን ችግር ለካቢኔ እንዲያቀርቡልን ወይም ጉዳዩ ሲነሳ እንዲያስረዱልን ነው።
- ጉዳዩ እንዴት ይነሳል? ማን ያነሳዋል?
- በሁሉም የመንግሥት ተቋማት ያሉ ሠራተኞች ተመሳሳይ ጥያቄ ይኖራቸዋል ወይም የዚህ ተቋም ሠራተኞች እኔን እንደወከሉት ሌሎቹም እንደዚያ ሊያደርጉ ይችላሉ ብዬ ነው።
- እሺ ተነሳ እንበል …
- ከተነሳማ በዚህ ተቋም ያሉ ሠራተኞች ያሉበትን አስከፊ ሁኔታ እንዲያስረዱልንና መፍትሔ እንዲጠይቁልን ነው፡፡
- ምን ብዬ ነው መፍትሔ የምጠይቀው?
- ሠራተኛው በሚያገኘው ደመወዝ የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም አልቻለም ይበሉልን።
- እሺ … ከዚያስ?
- ከዚያማ ሠራተኛው የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ እያቀረበ ነው ሊጨመርለት ይገባል ይበሉልን!
- እሺ እንደዚያ አልኩ እንበል። ለደመወዝ ጭማሪ የሚሆነው በጀት ከየት እንደሚመጣ አመላክት ብባልስ?
- እሱን በጋራ የምትመልሱት እንጂ ለእርሶ ብቻ የሚተው አይመስለኝም።
- በጋራ መፍትሔ ለመስጠትም እኮ ሐሳብ ማቅረብ ይጠይቃል።
- ክቡር ሚኒስትር መንግሥት የሠራተኛውን ችግር በቅንነት ከተመለከተውና ካሰበበት መፍትሔ አይጠፋም።
- አይ አንተ … እስኪ መፍትሔ ጠቁም ብትባል አንድ መፍትሔ የለህም ለማማረር ግን…
- ክቡር ሚኒስትር በእርሶ ያምራል ብዬ እንጂ ጠቁም ካሉኝማ እጠቁማለሁ!
- እስኪ በላ … ?
- መቼም የጫካ ቤተ መንግሥት ፕሮጀክት ይታጠፍ አልልም።
- እ … ብትልስ?
- እኔም አልልም ግን …
- ግን ምን ልትል?
- ይዘግይና ሰው እንታደግ እላለሁ!
- አሃ … ለዚህ ነው የመጣኸው?
- ክቡር ሚኒስትር በቀን አንዴ ብቻ ተመግበው የሚውሉ ባልደረቦቻችን ቁጥር እየጨመረ ነው። ጥያቄያችን ከፖለቲካ ንፁህ መሆኑንም እንዲረዱኝ እፈልጋለሁ።
- እንዴት ነው ከፖለቲካ ንፁህ የሚሆነው?
- እውነቴን ነው ክቡር ሚ;ለስትር!
- እውነቱ ምንድነው?
- የኑሮ እንጂ የፖለቲካ ጥያቄ የለንም ክቡር ሚኒስትር!
- የቤተ መንግሥት ግንባታ ይቁም እያልክ?
- መፍትሔ ጠቁም ስላሉኝ ነዋ!
- ብልህስ? የቤተ መንግሥት ግንባታ ይቁም ትላለህ?
- ተከራከር ካሉኝም ሠራተኛው እየተራበ ቤተ መንግሥት መገንባት ቅደም ተከተሉን የጠበቀ መስሎ አይታየኝም።
- ይኸው … ዋናው ጉዳይህ ቤተ መንግሥቱ ነው።
- አይደለም ክቡር ሚኒስትር!
- እየሰማሁህ?
- ክቡር ሚኒስትር ጉዳዬ መንግሥት ችግሩን ተረድቶ ደመወዝ እንዲጨምር መጠየቃችንን እንዲያስረዱልን ነው። ካልሆነ ደግሞ …
- ካልሆነ ምን?
- ደመወዝ ካልሆነ ደግሞ ለተማሪዎች እንደተዘጋጀው ለእኛም እንዲዘጋጅልን ነው።
- ለእኛም ማለት?
- ለመንግሥት ሠራተኛው ማለቴ ነው?
- ለመንግሥት ሠራተኛው ምን ይዘጋጅ ነው ምትለው?
– የምገባ ፕሮግራም! |
– |