Wednesday, September 27, 2023

በቻይና የ‹‹ዜሮ ኮቪድ ስትራቴጂ›› ያስነሳው ተቃውሞ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ቻይና እ.ኤ.አ. በ2019 ለተነሳው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መነሻ ብትሆንም፣ ወረርሽኙን ፈጥና በመቆጣር ረገድ ከሌላው ዓለም በተሻለ ግቧን መትታለች፡፡ በተለይ ወረርሽኙ የተቀሰቀሰባትንና የ11 ሚሊዮን ቻይናውያን መኖሪያ የሆነችውን ውኃን ከተማ ሙሉ ለሙሉ በመዝጋት የኮቪድ-19 ሥርጭትን የተከላከለችበት መንገድ ዓለምን ያስነደቀም ነበር፡፡

ቻይና የውኃን ከተማን ሙሉ ለሙሉ በመዝጋት የኮቪድ-19 ሥርጭትን የተቆጣጠረችበትን መንገድ የአገሪቱ ‹‹ዜሮ ኮቪድ ፖሊሲ›› አካል በማድረግ እየተገበረችውም ትገኛለች፡፡ ሆኖም ሰዎችን እንደፍላጎታቸው የማያንቀሳቅሰው ፖሊሲ አሁን ላይ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡

የቻይና ‹‹ዜሮ ኮቪድ ፖሊሲ›› በአገሪቱ በቫይረሱ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከምዕራቡ ዓለም ሲነፃፀር ዝቅተኛ እንዲሆን አስችሏል፡፡ የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ሪሶርስ ሴንተር መረጃ እንደሚያሳየውም፣ ቻይና ካላት 1.4 ቢሊዮን ሕዝብ በኮቪድ-19 የሞተባት 16 ሺሕ ገደማ ሲሆን፣ በቫይረሱ ክፉኛ የተመታችው አሜሪካ ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሞት አስመዝግባለች፡፡

ቻይና የቫይረሱን ሥርጭት የተቆጣጠረችበት ምክንያት ደግሞ በዜሮ ኮቪድ ፖሊሲ የተካተቱት የጅምላ ምርመራ በቫይረሱ የተያዙትን በመንግሥት ተቋማት ኳራንታይን አድርጎ ማስቀመጥ እንዲሁም ቫይረሱ የበዛባቸውን አካባቢዎችና ከተሞች ሙሉ ለሙሉ በመዝጋቷ ነው፡፡

የኮቪድ-19 ክትባት መስጠት ከተጀመረና ወረርሽኙም ከቀነሰ በኋላ ቻይና ይህንኑ ፖሊሲዋን ከመተግበር አልተቆጠበችም፡፡ ሰሞኑን መልሶ ያገረሸውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከትሎም ፖሊሲውን አጠናክራ መተግበር ጀምራለች፡፡ ሆኖም ይህ በቻይናውያን ዘንድ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡

አልጀዚራ እንደዘገበው፣ በቻይና በተለያዩ ከተሞች ቻይናውያን ጠንካራውን የኮቪድ-19 ገደብ በመቃወም ወጥተዋል፡፡ ለተቃውሞ መነሻ የሆነው ደግሞ በምዕራብ ዣንጃንግ በምትገኘው ኡራምኪ በአንድ ሕንፃ ላይ በተነሳው የእሳት አደጋ አሥር ሰዎች በጭስ ታፍነው ሕይወታቸውን ማጣታቸው ነው፡፡

ተቃውሞ አድራጊዎች ለኮቪድ-19 በተጣለው ገደብ ምክንያት የእሳት አደጋ ሠራተኞች አደጋው ከደረሰበት ሥፍራ መደረስ ባለመቻላቸው ሰዎች ሞተዋል ቢሉም፣ ባለሥልጣናት ሕንፃው በመቆለፉ እንደሆነ አሳውቀዋል፡፡

የተወሰኑ ዜጎች ቤጂንግን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ገደቡን ተቃውመው ሠልፍ ቢወጡም፣ ይህ በዜሮ የኮቪድ ፖሊሲ የተከለከለ በመሆኑ በፖሊስ እየተወሰዱ እንደሆነም ዘገባው ያሳያል፡፡

ቻይና ከሦስት ዓመታት በፊት ከተከሰተባት ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኦሚክሮን ቢኤፍ.7 የተባለው ዝርያ በብዛት ይገኛል፡፡ ስለሆነም ለቻይና መንግሥት የዜሮ ኮቪድ ፖሊሲን መተግበር ግድ ነው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቻይና አምባሳደር ዣንግ ጁን እንደሚሉትም፣ ቻይና የዜሮ ኮቪድ ፖሊሲን ልትተው አትችልም፡፡

‹‹አንዳንድ አገሮች ሕዝባቸውን መስዋዕት አድርገው በሌላ አቅጣጫ ተጉዘዋል፡፡ በርካታ ሰዎችም ሞተውባቸዋል፡፡ እኛ ይህንን ማየት አንፈልግም፡፡ ሰዎች ነፃነትን ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ሲሆን ለመሞትም መዘጋጀት አለባቸው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

በቻይና ሰሞኑን ያገረሸው ኮቪድ፣ ካለፉት ጥቂት ቀናት ጋር ሲነፃፀር የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም አሁን ላይ ከ38 ሺሕ በላይ ዜጎች በኮቪድ መያዛቸውን የቻይና ብሔራዊ የጤና ኮሚሽን ይገልጻል፡፡

ቫይረሱ በቅርቡ ከተቀሰቀሰ ወዲህም ዕድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ የሆኑ ሰባት ሰዎች ሞተዋል፡፡ በቻይና አዛውንቶች ከሌላው ዜጋ ሲነፃፀር የክትባት ተደራሽነታቸው ዝቅተኛ ሲሆን፣ ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ የሆኑትም እነሱ ናቸው፡፡ ቻይናም የዜሮ ኮቪድ ፖሊሲን እተገብራለሁ ከምትልበት ምክንያት አንዱ በዕድሜ የገፉ ሰዎች አለመከተባቸውን በመግለጽ ነው፡፡

የቻይና ባለሥልጣናት የዜሮ ኮቪድ ፖሊሲን የሚያስተካክሉ መሆኑን ቢገልጹም፣ ይህ ግን ክትትሉና ቁጥጥሩ ይላላል ወይም ይነሳል ማለት እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡

አገልግሎት አቅራቢዎችና ትራንስፖርት ሰጪዎች በኡራምኪ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን፣ ከከተማዋ ወደ ሌሎች ከተሞች የሚደረግ በረራም ቀጥሏል፡፡

19 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት ጉዋንዚሁ ከተማ ደግሞ አዛውንቶችና በበይነ መረብ ትምህርት የሚከታተሉ ተማሪዎች ከቤታቸቸው የማይወጡ ከሆነ በየቀኑ የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግ እንደማይጠበቅባቸው ተነግሯል፡፡

ከተሞች ኮቪድ ያለባቸው ሰዎች ሳያስይመዘግቡ አምስት ቀናት ካሳለፉ፣ ለነዋሪዎቻቸው የኮቪድ የጅምላ ምርመራ አስገዳጅ እንደማይሆንም ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -