ሕፃናት በለጋ ዕድሜያቸው አዕምሯቸው እንዲዳብር ማንበብ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ዜጎች ዕውቀት፣ ብልኃት፣ ሥልት፣ ዘዴና ችሎታ እንዲኖራቸው ማንበብ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ይነገራል፡፡ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ የጎለበተ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ዜጎች እንዲያነቡ የተለያዩ ሥልቶች ሲያዘጋጁ ይስተዋላል፡፡ አንዳንዶች በቅርብ ርቀት ላይ ቤተ መጻሕፍትን በመገንባት ሌሎች ደግሞ የመጻሕፍት ንባብ ውድድር በማዘጋጀት፣ ዜጎቻቸው የተሻለ ዕውቀት እንዲይዙና ክህሎት እንዲኖራቸው ያደርጋሉ፡፡ በኢትዮጵያ በተቋም ደረጃ ንባብን ለማበረታታት በርካታ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ድርጅቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ሕያው ፍቅር ለኢትዮጵያ ፕሮሞሽንና ኢንተርቴይመንት አንዱ ነው፡፡ አቶ ሰለሞን ደርቤ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የድርጅቱን እንቅስቃሴ በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የንባብ አብዮት ለትውልድ ኢትዮጵያ ምን ማለት ነው?
አቶ ሰለሞን፡- የንባብ አብዮት ለትውልድ ኢትዮጵያ የተባለበት ምክንያት አንባቢ ትውልድ እየጠፋ በመምጣቱ የተነሳ ነው፡፡ በተለይም ከዚህ በፊት ንባብ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ እያዘነበሉ በመሄዳቸው ችግሩ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች አንፃር ስትታይ ከማያነቡ አገሮች ተርታ መመደቧ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ትምህርት ቤቶች ላይ አንባቢ ትውልድ ባለመፈጠሩ ‹‹የንባብ አብዮት ለትውልድ›› ኢትዮጵያን በሚል ስያሜ ወደ ሥራ ልንገባ ችለናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕፃናትና ልጆች ላይ የተሠራ ሥራ ባለመኖሩ አንባቢ ትውልድ ልናጣ ችለናል፡፡ ሕፃናት ልጆች ገና ከለጋ ዕድሜያቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ሰለባ በመሆናቸው በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ተቸግረናል፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመሄድ ቢያንስ በቀን ለ15 ደቂቃ እንዲያነቡ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተረፈ በቀጣይ የመጽሐፍ ዓውደ ርዕይ ለማካሄድ ዕቅዶችን ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ይኼንንም ሥራ ተማሪዎች ክረምት ላይ ዕረፍት ሲወጡ ተግባራዊ የምናደርግ ይሆናል፡፡ ይኼ ከሆነ በተወሰነ መልኩም ቢሆን አንባቢ ትውልድ መፍጠር ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- አብዛኛውን ጊዜ የንባብ ክህሎትን ከማሳደግ አኳያ በርካታ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ተቋሙ ይህንን ችግር ለመታደግ ምን እየሠራ ይገኛል?
አቶ ሰለሞን፡- እንዳልከው በኢትዮጵያ የንባብ ክህሎትን ከማሳደግ አኳያ በርካታ ተግዳሮቶች አሉ ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም አንባቢ ትውልድ ከመፍጠር አኳያ በርካታ ችግሮች ይታያሉ፡፡ በትምህርት ቤቶች ላይም የኦንላይን (በይነ መረብ) ትምህርት መፈጠሩ አንባቢ ትውልድን እየገደለ ይገኛል፡፡ በዚህም የተነሳ በተለያዩ ቦታዎች ላይም የመጽሐፍ ዓውደ ራዕይ በማዘጋጀት ወጣቶችን የንባብ ልምዳቸውን እንዲያሳድጉ መንገድ ለመክፈት ዕቅድ ይዘን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ በዚህ መንገድ መጓዝ ከተቻለ አብዛኛውን ትውልድ የንባብ ልምድ እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ከንባብ ክህሎት ጋር ተያይዞ ከሌሎች አገሮች ተርታ እንድትመደብ ትልቅ አማራጭ ይኖራታል ተብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- የንባብ አብዮቱ በምን ያህል ትምህርት ቤቶች ላይ ተደራሽ ለመሆን አስቧል? በየትኛው የዕድሜ ክልል ላይ ለሚገኙ ሰዎችስ ተደራሽ ትሆናላችሁ?
አቶ ሰለሞን፡- በዚህ ዓመት ስፖንሰር የሚያደርገን ተቋም ካገኘን በርካታ ትምህርት ቤቶች ላይ ተደራሽ ለመሆን አስበናል፡፡ ነገር ግን ተቋማችን እንደ ፕሮጀክት ይዞ እየተንቀሳቀሰ ያለው ፈር ቀዳጅ የሆኑ ትምህርት ቤቶች ላይ ለአንድ ወር የሚቆይ የንባብ አብዮት ለማከናወን አቅዶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአንድ ወር ውስጥም ሃያ ትምህርት ቤቶች ላይ ተደራሽ ለመሆን ዕቅድ ይዘናል፡፡ የዕድሜ ክልል ላልከኝ ሁሉንም የዕድሜ ክልል ያማከሉ ሥራዎችን የምንሠራ ይሆናል፡፡ ሕፃናትና ልጆችን ዕድሜያቸውን በሚመጥን መልኩ የተዘጋጁ መጽሐፎችን እንዲያነቡ ይዳርጋል፡፡ በተለይም ልጆች በለጋ ዕድሜያቸው የማንበብ ክህሎት እንዲኖራቸው ይኼ ፕሮግራም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በቀጣይም የንባብ አብዮት ፕሮግራሞችን ቀርጾ በመንቀሳቀስ የንባብ ባህልን እንዲዳብር የምናደርግ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ከሌሎች ተቋሞች ጋር በቅንጅት ለመሥራት ምን አስባችኋል?
አቶ ሰለሞን፡- እንደ መጀመርያ ዕቅድ እዚህ ላይ ብዙ ሠርተናል ማለት ይቸግራል፡፡ የዚህ ፕሮግራምም ዋና ዓላማ የማንበብ ክህሎትን ከማሳደግ ባለፈ፣ ንባብን እንዲለመድ ያደረጉ ትምህርት ቤቶችን ዕውቅና መስጠት ይሆናል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዳግማዊ ሚኒልክ፣ ቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት፣ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ይገኙበታል፡፡ በእነዚህም ትምህርት ቤቶች የወጡ በርካታ ምሁራን በመኖራቸው ዕውቅና ልንሰጥ ዕቅድ ይዘናል፡፡ ይህም ፕሮግራም ቀጣይነት ባለው መልኩ በማስቀጠል የንባብ ክህሎትን እንዲያድግ የምናደርግ ይሆናል፡፡ ይህንን ከሠራን በኋላ ከሌሎች ተቋሞች ጋር ለመሥራት የምንሯሯጥ ይሆናል፡፡ ተቋሙም ከዚህም በፊት በማኅበራዊና በተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ያዘጋጀ ሲሆን፣ በተለይ የመጀመርያው ባለ ቀለም ፊልም ጉማን የሠራው ሚሽን ፓፓቲኪለን ውለታ የሚይሳይ ፕሮግራም አዘጋጅተን ሽልማት ሰጥተናል፡፡
ሪፖርተር፡- በቂ የማንበቢያ ቤተ መጻሕፍት ባለመኖራቸው የተነሳ አብዛኛው ማኅበረሰብ ሲቸገር ይታያል፣ ችግሩን እንዴት ያዩታል?
አቶ ሰለሞን፡- በእርግጥ ይህ ችግር መኖሩ በራሱ በርካታ ወጣቶችም ሆኑ አንባቢያን ማኅበረሰብ ሲቸገሩ ይታያል ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በቅርቡ በዚህ ነገር ላይ የተሠሩ ሥራዎች በመኖራቸው የችግሩ አሳሳቢነት ጎልቶ ይታያል ማለት ይቸግራል፡፡ በዚህ ጉዳይ በግለሰብ ደረጃ ራሱ የሚሠሩ ሰዎች ቁጥራቸው ከፍተኛ ስለሆነ የማንበቢያ ቦታ እጥረት አለ ብሎ ማሰብ ትንሽ ከበድ ይላል፡፡ ነገር ግን እንደ አገር አንባቢ ትውልድ ተፈጥሯል ብሎ ለማሰብ ግን ብዙ ይቀረናል፡፡ አንባቢ ትውልድን ከመፍጠር አኳያም በመንግሥት ደረጃ ራሱ ምንም ዓይነት ሥራ አልተሠራም ማለት ይቻላል፡፡ ተቋሙም በቀጣይ እንዲህ ዓይነት ሥራዎች ላይ በመግባት የንባብ ልምድ እንዲያዳብር የሚሠራ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ክልሎች ላይ ተደራሽ ለመሆን ምን ዕቅድ ይዛችኋል?
አቶ ሰለሞን፡- ቅድም እንዳልኩህ እንደ መጀመርያ ሥራችን ክልሎች ላይ ተደራሽ ለመሆን ያሰብነው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ስፖንሰር የሚያደርግ ተቋም ባለማግኘታችን የተነሳ ክልሎችን መድረስ አዳጋች ያደርገናል፡፡ በተለይም አብዛኛዎቹ ተቋሞች ለእንዲህ ዓይነት ሥራዎች ላይ ስፖንሰር ሲያደርጉ ባለመታየቱ ችግሩን ይበልጥ አጉልቶታል፡፡ ይህንንም ለማዘጋጀት የበርካታ ተቋሞችን በር አንኳኩተናል፡፡ ነገር ግን ያገኘው ምላሽ እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ክልሎች ላይ ለመድረስ ተቸግረናል፡፡
ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?
አቶ ሰለሞን፡- በቀጣይ ለአንድ ወር ያዘጋጀውን ፕሮግራም ወጥ በሆነ መልኩ በመሥራት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ለማድረግ ዕቅድ ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ታዋቂ ግለሰቦችን በመፈለግ የተለያዩ ሥራዎች የምንሠራ ይሆናል፡፡ በተለይም ደግሞ አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር ግንዛቤ የምንሰጥበት መንገድ የምናመቻች ይሆናል፡፡ ይህ ከሆነ አገር ወዳድ ትውልድን መፍጠር ይቻላል፡፡