- ለብሔራዊ ፈተና የሚያገለግሉ አንድ ሚሊዮን ታብሌቶች በአገር ውስጥ ሊመረቱ ነው
ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ በትምህርት ሚኒስቴር ይዘቱ ተዘጋጅቶ ለሁሉም ክልሎች በየቋንቋቸው ተተርጉመው የተላኩ አዳዲስ ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል የመማርያ መጻሕፍት ለማሳተም፣ ክልሎች 29 ቢሊዮን ብር እንደሚፈልጉ ሚኒስቴሩ አስታወቀ፡፡
ይህ የተገለጸው የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተቋማቸውን የ2015 ዓ.ም. ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ኅዳር 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ከአንድ ቋት የተቀዳ ተመጣጣኝና ተመሳሳይ የሆነ የትምህርት ሥርዓት ለማዘጋጀት ሚኒስቴሩ ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ሕጋዊ ውክልና ተቀብሎ ይዘቱን አጠናቆ በ2014 ዓ.ም. ለክልሎች ቢልክም፣ መጻሕፍቱ የሚታተሙበት ገንዘብ እጥረት ማጋጠሙን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መማሪያና ማስተማሪያ መጻሕፍትን የማሳተም ግዴታ እንደሌለበት የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ክልሎች በአገር ውስጥ ለማሳተም የገንዘብ እጥረት እንዳለባቸውና የማተሚያ ቤቶች አቅም ውስንነት መኖሩን፣ እንዲሁም በውጭ አገር ለማሳተም ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በማጋጠሙ መጻሕፍቱን ለተማሪዎች ማድረስ እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ23 ሚሊዮን በላይ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንደሚኖሩ፣ የአንድ መጽሐፍ ኅትመት ዋጋ በአማካይ 300 ብር መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የመማሪያና የማስተማርያ መጻሕፍ አዘጋጅቶና አሳትሞ የማድረስ ኃላፊነት የትምህርት ሚኒስቴር ቢሆንም፣ ለማሳተም ግን የገንዘብ እጥረት ማጋጡሙ ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የሚያገለግሉ አንድ ሚሊዮን የኮምፒዩተር ታብሌቶችን፣ በአገር ውስጥ ለማስመረት መታሰቡን የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ ፈተና ስርቆት የትምህርት ሥርዓቱን በማዳከምና ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ በመፍጠር ለአገሪቱ ሥጋት መትከሉ የተገለጸ ሲሆን፣ ወደፊት ለስርቆት የማያመች ፈተና የሚሰጥበትን መንገድ እየተቀየሰ መሆኑን ኃላፊዎቹ አክለዋል፡፡
አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት የተነገረለትን የ2014 ዓ.ም. የብሔራዊ ፈተና፣ ‹‹አንዳንድ አካላት ውድ ነው በሚል ቅሬታ ሲቀርቡ ሰምቻለሁ፤›› ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በውድነት ምክንያት ይህን ችግር አለመቀየርን የሚያክል አገርን ውድ የሆነ ነገር የሚያስከፍል ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡ በዚህም ከፈተናው ከተገኘው ጥሩ ውጤት አንፃር የወጣው ገንዘብ ትንሽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ለፈተና ስርቆት የወጣውን ገንዘብና ካጋጠሙ የፀጥታ ችግሮች አንፃር ችግሩን መፍታት የሚቻለው፣ ፈተናውን በዲጂታል መንገድ ማከናውን ሲቻል ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም የነበሩትን አሠራሮች ሊቀይሩ የሚችሉ የፈተና አሰጣጥ መንገዶችን መቀየሱን ተናግረዋል፡፡
የመጀመርያው ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ታብሌት ኮምፒተሮችን ከውጭ አገር በውጭ ምንዛሪ ገዝቶ ማስገባቱ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ታብሌቶቹን በአገር ውስጥ ለማምረት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር ማምረት ስሚቻልበት ሁኔታ ውይይት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም የታብሌት የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ውይይት በማድረግ፣ ፋብሪካ ለማቋቋምና ወደ ሥራ ለመግባት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ፋብሪካው ተገንብቶ ምርቱን በግንቦት ወር ለሚሰጠው ብሔራዊ ፈተና ስለመድረሱ እርግጠኛ አይደለሁም፤›› ያሉት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ ታብሌቶቹ በ2016 ዓ.ም. ለሚሰጠው ፈተና እንደሚደርሱ ተሰፋ እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ፈተናውን በኦንላይን ለመስጠት የሚያስችል የሶፍትዌርና የሲስተም ማበልፀግ ሥራ፣ በዘርፉ ሙያ ካዳበሩ ከዳያስፖራ ኢትዮጵውያን ጋር በመነጋገር መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ተማሪዎች በተማሩበት ትምህርት ቤት ይሰጥ የነበረውን የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሰቲ መግቢያ ፈተና ስርቆትን ለማስቀረት የ2014 ዓ.ም. መልቀቂያ ፈተና፣ የፈተናውን አሰጣጥና ደኅንነት የሚቆጣጠር በዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የሚመራ ግብረ ኃይል በማቋቋምና ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲ በማጓጓዝ ፈተናውን በተለየ መንገድ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲሰጥ መደረጉ ይታወሳል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተከናወነውን ብሔራዊ ፈተና ለመፈተን ከተመዘገቡ 595,700 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች 586,541 ለፈተና ሲቀመጡ፣ 9,159 ተማሪዎች በፈተና ጣቢያ አለመገኘታቸውን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ በማኅራዊ ሳይንስ ለፈተና ከተመዘገቡት 352,622 ተማሪዎች ውስጥ፣ 350,505 ተማሪዎች ለፈተና ሲቀመጡ 2,117 በፈተና ጣቢያ አለመገኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ፈተናውን ለማከናወንና ቁሳቁስ ለማሠራጨት 54 የቻርተር አውሮፕላን በረራ ማድረጉን፣ 6,790 የፖሊስ አባላትን ማሰማራቱንና የፈተና ጣቢያ ማዕከላት ኃላፊዎች፣ አስተባባሪዎች፣ የጣቢያ ኃላፊዎች፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ ፈታኞች፣ ለዓይነ ሥውራን አንባቢና የፈተና ቆጣሪን ጨምሮ ከ25,700 በላይ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
በፈተናው ወቅት አንፈተንም ያሉ ከ13 ሺሕ በላይ ተማሪዎች እንዳሉና በፈተና ወቅት በሕመምና በጭንቀት ምክንያት 141 ተማሪዎች ሳይፈተኑ መቅረታቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ፈተና ጥለው የወጡ ተማሪዎች በመጪው የፈተና ጊዜ በግላቸው መፈተን እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
በፈተናው ወቅት 70 ተማሪዎች መውለዳቸውን፣ በትራንስፖርት ወቅት በተፈጠረ ድንገተኛ ሕመም ያጋጠመ ሞት፣ በፈተና ወቅት በተኩስ ሕይወቱ ያለፈ ፖሊስ፣ በትራፊክ አደጋ የተከሰተ የተማሪ ሞት፣ እንዲሁም በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተከሰተ የድልድይ መደርመስ ጨምሮ የሞት አደጋዎች ማጋጠማቸውን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹በፈተናው ወቅት ችግሮች አጋጥመውናል፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በተለይም ሞባይል ስልክ በፀጉርና በጫማ ውስጥ፣ ጥይት፣ ዱላ፣ አረቄና ጫት ወደ ፈተና ጣቢያ ይዘው ለመግባት ሲሉ የተያዙ ተማሪዎች፣ እንዲሁም አባት ለልጁ ለመፈተን የተደረጉ ሙከራዎች ማጋጠማቸውን አስረድተዋል፡፡
በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ በተደረመሰ ድልድይ 231 ቀላል፣ 201 መካከለኛ፣ 13 ከፍተኛ፣ አምስት በጣም ከፍተኛ ጉዳትና የአንድ ተማሪ ሞት ማጋጠሙን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡