አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት ያስችላሉ ያላቸውን ሁለት ዓይነት የክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ፡፡
ባንኩ ማክሰኞ ኅዳር 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል ይፋ ባደረገው ፕሮግራም እንዳስታወቀው፣ የክሬዲት ካርዶቹ ለሁለት የብድር ዓይነቶች የተዘጋጁ ናቸው፡፡ አንደኛው ደንበኞች ከተቀመጠላቸው የብድር ጣሪያ ውስጥ የተጠቀሙበትን የብድር መጠን በክፍያ ቀናቸው በሙሉ ተመላሽ የሚያደርጉበት ሲሆን፣ ሁለተኛው የክሬዲት ካርድ ደግሞ ተዘዋዋሪ (ሪቮልቪንግ) ብድር ዓይነት ሆኖ፣ ደንበኞች በየወሩ የተጠቀሙበትን የብድር መጠን የተወሰነ መቶኛ ተመላሽ እያደረጉ መጠቀም የሚያስችል እንደሆነ፣ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡
እንደ ባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገለጻ፣ የሪቮልቪንግ ብድር ዓይነት ደንበኞች በተጠቀሙበት መጠን በየወሩ ብድር እንዲዘዋወር የሚያደርግ ነው፡፡
በዕለቱ ይፋ የተደረገው የክሬዲት ካርድ አገልግሎት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር መሆኑን፣ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የመጀመርያውና ፈር ቀዳጅ ዕርምጃ እንደሆነ አቶ ፀሐይ አስታውቀዋል፡፡
የክሬዲት ካርድ አገልግሎት መጀመር በደንበኞች የብድር አወሳሰድና አመላለስ ሁኔታ ላይ በመመሥረት፣ ታማኝ ደንበኞችን ለመለየትና በአግባቡ ለማስተናገድ የሚያስችል እንደሆነም አገልግሎቱን በተመለከተ ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የባንኩ ክሬዲት ካርድ አገልግሎት በባንኩ ፖሊሲ መሠረት መሥፈርቱን ሊያሟሉ ለሚችሉ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ የተዘጋጀ እንደሆነ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አገልግሎቱም በአመልካቾቹ የመበደር አቅም ላይ በመመርኮዝ ጣሪያ ተበጅቶለት የሚሰጥ ነው፡፡ የአዋሽ ክሬዲት ካርድ ደንበኞች በንግድ ቦታዎች ክፍያ እንዲፈጽሙ፣ ከኤቲኤምና ከቅርንጫፎች በፖስ ተርሚናሎች ማውጣት የሚያስችልም ስለመሆኑ ተብራርቷል፡፡
ይህም ካርዱ የተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመፈጸም ከማስቻሉም በላይ፣ የብድር አገልግሎት አሰጣጡ ዘመናዊ፣ ምቹና የተሳለጠ እንዲሆን የሚያደርግ ሲሆን፣ ደንበኞችም የጥሬ ገንዘብ ዕጦት ሊያጋጥማቸው ስለሚችል ለአስቸኳይ ችግር ዋስትና እንዲኖራቸው የሚያግዝም ነው ተብሏል፡፡
ስለዚህ አገልግሎት ሪፖርተር ከባንኩ ያገኘው ተጨማሪ ማብራሪያ እንደሚያመለክተው፣ መሥፈርቱን የሚያሟላ አንድ ደንበኛ የሚፈልገውን የገንዘብ መጠን ሲበደር በክሬዲት ካርዱ ላይ በመሙላት መጠቀም የሚችለበት ነው፡፡
በክሬዲት ካርዱ ውስጥ የገባውን ብድር ደንበኛው ማንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ በየወሩ ወለድ እየታሰበበት ክፍያ ይፈጽማል፡፡
የሪቮልቪንግ ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኛ በካርዱ የተሞላለት ብድር እንዳለቀ፣ ወዲያው በቋሚነት እየተተካ የሚጠቀምበት አሠራር ነው፡፡
በተለይ ብሔራዊ መታወቂያ ለእያንዳንዱ ዜጋ መስጠት ከተቻለ፣ በክሬዲት ካርዱ የሚሰጠውን የብድር አገልግሎት ይበልጥ እንደሚያሳድገው ተገልጿል፡፡