የራሳቸው የፊደል ገበታ ካላቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ለጽሕፈትም ሆነ ለሥነ ጽሑፍ መሠረት የሆነው ፊደል ከአክሱም ዘመን ጀምሮ በድንጋይ ላይ በመቀጠልም በብራና ላይ በግእዝ ቋንቋ እየተጻፈ እስከዚህ ዘመን ደርሷል፡፡
ፊደል የሚለው ቃል “ፈደለ” ጻፈ፣ ፈጠረ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ መሆኑ መዛግብተ ቃላቱ ይገልጻሉ፡፡ ፊደል በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ አገላለጽ ምልክት፣ አምሳል፣ የድምፅና የቃል መልክ ሥዕል፣ መግለጫ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በተለይ በዋናነት የሚጠቀሰው የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ሲሆን፣ በተከታታይ ዘመናትም እነ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ኦሮምኛና ሌሎችም ቋንቋዎች የየራሳቸው ሥነ ጽሑፍን የግእዙን የፊደል ገበታን መሠረት አድርገው አዘጋጅተዋል፡፡
ከሦስት አሠርታት ወዲህ ኦሮምኛን ጨምሮ የተለያዩ ቋንቋዎች የላቲኑን የፊደል ገበታ መጠቀም መጀመራቸውም ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ መገለጫ የሆነውን የግእዙ የፊደል ገበታን ለማክበር ያሰበ አንድ መሰናዶ መሰንበቻውን በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዶ ነበር፡፡
‹‹ዝክረ ፊደል›› በሚል በራስ ሆቴል በተዘጋጀው የፊደል ቀን “ኢትዮፒክ” እየተባለ በውጭ ዓለም ይበልጥ ስለሚታወቀው የግእዝ የፊደል ገበታ አስመልክቶ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡ ስለአገራዊው በመድረኩ ላይ ፊደል ታሪክ ያቀረቡት አየለ በከሪ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ምሁሩ ‘Ethiopic, An African Writing System: Its History and Principles’ የተሰኘ መጽሐፍ ያሳተሙ ናቸው፡፡
የግእዝ ወይም ኢትዮፒክ የሚባለው ፊደል ከታላላቅ ፈጠራዎች አንዱ ነው ያሉት አየለ (ዶ/ር)፣ ገለታው አናባቢና ተነባቢን አጣምሮ የያዘ ቀለማዊ ፊደል ነው ብለውታል፡፡ የፊደል አመጣጥ ታሪክን በተመለከተም ያነሱት ነጥብ አለ፡፡ ‹‹ፊደል የመጣው ከሳውዲ ዓረቢያ ነው›› የሚሉ ጸሐፊዎች መኖራቸውን ለአብነትም ያህል ሲልቪያ ፓንክረስትን አንዷ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
እንደ አየለ (ዶ/ር) ገለጻ ከሆነ ግን ‹‹ፊደል›› የመጣው ከሳውዲ ዓረቢያ የሚለው ማስረጃ የለውም፡፡ የታሪክና የአርኪዮሎጂ ግኝቶች በአብዛኛው እንደሚያመለክቱት በሳውዲ ዓረቢያ የነበረ ሥልጣኔ የኢትዮጵያ አካል የነበረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
በትግራይ ውቅሮ (መቃብር ጋውዓ) ላይ የተገኙ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች መኖራቸውን እነዚህም ጽሑፎች እውነቱን የሚያሳዩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በተለይም ከአክሱም በቅርብ ርቀት በሚገኝ አካባቢ ላይ የተደረገ ጥናት የሚያሳየው በግእዝና በግሪክ ፊደሎች የተጻፉ መገኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡
በውቅሮም በተደረገው ጥናት የተገኙ ፊደሎችን በመንከባከብ ጀርመኖች ራሳቸው እዚያው ቦታ ላይ ሙዚየም ከፍተው ማኅበረሰቡ እንዲገነዘበው እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ፊደል በምናጠናበት ጊዜ አብዛኛዎቹ ነገሮች ልናገኝ የምንችለው ስለኑቢያ፣ ኤዥያና ስለግብፃውያን ሥልጣኔ በምንመራመርበት ጊዜ ነው ይላሉ፡፡
ከዚህ ቀደም ‹‹መ›› በሳቢያን፣ ፕሮቶ ኢትዮፒክ በሚባለው ላይ ቆሞ የተጻፈ እንደነበር፣ በወቅቱም ይህ የአጻጻፍ ስታይል በየትኛውም መንገድ መነበብ እንዳለበት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ ከአኃዝ ቁጥር ጋር ተያይዞ ውይይት መደረጉን በውይይቱም የ‹‹መ›› ፊደል ራሱ እንደ አኃዝ ቁጥር ነው የሚሉ ተመራማሪዎች እንደነበሩ አብራርተዋል፡፡
ግእዝ ላይ ሀ ሁ ሂ ሀ ሄ ህ ሆ መኖሩን አብዛኛውን ሰው የሚጠቀመው ሀ ብሎ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህም ትክክለኛ አረዳድ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
በግዕዝ ቋንቋ ያሉ ድምፆች በሙሉ ካልቸር ለማድረግ ሰባት የድምፅ ክፍፍል መኖሩን ነገር ግን ዋናዎች ተዋናዮች ሃያ ስድስት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከሀ እስከ ፐ የፊደል ገበታ ዐረፍተ ነገር የሚሠራባቸው ቢሆንም ፐ ፑ ፒ ፓ ፔ ፕ ፖ ባሉት ሰባት ድምፆች ግን የኢትዮጵያን ቃል ተጠቅሞ ዐረፍተ ነገር መሥራት እንደማይችል ተናግረዋል፡፡
በአክሱም አካባቢም አንድ አርሶ አደር ያገኘው በሦስት ዓይነት የተጻፈ ትክል ድንጋይ መኖሩን የተናገሩት አየለ (ዶ/ር) ይህንንም በአግባቡ ተቀምጦ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፊደል 182 ሆሄያት ወይም ፊደላት (26×7) እንዳለው በኢትዮጵያ አቆጣጠርም የዓመት አጋማሽ 182 መሆኑንና ግንኙነት ጭምር እንዳለው አስረድተዋል፡፡
መነሻው ሀ ቢሆንም መድረሻው ላይ አሁንም ቢሆን ሙግት እንዳለ አንዳንዶች ከሀ እስከ ፐ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ከሀ እስከ ተ ነው የሚሉ ጭምር እንዳሉ ያስረዳሉ፡፡
በኤዥያና በግብፃውያን አካሄድ ሀ የተባለችው ፊደል በአንበሳ ፊት የተገለጸች ሲሆን፣ ተ ደግሞ በጭራው መሆኑን ገልጸው፣ በእነዚህም ሁለት አገሮች የመጨረሻው ፊደል ማሰሪያ መሆኑን ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአማርኛም ሆነ በግዕዝ በፐ ምንም ዓይነት ቃል እንደሌለ ከውጭ የወሰድናቸው ቃላት መኖራቸውን ጠቅሰው አብዛኛዎቹ አኃዞች በፊደል ውስጥ መኖራቸውን፣ እነዚህም አኃዞች ከፊደሉ ለመለየት ከላይና ከታች ሰረዝ ይደረግባቸዋል ብለዋል፡፡
አብዛኛዎቹን ፊደሎች የራሳቸው መልዕክት እንዳላቸው፣ ለምሳሌ ያህል ‹‹የ››ን ብንወስድ 100 ሲሆን፣ ሲገለበጥ ደግሞ አንድ ቁጥር እንደሚሆን፣ ‹‹ገ›› ደግሞ በሁለት አቅጣጫዎች ተንተርሶ የተጻፈ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አየለ በክሬ (ዶ/ር) ገለጻ ከሆነ፣ የአርሜንያን ፊደል ከኢትዮጵያ ፊደል ጋር ልዩነት እንደሌለው፣ ነገር ግን እነሱ ፊደላቸውን ገልብጠው እንደሚጠቀሙ፣ ይህንንም በአንድ ወቅት ጥናት ባደረጉ ጊዜ ማየታቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ፊደሎች የተወሰዱት ከግእዝ መሆኑን፣ ይህም ምንም ዓይነት ጥያቄ እንደማያስነሳ አስምረውበታል፡፡
በሌላ በኩል ግዕዝ ውስጥ የሌሉ ድምፆች አማርኛ ውስጥ እንዳሉ፣ ለአብነት ያህል ‹‹ቸ፣ ሸ፣ ጨ››ን መጥቀስ እንደሚቻል ገልጸው፣ ለእነዚህ ቃላት ካራክተር ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል፡፡
የአውሮፓ አልፋ ቤት ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ 1,500 ዓመት ድረስ ይቀያየር እንደነበር፣ ነገር ግን በአንድ ወቅት መጻፍና ማንበብ የማይችል የጀርመን ንጉሥ ሻልኔ በሙሉ ሊቆችን በመሰብበስ ለውጥ እንዲደረግ በማወጁ ሊቀየር እንደቻለ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በመድረኩ የፊደል መታሰቢያ ቀን እንዲኖር በተደረገው ምክክር ላይ ሐሳባቸውን ያቀረቡት ፖለቲከኛው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች አገሮች ሁሉ የሥልጣኔ መንፈስ አድሮባት እንድታደግ የሥልጣኔ መንፈሱ ሊኖራት ይገባል ብለዋል፡፡
አብዛኛዎቹ አገሮች አንድ ዓይነት ቋንቋ፣ ባህልና እምነት እንዳላቸው፣ ኢትዮጵያ ይህንን መሠረት በማድረግ በፍጥነት ወደ እነዚህ አገሮች ተርታ መሠለፍ እንዳለባት ገልጸዋል፡፡
በተለይም የኢትዮጵያ ከያኒያንም ሆኑ ደራሲዎች የዚህን እውነታ ሰፋ አድርገው እንደማይጽፉ ጠቅሰው፣ ይህንንም ሙከራ ተግባራዊ አድርጎና ሰፋ አድርጎ የጻፈው መሳይ ከበደ (ፕሮፌሰር) ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ላይ እየተጠቀመችበት ያለው የግእዝ የፊደል ገበታን ለማዳን ከፍተኛ አስተዋጽኦ መደረጉን፣ በጣሊያን ወረራ ወቅት ኢትዮጵያ ሽንፈት ቢገጥማት ኖሮ፣ የሌሎችን ቋንቋዎች ፊደል ተከታይ እንሆን ነበር ሲሉ አስረድተዋል፡፡