Thursday, November 30, 2023

የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና ወረዳዎችን በክላስተር አደረጃጀት ሥር እንዲገቡ የያዘውን ዕቅድ ለመተግበር እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ሲዳማና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ራሳቸውን ከቻሉ በኋላ፣ በደቡብ ክልል ሥር የቆዩ ዞኖችና ወረዳዎች ዕጣ ፈንታ ለረዥም ጊዜ ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሰሞኑ እንዳስታወቀው ከሆነ ግን፣ ዕጣ ፈንታቸው ባልተለየ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ ለጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዟል፡፡

የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ለጉራጌ ዞን የክልልነት ጥያቄ ምላሽ ይሰጥ በማለት ለተቃውሞ የወጡ የጉራጌ ተወላጆች

ሲዳማና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ራሳቸውን ችለው ከወጡ በኋላ የቀሩትን ዞኖችና ልዩ ወረዳዎችን በሁለት የክላስተር ክልል አደረጃጀቶች ሥር የማዋቀር ዕቅድ በመንግሥት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ግን ከአንዳንድ የዞን አስተዳደሮች በኩል ከባድ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡

በዚህ የተነሳ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዴኦና ኮንሶ ዞኖች፣ እንዲሁም ቡርጂ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ፣ አሌና አማሮ ልዩ ወረዳዎች ነው የክላስተር ክልል አደረጃጀትነት ሕዝበ ውሳኔው በጥር ወር የሚካሄደው፡፡

ቀሪዎቹ ጉራጌ፣ ሃዲያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ ጠምባሮና ሀላባ ዞኖች፣ እንዲሁም የየም ልዩ ወረዳ ዕጣ ፈንታ እስካሁን አለየለትም፡፡ ከእነዚህ በአንድ ክላስተር ክልል አደረጃጀት ይካተቱ ከተባሉት መካከል ደግሞ አደረጃጀቱን አጥብቀው የተቃወሙ የዞን አስተዳደሮች በመኖራቸው፣ ጉዳዩ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ገና ውሳኔ እየጠበቀ ነው፡፡  

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ ጥያቄው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ መፅደቅ ይጠበቅበታል፡፡ በአንድ ክላስተር ተደራጁ ከተባሉት መካከል በተለይ የጉራጌ ዞን ያቀረበው ተቃውሞ ጠንከር ብሎ በመምጣቱ የተነሳ፣ በዚህኛው አደረጃጀት ላይ ሕዝበ ውሳኔው ይካሄድ ብሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን ለምርጫ ቦርድ ለመምራት መቸገሩ ነው የተነገረው፡፡

ይህም ቢሆን የተለያዩ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖችና ወረዳዎች በአንድ ክልል ሰብሰብ ብለው እንዲደራጁ የቀረበው ዕቅድ ከእነ ብዙ ተቃውሞው ወደ መሬት እየወረደ ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ ተቃውሞው የበለጠ እንዲባባስ እያደረገው ይገኛል፡፡ በተለይ በክላስተርም ሆነ በሌላ መንገድ ከሌሎች ብሔረሰብ አስተዳደሮች ጋር ተሰባስበን ክልል አንፈጥርም ብለው ሲቃወሙ የቆዩ ዞኖች፣ አሁንም በተቃውሟቸው እንደገፉ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ከሰሞኑ የፖለቲካ ውጥረቱና ተቃውሞው የጨመረው የጉራጌ ዞን በዋናነት ይገኝበታል፡፡

ከሰሞኑ ብቻ ጉራጌ ዞን የራሱ ክልል ይገባዋል የሚል ተቃውሞ ያነሱ ከ200 በላይ ወጣቶች መታሰራቸውን የአካባቢው ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ጉራጌ ለብቻው ክልል እንዲሆን ሲቀሰቅሱና በተለያዩ መንገዶች ጥያቄ ሲያነሱ የቆዩ የማኅበረሰብ አንቂዎችና ፖለቲከኞች መታሰራቸው ተሰምቷል፡፡

የጉራጌ ዞን ዕዣ ወረዳን ወክለው የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌን ጨምሮ፣ የጉራጌ ክልልነትን ጥያቄ ሲያቀነቅኑ የነበሩ ታዋቂ ፖለቲከኞችና ማኅበራዊ አንቂዎች መታሰራቸው ደግሞ ችግሩን እያወሳሰበው እንደሚገኝ  ሥጋታቸውን የሚገልጹ አሉ፡፡

የዞኑ አስተዳደር ኅዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ጥያቄውን ሽፋን በማድረግ ሕገወጥ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቆ ነበር፡፡ የዞኑ አስተዳደር በዚህ መግለጫው ለረዥም ጊዜ ሲቀርብ የነበረውን የክልልነት ጥያቄን ለመመለስ የሚያስችል አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ የለም ብሎ እንደሚያምን አስታውቆ ነበር፡፡ የዞኑ አስተዳደር መግለጫውን ሲቀጥልም፣ ‹‹መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ በመቀበል ተግባራዊ መደረግ እንዳለበትና የዞናችን ሰላም ወደነበረበት መመለስ እንዳለበት የዞኑ አስተዳደር ያምናል፤›› በማለትም የክላስተር አደረጃጀቱን ውሳኔ የተቀበለው መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡

የዞኑ አስተዳደር ይህን ቢልም ጥያቄያችን መልስ ሊያገኝ ይገባል ያሉ የጉራጌ ተወላጆች ግን፣ የክልልነት ጥያቄያቸውን ማስተጋባት ሲቀጥሉ ነው የታየው፡፡ ይህን ተከትሎም የደቡብ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ባውዴ በመገናኛ ብዙኃን ቀርበው ዞኑ በኮማንድ ፖስት ሥር እንዲመራ መታዘዙን ይፋ አድርገው ነበር፡፡

ዞኑ ከኅዳር 15 ቀን ጀምሮ በኮማንድ ፖስት ሥር የወደቀ ሲሆን፣ የክልልነት ጥያቄ ተገን በማድረግ ሕገወጥ እንቅስቃሴ አድርገዋል የተባሉ ሰዎች እየታሰሩ መሆኑ ታውቋል፡፡ በዞኑ ባሉ አንዳንድ ከተሞች መንገድ መዝጋትን ጨምሮ፣ መደበኛ የሕዝብ እንቅስቃሴዎችን አስተጓጉለዋል በሚል በርካቶች እየታሰሩ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ወደ አላስፈላጊ ግጭትና የፖለቲካ ውዝግብ ለምን አመራ? ተብለው የተጠየቁት በዞኑ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የኢንዱስትሪ ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ፣ ሕዝቡ እያደረገ ያለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹ሰላማዊ የሆነውን እንቅስቃሴ ሕገወጥ ነው ብሎ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ሴራ የሚጠነስሰው የመንግሥት አካል ነው ግጭቱን የሚፈልገው፤›› ሲሉ አቶ ብርኃኑ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በጉራጌ ዞን የሚኖሩ ሌሎች ማኅበረሰቦችም ሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት፣ ንብረት ማውደምም ሆነ ሌላ ትንኮሳ ጥያቄውን እያቀረቡ ባሉ ወገኖች አለመካሄዱን የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ፣ ሕዝቡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የክልልነት ጥያቄውን እያቀረበ ስለመሆኑ ተከራክረዋል፡፡

‹‹አቶ ዓለማየሁና ሌሎች የክልሉ የፀጥታ ባለሥልጣናት ግን የታጠቁ ኃይሎች አሉ፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወጣቱም ሆነ ሽማግሌዎችና ሴቶች ጭምር በአመፅ እየተሳተፉ ነው በማለት ከሰዋል፡፡ ይህ ፍፁም የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን ሆን ተብሎ የተቀመረ የፖለቲካ ሴራ ነው›› በማለትም ተችተዋል፡፡ ‹‹የታጠቁና አደገኛ ሰዎች ካሉ ዞኑን የወረሩት የደቡብ ክልል ፀጥታ ኃይሎች ላይ ችግር ይደርስ ነበር እኮ፤›› ሲሉም ሞግተዋል፡፡ ጥያቄውን ከሰላማዊ መንገድ ወደ አመፅና ብጥብጥ እንዲገባ ራሳቸው የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ግፊት እያደረጉ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ሰሞኑን ለሦስተኛ ዙር በተጠራው አድማ ጎማ መቃጠሉንና መንገድ መዘጋቱን አቶ ብርሃኑ አምነዋል፡፡ ‹‹ይህንን ማኅበረሰቡ ፈፅሞ አይደግፈውም፡፡ እኛም ከሰላማዊና ከጨዋው የጉራጌ ሕዝብ ጋር አብሮ የማይሄድ እንቅስቃሴ ነው ብለን አውግዘናል፡፡ ይህ አጋጣሚ ሊከሰት የቻለው ግን በሌላ ሳይሆን፣ የፀጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት እየዞሩ ወጣቶችን ማሰር ስለጀመሩ ነበር፤›› ሲሉ አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ከክልልነት የአደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ወገኖች ጥያቄውን ለራሳቸው የፖለቲካ መገልገያ እያደረጉት ይገኛል ሲል ገልጾ ነበር፡፡ በዚህ የአደረጃጀት ጥያቄ ስም ኢመደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር ሕገወጥ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት እንዳሉም መንግሥት አስታውቋል፡፡  

አሁን ይኼው ውንጀላ በደቡብ ክልል የፀጥታ ባለሥልጣናት እየተንፀባረቀ ሲሆን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ በሰሞኑ መግለጫቸው ይህንኑ አንስተውታል፡፡ በጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ስም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ሕገወጦች የመንግሥት ሠራተኞችና አመራሮች መደበኛ ሥራቸውን እንዳይሠሩ እያስተጓጎሉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ መንገድ መዝጋት፣ ድብደባ መፈጸም፣ ባንዲራ አዘጋጅቶ መስቀል፣ የሥራ ዓድማ ማወጅና ሌላም ሕገወጥ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን አቶ ዓለማየሁ በመግለጫቸው ከሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህንና በመንግሥት የሚቀርቡ ክሶችን የማይቀበሉ አሉ፡፡ ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማኅበር (International Gurage Association-IGA) የተባለው ማኅበር ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት በጉራጌ ሕዝብ ላይ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶችን እየፈጸመ ነው ሲል ከሷል፡፡

ማኅበሩ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የክልልነት ጥያቄያችንን በሰላማዊ መንገድ በመመለስ ፋንታ የጉራጌ አመራሮች፣ አባቶች፣ እናቶችና ወጣቶች ላይ የመብት ጥሰት በፀጥታ ኃይሎች እየተፈጸመ ነው፤›› በማለት የመንግሥትን ዕርምጃ አውግዟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲም ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ፣ በጉራጌ ዞን ያሉ አባሎቼ ላይ እየተካሄደ ነው ያለው እስራት ያሳስበኛል ሲል ገልጾ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የኢዜማን መግለጫ አስመልክቶ ትችት የሰነዘረው ዓለም አቀፉ የጉራጌ ማኅበር በበኩሉ፣ ኢዜማ በመግለጫው አባሎቼ ታሰሩ ቢልም የጉራጌ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄን ግን ሳያነሳ አልፎታል በማለት ወቀሳ አቅርቧል፡፡

‹‹እኔም አንድ የመንግሥት አመራር ነኝ፣ ነገር ግን ያገባኛል በምለው የማኅበረሰብ የመብት ጥያቄ ላይ የነቃ ተሳትፎ አደርጋለሁ፤›› በማለት የተናገሩት አቶ ብርሃኑ፣ ወልቂጤ ላይም ሆነ በሌሎች የዞኑ አካባቢዎች ሕዝቡ ፍፁም ሰላማዊ የሆነ ጥያቄ እያቀረበ መሆኑን ተናግርዋል፡፡

‹‹እኛ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ነው እያቀረብን ያለነው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ደግሞ መንግሥት የራሴ በሚላቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዛሬ አራት ዓመት ኅዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በዞን ምክር ቤት በድምፅ ብልጫ የፀደቀ በመሆኑ፣ እሱ እንዲከበር ነው ሕዝቡ እየጠየቀ የሚገኘው፤›› ሲሉ አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ይህን ለመቀየር ጥናት አስደርጎ የክላስተር አደረጃጀት የሚል የክልል አወቃቀር ይዞ መምጣቱን የሚያስታውሱት አቶ ብርሃኑ፣ ይህንንም የጉራጌ ዞን በመቃወሙ አሁን ወደ ተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ መገባቱን አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት በጉራጌ ዞን ተገኝተው ባሰሙት ንግግር፣ የጉራጌ ማኅበረሰብን ሰላምና ሥራ ወዳድነት አድንቀው ተናግረው ነበር፡፡

‹‹የጉራጌ ባህል ለብልፅግና ቁልፍ ነው፡፡ እነ ቃቄ ወርዶትን ያፈራው የጉራጌ ሕዝብ ሥራና ንግድ ብቻ ሳይሆን ትግልም ያውቅበታል፡፡ በአንድ እጃችሁ እየሠራችሁ በሌላ እጃችሁ ደግሞ የአገራችሁን ሰላም አረጋግጡ፡፡ ኩርፊያና ግጭት በጉራጌ ባህል የሉም ባይባሉም እንኳን፣ ማኅበረሰቡ ለዘመናት ያዳበረው የሽምግልናና ዕርቅ ባህል የሚወደስ በመሆኑ እሱን ተጠቀሙበት፡፡ ጉራጌ የመደመር ምሰሶና ተምሳሌት የሆነ ሕዝብ ነው፤›› በማለት ዓብይ (ዶ/ር) የጉራጌን ማንነትና እሴት አድንቀው ነበር፡፡

በዚህ ደረጃ በአገር መሪ የተወደሰው የጉራጌ ማኅበረሰብ አሁን ወደ ውዝግብ እያመራ ያለውን የክልልነት ጥያቄ በተመለከተ ችግሩን የመፍቻ ጥበብ አያጣም የሚለው እምነት የብዙዎች ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -