ኮሚሽኑን ለመርዳት ገንዘብ በሻንጣ ይዞ መሄድ አያስፈልግም ተባለ
ከተቋቋመ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀሩት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማካሄድ ያቀደውን የምክክር ሒደት እንዲያመቻቹለትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶችን ለመክፈት፣ በአገሪቱ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ኮንሰርቲየም ጋር ለመሥራት የስምምነት ማዕቀፍ እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውን ሥራዎች አስመልክቶ ማክሰኞ ኅዳር 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) ከሌሎች ኮሚሽነሮች ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤቶች በኢትዮጵያ ከሚገኙ 48 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከትግራይ ክልል ውጪ ካሉት ዩኒቨርሰቲዎች ጋር በቅርቡ የመግባቢያ ስምምነት የሚያደርግ መሆኑን፣ ይህ ስምምነትም የዩኒቨርሲቲዎቹን ካምፓስና በውስጣቸው ያለውን ዕምቅ የሰው ኃይል ለመጠቀም ያግዛል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች የሁሉንም ብሔረሰቦች ማንነት የሚወክሉና ‹‹ትንሿ ኢትዮጵያ›› በመሆናቸው፣ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ ምሁራንንና ወጣቶችን በአወያይነት መጠቀም መቻል የአካባቢን ሥነ ልቦናና ቋንቋ በቀላሉ ከመገንዘባቸው ባለፈ ምክክሩን በገለልተኛ በመምራት የኮሚሽኑን ሥራ ያቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ መስፍን (ፕሮፌሰር) አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ምክክሩን ማድረግ የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ከማድረጉም በላይ፣ የሚከፈቱት ጽሕፈት ቤቶች በቀጣይ የኮሚሽኑ ሥራ ተጠናቆ ወደ አዲስ ምዕራፍ ቢገባ ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ በሰላም፣ በተግባቦትና ችግሮች ከመፍታት ዕሳቤ ዙሪያ ማዕከላት ሆነው እንደሚቀጥሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
አገራዊ ምክክሩን ተቀባይነትና ተዓማኒነት ባለው መንገድ ለማከናወን፣ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዓውዶችን ለመረዳት፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ወካይ በሆነና ከተለመደው የመንግሥት መዋቅር ወጣ ባለ መንገድ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖትና ከጎሳ መሪዎች፣ ከአባገዳዎች፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከሰላም እናቶች፣ ከሚዲያ ተቋማትና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር ትውውቅ ማድረጉን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ውጪ ባሉ ሁሉም ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በአገራዊ ምክክሩ ዙሪያ ትብብር ለማድረግ፣ ከአመራሮቹ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡
በምክክሩ መሣሪያቸውን አስቀምጠው የሚመጡ የታጠቁ ኃይሎችን ጨምሮ፣ በትኛውም አካባቢ ያሉ ድምፃቸው ያልተሰማ ወይም የተገለሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚካተቱ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡
በበርካታ አገሮች ጠመንጃ ይዘው ወደ ጠረጴዛ የሚመጡ አካላት የሚያደርጉት ሒደት ድርድር እንጂ ውይይት ባለመሆኑ፣ አሸናፊና ተሸናፊ ሆነው እንደሚወጡ፣ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሊያደርገው ያቀደው የውይይትና ምክክር ሒደት ግን ሁሉም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት መሆኑን መስፍን (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከ40 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት የስምምነት ማዕቀፍ እያዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ፋይናንስ አቅርቦት ምንጭ ከመንግሥት በመሆኑ ‹‹የውጭ እጅ አናይም›› ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ሌሎች አካላት ገንዘብ ለመስጠትና ለመደገፍ ከፈለገጉ ኮሚሽኑ በገንዘብ ሚኒስቴር ባለው ቋት አማካይነት እንጂ ‹‹ገንዘብ በሻንጣ ወይም በሳምሶናይት ይዞ ወደ ኮሚሽኑ ይዞ መምጣት አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የተጠቀሰው በበርካታ አገሮች በተደረጉ የምክክር ሒደቶች የምክክር ኮሚሽኖች የተጠመዘዙትና እንቅፋት የመታቸው፣ የውጭና የአገር ውስጥ ጣልቃ ገብነት ሲበረታባቸው በመሆኑ እንደሆነ ዋና ኮሚሽነሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ የጠየቀውን 3.2 ቢሊዮን ብር በጀት ፓርላማው የመደበ መሆኑን፣ በተመሳሳይ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት 80 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡