Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎና የሕዝብ እንደራሴዎቻችን ነገር

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎና የሕዝብ እንደራሴዎቻችን ነገር

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ዕለቱ ኅዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር፡፡ የኢፌዴሪ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በስድስተኛው ዙር ሁለተኛው የሥራ ዘመን አራተኛ መደበኛ ስብሰባውን ለማካሄድ ተሰይሟል፡፡

ዋነኛው የዕለቱ የመወያያ አጀንዳ ደግሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ከበርካታ ሳምንታት በፊት የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት የጋራ ስብሰባ አድርገውት የነበረውን ዓመታዊ የመክፈቻና የመንግሥታዊ ሥራ ዕቅድና ፕሮግራም ማስተዋወቂያ ንግግር በተመለከተ፣ በእንደራሴዎቹ አማካይነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ተፈላጊውን መልስና ማብራሪያ ለመስጠት ሲሆን፣ ይህንኑ ተግባር ከበቂ በላይ የሆነ ጊዜ ወስደው አከናውነዋል፡፡

ከዚያ ባሻገር በትሕነግና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል ሲካሄድ የቆየውን ድርድርና በአፍሪካ ኅብረት ሸምጋይነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የተኩስ ማቆም ውልም ሆነ የዘላቂ ሰላም ስምምነት ጨምሮ፣ ሌሎች ተዛማጅና ተዛማጅ ያልሆኑ ጉዳዮችን አክለው ሰፊ ሀተታ አቅርበውባቸዋል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያ መድረክ ከተነሱላቸው አያሌ ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹን በሚገባ የመለሱ ሲሆን፣ ሌሎቹን ደግሞ ከአንደኛው ጠርዝ ወደ ሌላው እያንገዋለሉ ያለ ጥልቅ ምርመራ ሲዘሏቸው ተመልክተናል፣ አዳምጠናልም፡፡ ጨርሶ ያልዳሰሷቸው ጥያቄዎችም እኮ ነበሩ፡፡

ሆኖም በዚህ አጭር መጣጥፍ ትኩረት ለማድረግ የምሻው ተዥጎርጉረው በታለፉ፣ ወይም ሀቀኛ ምላሽ ባልተሰጠባቸውና ከናካቴው ባልነካኳቸው ጥቂት ጉዳዮች ላይ ብቻ ይሆናል፡፡ ፈርዶብኝ ቀዳሚ ትኩረቴን የሳበው ታዲያ የወልቃይት ጠገዴና የራያ ዕጣ ፈንታን የሚመለከተው ጉዳይ መሆኑ አልቀረም፡፡

ቀድሞ ነገር ወደ ደቡብ አፍሪካ የተጓዝነው በሰላም ድርድሩ ስም በአወዛጋቢነታቸው የሚታወቁትን እነዚህን አካባቢዎች ለተደራዳሪው ቡድን አሳልፎ ለመስጠት፣ ወይም ለማስረከብ አልነበረም በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተንደረደሩበት የማስተባበያ ምላሽና ማብራሪያ ገና ከጅምሩ እንደተወሰደ አቋም ተደርጎ ተተርጉሞባቸዋል፡፡ ይልቁንም የፌዴራሉ መንግሥት ይህንን የማድረግ መብት ጨርሶ እንደሌለው በአጽንኦት ካስታወሱ በኋላ፣ በተለይ ወልቃይቴ ወትሮውንም ቢሆን የተወላገደ አማርኛ ወይም ትግርኛ ሲናገር የኖረና የራሴ የሚለው ማንነት ያለው ማኅበረሰብ እንጂ፣ የግድ ትግሬ ወይም አማራ ካልሆንክ ተብሎ ሊቀነቀንለት የሚገባ እንዳልሆነ የራሳቸው ድምዳሜ ላይ የደረሱበትን ሐሳብ እንደ አዲስ አስተጋብተዋል፡፡

በእርግጥ የምክር ቤቱ አሠራር ስለማይፈቅድ መሰለኝ፣ የክትትል ጥያቄ በማቅረብ መልሶ የሞገታቸው ሰው ባለመኖሩ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ከልባቸው ይሁን ከኩላሊታቸው በውል ለመረዳት ያዳግታል፡፡ አንድ ጥሬ ሀቅ ግን ተፈናጥሮ እንደ ወጣባቸው የሚያከራክር ሆኖ አልተገኘም፡፡

ያ ንግግራቸው የወልቃይት ጠገዴና የሰቲት ሁመራ ነዋሪ ሕዝብ ለማንነት ነክ ውዝግብ እንደተዳረገ መቀጠሉ ቀርቶ፣ ተጠሪነቱ ለአማራም ሆነ ለትግራይ ክልል ሳይሆን ለፌዴራሉ መንግሥት ሆኖ እንዲተዳደር በህቡዕ መታቀዱን አመላካች ተደርጎ ተወስዶባቸዋል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥቱ መልዕክተኞች መካከል ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በፕሪቶሪያ በተፈረመው የሰላም ስምምነት ውስጥ በየትኛውም ሥፍራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተካቶ አናገኘውም፡፡ ከዚያ ይልቅ የስምምነት ማዕቀፉ በአንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ 4 ሥር የደነገገው የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውና ሁለቱን አጎራባች ክልሎች የሚያነታርኩት የትኛዎቹም ግዛቶች፣ በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሠረት ታይተው አስተዳደራዊ መፍትሔ የሚሰጥባቸው ስለመሆኑ ብቻ ነው፡፡

ይህ በራሱ ምን ማለት እንደሆነ በሰፊው ሊያወያይና ሊያከራክር ቢችልም፣ ቢያንስ ግን በምክር ቤቱ ፊት እሳቸው እንዳቀረቡት ወልቃይት ራሱን ችሎ እንደሚደራጅና ለፌዴራሉ መንግሥት እንደሚጠራ ከወዲሁ የሚጠቁም አንድምታ የለውም፡፡ ያንን በማድረግም ለችግሩ ፍትሐዊ መፍትሔ ላይ መድረስ የሚቻል መስሎ ከወዲሁ አይታይም፡፡

በመሠረቱ የፌዴራሉ መንግሥት አካባቢውን ለትግራይ ክልል የመመለስ መብት እንደሌለው ሁሉ፣ ለእኔ ይጠራና ራሴ በማዕከላዊነት ላስተዳድረው እስከ ማለት የሚዘልቅ መብትም አይኖረውም፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አሁን በሥራ ላይ ያለው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ከመውጣቱ በፊት፣ በሕወሓት የአገዛዝ ቀንበር ሥር ወድቆ በማንነቱ ያላግባብ ሲገፋ፣ ሲታሰር፣ ሲሳደድ፣ ሲገደልና ከቀዬው ሲፈናቀል የኖረ ሕዝብ መሆኑን ለመካድ ያልደፈሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መሬቱ ቅድመ ሕገ መንግሥት በኃይልና በግፍ እንደተወሰደበት ቢያምኑም፣ በጊዜው ስህተት ነበር ያሉት ይህ ዓይነቱ የጉልበተኞች ዕርምጃ ግን በሌላው ወገን ጊዜ ተጠብቆ ይደገም ዘንድ ፈጽሞ እንደማይፈልጉ በአደባባይ ነግረውናል፡፡

እንደ እሳቸው የሥጋት አስተያየት ከሆነ እንዲህ ያለው የተረኝነት ዕርምጃ ማለቂያ ለሌለውና ለማያባራ የእርስ በርስ ግጭትና ደም መፋሰስ ይዳርገን እንደሆነ ነው እንጂ፣ በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን ሊያረጋግጥ ስለማይችል የተሻለ አማራጭ የሚሆነው በዳይና ተበዳይን አቀራርቦ በማደራደር ለተራዘመው ውዝግብ ዓይነተኛ መቋጫ ማበጀት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ ሰለባዎቹ በማያምኑበትና ለጉዳዩ አግባብነት በሌለው ሕገ መንግሥት መሠረት ውዝግቡ እንዴት ሊዳኝ እንደሚችል በውል አላስረዱንም፣ ሊያስረዱን የሚችሉም አይመስለኝም፡፡

ከሰላም ድርድሩ ጋር በተያያዘ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባደረጉት ገለጻ በጨረፍታም ቢሆን ያነሱት ሌላው ነጥብ፣ በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር የመወያየቱን ተገቢነት ወይም ኢተገቢነት የሚመለከተው ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ተደጋግሞ የሚሰነዘርባቸውን ትችትና ወቀሳ ያጣጣሉት ዶ/ር ዓብይ ሕጉን የራሳቸው ካቢኔ እንዳላመነጨው ሁሉ፣ ‹‹ያወጣችሁት ሕግ ከአሸባሪ ጋር አትተባበሩ ነው እንጂ አትደራደሩ አይልም፤›› ሲሉ በመሸርደድ፣ የሕግ አውጪ አካሉን አባላት መክረው ላወጡት አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ዓ.ም. ሳይቀር የሩቅ ባይተዋሮች አስመስለዋቸዋል፡፡

የተከበሩት እንደራሴዎች ግን በምላሹ የተስማሙ በሚመስል ሁኔታ ሳቅና ጭብጨባውን ሲያቀልጡት አስተውለናል፡፡ ሕግ በዋነኝነት ከሞራል ፍልስፍና የሚቀዳ እንደ መሆኑ መጠን፣ አስቀድሞ በሽብርተኝነት የተፈረጀውን ቡድን ለምክር ቤቱ አቅርቦ ቅድመ ድርድር ፍረጃውን ማስነሳት እንደሚገባ እንኳ ከወዲሁ አምኖ ለመቀበል አላስፈለጋቸውም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የአርበኛ ዘመነ ካሴ ጉዳይ በተለይ ተጠቅሶ ራሱ መንግሥት አስቀድሞ በሚያውቀውና በፈቀደው አግባብ በአካባቢው ተቀባይነት ያለውን የሽምግልና እሴት ተጠቅመን ሰውየውን ብናቀራርበውም፣ ይህ በጎ ጥረታችን ወደ ጎን ተትቶ ባልተጠበቀ ሁኔታ ላልተገባ እስር መዳረጉ እንደምን ለሰላም መስፈን ያግዛል? እንዲህ ያለው ዕርምጃስ የተከበሩትን የአገር ሽምግልና እሴቶች መናድና መሸርሸር አይሆንምን? የሚል ሌላ ፈታኝ ጥያቄ በምዕራብ ጎጃም ዞን የጅጋ ምርጫ ክልልን ከሚወክሉ አንድ እንደራሴ በኩል ቀርቦላቸው ነበር፡፡

ሆኖም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ወደፊትም ቢሆን ለሰላም የምታደርጉትን ይህንን ዓይነቱን ጥረት ብትቀጥሉበት የሚታሰር ዜጋ አይኖርምና ግፉበት፤›› ሲሉ ጥያቄውን ያቀረቡትን ንቁ የሕዝብ እንደራሴ በመሸንገል ብቻ ያላንዳች ውል ያለው ምላሽና ማብራሪያ ማለፋቸው ይበልጡኑ አስገርሞኛል፡፡

ለመሆኑ ከመንግሥት አቅም በላይ የሆነ እስኪመስል ድረስ እንዳሻው ለሚፈነጨውና ንፁኃን አማሮችንና ለዘብተኛ ኦሮሞዎችን ያለ ከልካይ በግፍ ለሚጨፈጭፈው ለኦነግ ሸኔ ትጥቅና ስንቅ የሚያቀርብለት ማነው? ለሚለው የሌላዋ ሴት እንደራሴ ቁልፍ ጥያቄም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት አንዳች ረብ ያለው ምላሽ አልነበረም፡፡

‹‹የሸኔ ነገር እንኳን ለእኛ ለጋላቢዎቹም የበረታ እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል፤›› በማለት ነበር ጥያቄውን እንደ ዋዛ ከአግራሞት ጋር የዘለሉት፡፡

በመሠረቱ ከሰዎች ተፈጥሯዊ እኩልነት ባሻገር የአገሪቱ ዜጎች ሁሉ በየትኛውም አካባቢ ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ እኩልና ያልተሸራረፈ ሕጋዊ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ በየትኛውም እርከን የተደራጀ መንግሥታዊ መዋቅር ቀዳሚና ተኪ የለሽ ኃላፊነቱ ነው፡፡

ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራቸው ኮርተውና መንግሥታዊ ጥበቃን ተማምነው በሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች እየተሳፈሩ ከሰሜኑ የአገራችን ክፍል ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለመግባት የሞከሩ በርካታ መንገደኞች፣ በብሔራዊ ማንነታቸውና በሚናገሩት የአፍ መፍቻ ቋንቋ ብቻ እየተመረጡና የነዋሪነት መታወቂያቸው እየታየ ጉዟቸውን አቋርጠው ወደኋላ እንዲመለሱ በኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ኃይሎች አማካይነት ስለሚገደዱበትና ያላግባብ ስለሚንገላቱበት ሕገወጥና ዓይን ያወጣ ዕርምጃ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት የአገም ጠቀም ማብራሪያ የምር እንዳሳዘነኝና ተስፋ እንዳስቆረጠኝ ፈጽሞ ለመደበቅ አልፈልግም፡፡

ከዚሁ ስሞታ ጋር በተገናኘ የአዲስ አበባ ሰላምና ደኅንነት ይጠበቅ ዘንድ ንፁኃን ወገኖች በፍተሻ ስም፣ ለሁለትና ለሦስት ቀናት ወደ መዲናይቱ ድርሽ እንዳይሉ በአቅራቢያ ኬላዎች ላይ በጅምላ መታገዳቸውና ጉዟቸው እንዲስተጓጎል እየተደረገ አውላላ ሜዳ ላይ የሚፈሱበትንና ከፍተኛ ዋይታ የሚያሰሙበትን አደገኛ ዕርምጃ ለአገር ደኅንነት እንደተከፈለ ዋጋ ሊቆጥሩት ይገባል ብለውናል፡፡

እኔ በበኩሌ ይህንን ዓይነቱን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ እንደለየለት ሹፈት ነው የምቆጥረው፡፡ ምናልባትም ይህ ዓይነቱ ኃላፊነት የጎደለው አመላለስ ነው እንግዲህ፣ በሕግ ማስከበር ስም እንንቀሳቀሳለን የሚሉትን ሕግ ተላላፊዎች የልብ ልብ የሚሰጣቸውና ባፈነገጠው ዕርምጃቸው እንዲገፉበት የሚያበረታታቸው፡፡

እስካሁን በለሆሳስ ስለሚወሳለት የጫካ ፕሮጀክትም ቢሆን በመጠኑ ዘርዘር አድርገው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነገሩን በዚህኛው የፓርላማ ቆይታቸው ነበር፡፡ ይህንኑ በተመለከተ ለሕዝብ እንደራሴዎቹ ሲያብራሩላቸው እንደተከታተልነው ከሆነ፣ 49 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ሲባልለት የሰማነው ይህ አስደማሚ ፕሮጀክት አምስት መቶ ቢሊዮን ብር እንኳ ቅም እንደማይለው ዕቅጩን ተናግረው የሞቀውን የጓዳ ሹክሹክታ አቀዝቅዘውታል፡፡

በርካታ ዜጎችን ከየመኖሪያ ቤቶቻቸው ያፈናቅላል ተብሎ ክፉኛ የተሠጋበት የሳተላይት ከተማ፣ በእሳቸው አገላለጽ መሠረት ለብዙ ወገኖች የሥራ ዕድል የመፍጠርና ዳጎስ ያለ ብሔራዊ ገቢ የማመንጨት አቅም ያለው ፕሮጀክት ነው፡፡

ያም ቢሆን ታዲያ የሩቅ ህልመኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ገና ግልጽ ያላደረጉልን ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም አብዝተው የሚረገረጉለትን ግዙፍ ፕሮጀክት በመሬት ላይ ዕውን ለማድረግ ወረቱን ያገኙት ከማንና ከየትኛው ምንጭ እንደሆነ በትክክል አለመታወቁ ነው፡፡

አሁን ለያዙት ከፍተኛ ኃላፊነት ገና እንደተሾሙ ሥራቸውን በብቃትና በታማኝነት ለማከናወን በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ የፈጸሙበትና ሕዝባዊ አደራ የተቀበሉበት የእገሪቱ ሕገ መንግሥት ደግሞ፣ በአንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 1 ሥር የመንግሥታቸውን አሥራር ግልጽነትና እሳቸውን ጨምሮ የባለሥልጣኖቻቸውን ተጠያቂነት አጽንኦት ሰጥቶ ይደነግጋል፡፡

በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰፊ ጊዜ ወስደው የሚያስጎመጅ ማብራሪያ በመስጠት ሲደክሙ ያረፈዱት፣ ምክር ቤቱ ጨርሶ ስለማያውቀውና ዝርዝር ዕቅዱንም ሆነ የማስፈጸሚያ በጀቱን አስቀድሞ ስላላፀደቀለት ወደር የለሽ ፕሮጀክታቸው ነበር ለማለት ይቻላል፡፡

ከፍ ብሎ ለተጠቀሰው ለዚሁ አነጋጋሪ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ ከውጭ በጎ አድራጊ ወገኖች የተቀበሉት አንዳች ድጋፍ ቢኖር እንኳ በመንግሥት ስም ታውቆና በሚገባ ተመዝግቦ በጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል እንጂ፣ ዕርዳታ ወይም ስጦታ ነው ስለተባለ ብቻ የአገሪቱ ሕግ ከሚፈቅደው አሠራር ውጪ ገቢ ሆኖ በሥራ ላይ እንደማይውል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይጠፋቸዋል ተብሎ አይገመትም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የተደራጀ ሌብነትንና ከቀን ወደ ቀን ለከት እያጣ የመጣውን መንግሥታዊ ዝርፊያ አስመልክቶ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ያመረሩ መስለው ታይተዋል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ለጊዜው እሳት የሚያጠፋ ኮሚቴ ማቋቋምም ሆነ ግብረ ኃይል መሰየም በአገራችን ያን ያህል እንግዳና ያልተለመደ ነገር እንዳልሆነ በሚገባ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ በውስን ቁመናና በተዳከመ አቅም የሚንከላወሰውን የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንደ ተቋም የሚያጠናክር ብሔራዊ ኮሚቴ እስከ መሰየም መድረሳቸውን፣ በመንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ ከላይ እስከ ታች በሰፊው ተንሰራፍቶ የሚታየውን ሙስናና ብልሹ አሠራር አምርረው ለመዋጋት መወሰናቸውን ለሕግ አውጪ አካላቱ በይፋ ማሳወቃቸውና የዜጎችን ያላሰለሰ ድጋፍ መጠየቃቸው በበኩሌ የሚበረታታ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

በግብር ላይ ካላዋሉት ደግሞ በቃላቸው መሠረት ነገ ከነገ ወዲያ ጠብቀን ስለምንይዛቸው፣ ይህንን ውሳኔያቸውንና ያለ ቅጥ እየገነገነ ከመጣው ዘርፈ ብዙ ችግር ጋር በተያያዘ ያደረጉትን ገለጻ ከወዲሁ ባናጣጥለው መልካም ነው፡፡

እዚህ ላይ የዶ/ር ትዕግሥትንና የአፈ ጉባዔውን እሰጥ አገባ ሳላነሳ መጣጥፌን ልቋጨው አልወደድኩም፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተወከሉት እኝህ የሕዝብ እንደራሴ፣ የመዲናዋን ፖለቲካዊ አቋም በተመለከተና አቀራረቡ የእንደራሴዋን ግላዊ ነፃነት በሚያጋልጥ ብርቱ ጥያቄ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲያፋጥጧቸው ታዝቤያለሁ፡፡ ጠቅላዩ ግን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ ዙሪያ መለስ መሽከርከሩን የመረጡ መስለው ታይተዋል፡፡

‹‹በዚህ ምክር ቤት አሠራር የተዛነፈ አካሄድ አለ›› ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲያሰሙ የተመለከትናቸው የሕዝብ እንደራሴ፣ የስብሰባውን ዓውድ በመጠኑም ቢሆን ቀይረውታል ለማለት ያስደፍራል፡፡

እንደራሴዋ ከተከበሩ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ከአቶ ታገሰ ጫፎ ጋር ያደረጉት ምልልስ ፍሬ አስገኝቶ ይናገሩ ዘንድ ከተፈቀደላቸው በኋላም፣ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣ ያሉና ተደራራቢ ጥያቄዎችን አቅርበውላቸው ነበር፡፡

ለገጣፎና አዲስ አበባ በቆዳ ስፋትና በሕዝብ ብዛት ዝሆንና ትንኝ ናቸው በሚል ድምፀት ፓርላማውን ትንሽ ፈገግ ያሰኙት ንቁ የሕዝብ እንደራሴ፣ ‹‹ሁለቱም በአንድ ዓይነት አጠራር የከተማ አስተዳደሮች መባላቸው ያመናልና ለመሆኑ አዲስ አበባ የማን ናት? እኔስ የማን ነኝ?›› በሚሉ ጥያቄዎች ሳይወሰኑ የመዲናዋን መፃኢ ዕጣ ፈንታ በተመለከተ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንደሚያሻቸው አመልክተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሳይቀር ፖለቲካዊ ውክልና የሚያገኙበት ዕድል አለመኖሩን ሲያስቡ፣ አብዝቶ እንደሚያስጨንቃቸው ሞግተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ግን የእንደራሴዋን ማንነት በዕጩነት ከመለመላቸውና ለምክር ቤቱ ወንበር ካወዳደራቸው የፖለቲካ ድርጅት ጋር አቆራኝቶ ከመተቸት የዘለለ ባለመሆኑ፣ “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” ሆኖ ነበር እስከ መጨረሻው ድረስ የተከታተልነው፡፡

‹‹በመሠረቱ ፓርቲዎን እንጂ እርስዎን በግል ማን ያውቅዎታል?›› ተብለው በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሳሳተ አመላለስ በአደባባይ የተወረፉ ጊዜ የተሸማቀቅንባቸው እንደራሴ፣ ያለ ጥርጥር ላወዳደራቸው ፓርቲና እሱ ለቀረፀው ፖሊሲም ሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም ምንጊዜም ቢሆን ታምኖ መገኘት ይጠበቅባቸው ይሆናል፡፡ አንድ ጊዜ በሕዝብ ተመርጠው የምክር ቤቱን መቀመጫ ከተረከቡ በኋላ ግን፣ ተጠሪነታቸው ለመራጩ ሕዝብ፣ ለሕገ መንግሥቱና ለራሳቸው ህሊና እንደሆነ መዘንጋት ባልተገባ ነበር እላለሁ፡፡

በመጨረሻም ይህ ጸሐፊ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የግል ጠብ የለውም፡፡ ይልቁንም አሁን ወደ ያዙት ከፍተኛ የኃላፊነት ማማ ከመውጣታቸው በፊት በአካል ከማወቅ አልፎ፣ ለፈጣን አዕምሯቸውም ሆነ ለተባው አንደበታቸው ላቅ ያለ ክብርና አድናቆት አለው፡፡ ይህንንም አቋሙን በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች ከመግለጽ ቦዝኖ አያውቅም፡፡

መሪያችን በአገርና በሕዝብ ባላደራነታቸው እስከ ቀጠሉ ድረስ አልፎ አልፎ መመከርና መስተካከል አለባቸው ብሎ ሲያስብ ግን፣ እስከ ዛሬ ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ በአመክንዮ የተደገፈ ሂስ ከመሰንዘር ወደኋላ አይልም፡፡

ለዛሬው እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ካገኙ በኋላ፣  በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው ለበርካታ ዓመታት አገልግለው በቅርቡ በክብር የተሰናበቱ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው clickmerha1@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...