በአዲስ አበባ ከተማ መሀል ፒያሳ፣ አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ እየተካሄደ ያለው ታሪካዊው የዓድዋ ሙዚየም ዜሮ ኪሎ ሜትር ግንባታ መከናወን ከጀመረ ሦስት ዓመት ሆኖታል፡፡ አብዛኛው ግንባታ ቢጠናቀቅም አሁን ላይ የመጨረሻ (ፊኒሺንግ) ሥራ ይቀረዋል፡፡ የመጨረሻው ሥራ ደግሞ ሁሉንም አካታች በሆኑ የሥነ ጥበብ ሥራዎች የታነፀ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትልልቅ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት በሥነ ጥበብ ላይ ያተኮሩ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ኅዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ያካሄደውን የምክክር መድረክ ከተሳተፉ ታዳሚዎች መካከል፣ አንዳንዶቹ ከሰጡት አስተያየት ለመረዳት እንደተቻለው የማጠቃለያ ሥራ ሥነ ጥበብ የተሞላበት እንዲሆን ማድረግ ከተፈለገ፣ የሕንፃውን ዙሪያ በመስታወት እንዲጋረድ ከማድረግ ይልቅ ድንጋይ ልጥፍ ቢሆን ተመራጭ ነው፡፡
ድንጋይ ልጥፍ እንዲሆን ያስፈለገበትም ምክንያት የአየር ሁኔታውን ከመቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሪን ከማዳን፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድልን ከመፍጠር፣ የኅብረተሰቡን ተሳትፎና አንድነት ከማንፀባረቅ አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው በመገንዘብ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ለልጥፍ የሚውሉ ድንጋዮች የሚሰበሰቡት ከየክልሎች እንዲሆን፣ ክልሎችም የየራሳቸው ዓይነት ድንጋዮች እንዳላቸው፣ እነዚህን የመሳሰሉ ድንጋዮች በተፈለገው ግንባታ ላይ ሲለጠፍ ለሥነ ጥበቡ መሸብረቅና ማማር አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ፣ ይህ ሁኔታም የኅብረተሰቡን አንድነትና ተሳትፎ እንደሚያሳይ፣ ለአገረ መንግሥቱ ፅናት ያበረከቱት አስተዋጽኦ አካታችነት መንፈስን ሊያመጣ እንደሚችል ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል የኢትዮጵያ ቅርፃ ቅርፅና ሠዓሊያን ማኅበር አባል አቶ ወንድወሰን ከበደ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በከተማ አስተዳደር በጀት ይገንባ እንጂ፣ ታሪካዊ ዳራው አገርንና አኅጉርን የሚወክል ስለሆነ፣ የኪነ ሕንፃ ጥበብ ታሪካዊ ዳራውን ያማከለ ሆኖ በጥንቃቄ ሊከናወን ይገባል፡፡
የዓድዋ ዜሮ ፕሮጀክት እየተገነባ ያለው የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ውስጥ እስከሆነ ድረስ፣ የአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ሐሳብ በማፍለቅም ሆነ በሌላ ነገር የሚያስተላልፍበት መንገድ ሊመቻችላቸው እንደሚገባ፣ ይህም ሁኔታ በአፍሪካውያን ወንድሞች መካከል ኅብረትን እንደሚፈጥር፣ ከተማዋንም የሥነ ጥበብና የፋሽን ማዕከል ከማድረግ አንፃር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት አቶ አሰፋ በአሁኑ ጊዜ የዓድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ግንባታ ፕሮጀክት እየተከናወነ ያለበት ቦታ፣ ለዘመቻው የታለፈበት የዓድዋ ድልድይ በአጠቃላይ አዲስ አበባ ከተማና የአገሪቱ መሪዎች ይኖሩባቸው የነበሩ ቤቶች በ1880ዎቹ የነበራቸው ገጽታ ምን ይመስሉ እንደነበር የሚያሳዩ ፎቶግራፎቹ በሙዚየሙ ቢካተቱ ለሚቀጥለው ትውልድ ጥሩ ማሳያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
ከሙዚየሙ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ባህላዊ ዕቃዎች ለጎብኚዎች ማሳያና መሸጫ ክፍሎች፣ ለአካል ጉዳተኞች መወጣጫ የሚያገለግሉ ደረጃዎች ሊኖሩት እንደሚገባና የእሳት አደጋ መከላከያዎችንም ባካተተ መልኩ መከናወን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
አሁን በመሠራት ላይ ያለው ሙዚየም የጠራ፣ ሁሉንም የሚያካትት፣ የሚቀበለውና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ ከሆነ ውጤቱ ለሁሉም እንደሚጠቅም የገለጹት በሙዚየም ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ባልደረባ አቶ መሐመድ አህመድ ናቸው፡፡
‹‹ዛሬ ባለንበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ለመበተንና ሕዝቦቿን ለመከፋፈል ለሚሠሩና ለሚያሴሩ ወገኖች አንዱ መንገድ ከፋች፣ የቀድሞ ታሪካችን በተዛባ መልኩ በመሠራቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በሙዚየሙ ውስጥ የአሥር ጀግኖች ስም ዝርዝር ተለጥፎ መታየቱ አንድ ቁምነገር ቢሆንም፣ ስማቸው በትክክል መጣራት እንዳለበትና አቀማመጡም ቅደም ተከተላቸውን የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ መልካም መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡
ለምሳሌ ያህል ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ በታሪክ ጎልተው የሚታወቁበት ‹‹አባ መላ›› የተባለው ቀርቶ ‹‹አባ መቻል›› በሚል ተጽፎ ለዕይታ ቀርቧል፡፡ ይህም ሁኔታ በአስቸኳይ መታረምና በትክክለኛው መጠሪያቸው መተካት እንዳለበት አስተያየት ሰጪው ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ዓድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ከተባለው መነሻ ተነስቶ፣ በቀጥታ ሄዶ ዓድዋ ላይ የተዋጋበት ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት አስተያየት ሰጪው አመልክተው፣ ፍልሚያው ቦታ እስከሚደረስ ድረስ ብዙ ውጣ ውረዶች እንዳለፉ፣ ጦሩ የተገናኘበት ቦታ ወረኢሉ፣ ከዚያም የአሸንጌና የመቀሌ ጦርነቶችንም አልፎ መንቀሳቀሱን የሚጠቁሙ መረጃዎች በአግባቡ መያዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሁሉም ጦር ወደ ፍልሚያው እንዳልተንቀሳቀሰ፣ በተለይ የእነ ኩምሳና የእነ አባ ጅፋር ጦር ሸዋ ከመጣ በኋላ አፄ ምኒልክ፣ ‹‹ሁላችንም ሄደን አገርን ባዶ ልናደርገው ነው፡፡ ስለሆነም የመጣው ጦር ወደ መጣበት ተመልሶ አካባቢውንና ምዕራብ ኢትዮጵያን ይጠብቅ፤›› ብለው፣ እንዲመለሱ ማድረጋቸው በሙዚየሙ ውስጥ ቦታ ሊኖረው እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
ዓድዋ የዘመተው ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለው ሁሉም ሕዝብ ነው፡፡ ስለሆነም የተገኘውም ድል የጋራ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ጭፈራውና ፉከራው ወይም ወኔ ቀስቃሽ ዜማዎች ሁሉ የሁሉንም ብሔረሰብ የሚገልጹ መሆን አለባቸው፡፡ ሙዚየሙ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው እንደመሆኑ መጠን፣ መግለጫዎቹ ላይ የሚጻፉባቸው ቋንቋዎች አገራዊ ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢንተርናሽናል ቋንቋዎችም ቢካተቱበት እንደማይከፋ ነው የገለጹት፡፡
የዓድዋ ታሪክ በሙዚየም እንዲቀመጥ ተደርጎ፣ ጣሊያን ደግሞ ሁለቴ ነው የወረረችን፡፡ ታዲያ ሁለተኛውን ምን እናድርገው? በአንደኛው ብቻ ይበቃል ብለን እንተወው? ወይስ ለሁለተኛውም ወረራ ማሳያ የሚሆን ሌላ ፕሮጀክት እንቀይስ? በማለት አስተያየት ሰጪ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹የመቀየሱ ጉዳይ ቢታሰብበት ጥሩ ነው፤›› ሲሉም አስተያየታቸውን ደምድመዋል፡፡
የትልልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅና የምሕንድስና ዘርፉ ኃላፊ ምሬሳ ልኬሳ (ኢንጂነር)፣ የዓድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት የሆነው የሕንፃ ግንባታ 11 ብሎኮች እንዳሉት፣ አጠቃላይ የመሬቱ ስፋት 12 ሔክታር መሬት ሆኖ ሕንፃው ያረፈው ደግሞ 3.3 ሔክታር መሬት ላይ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
‹‹የጋራ የሆነው ታሪካዊ ገድላችንን የምንዘክርበት የዓድዋ ሙዚየም፣ ከአገራችን ታሪካዊ ቅርስነት ባሻገር የመላው ጥቁር አፍሪካውያን ንቅናቄ የሚታወስበት ግዙፍ የታሪክ ቅርስ እንደመሆኑ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የጎላ ሙያዊ አበርክቶ እንዲያደርጉ ይፈለጋል፤›› ብለዋል፡፡
4.6 ቢሊዮን ብር የተበጀተለትና ግንባታው በመስከረም 2012 ዓ.ም. የተጀመረውን ይህን ፕሮጀክት በተቋራጭነት ቻይና ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ኩባንያና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮንስትራክሽን ቢሮ በባለቤትነት እያከናወኑት የሚገኝ ሲሆን፣ የቻይናው ተቋራጭ የግንባታ ዲዛይኑንና ግንባታውን በ730 ቀናት ውስጥ ሠርቶ በመስከረም 2014 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ ውል እንደገባ ይታወሳል፡፡
የዓድዋ ሙዚየም ዜሮ ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ ከ2,000 እስከ 4,000 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት፣ የተለያዩ ቢሮዎች፣ ካፍቴሪያና የመሳሰሉትን አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች፣ የቤት ውስጥ ስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ የአውቶቡስና የታክሲ መናኸርያ፣ እንዲሁም ከሕንፃው ውጪ የቴአትርና የዓውደ ርዕይ ማሳያ ቦታዎች እንደሚኖሩት ተገልጿል፡፡