Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የሃያ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ

በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የሃያ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ

ቀን:

በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በሦስት ወረዳዎችና በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን አንድ ወረዳ በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑና እስካሁንም የሃያ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ሰኞ ኅዳር 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ በተጠቀሱት አካባቢዎች በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የሞቱ ሰዎች ብዛት ሃያ መድረሱን አመልክተዋል።

ሪፖርተር ከወር በፊት ባቀረበው ዘገባ በኢትዮጵያ በተከሰተው ወረርሽኝ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ማረጋገጡ የሚታወስ ሲሆን፣ በወቅቱም የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ወረርሽኙን እየተቆጣጠረው መሆኑን ለሪፖርተር ገልጾ ነበር።

ከአንድ ወር በፊት በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት የኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ወሰን፣ በሶማሌ ክልል ውስጥ የተያዙት 17 ሰዎች መሆናቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ አምስት ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ የአራቱ ሰዎች ሕልፈት ያጋጠመው ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ሦስቱ ወረዳዎች ውስጥ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡

የተመረዘ ውኃን መጠቀም በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ወረርሽኙ ለመከሰቱ በምክንያትነት የተጠቀሰ ሲሆን፣ የውኃና የንፅህና አገልግሎት አቅርቦት ውስንነትና የንፅህና አጠባበቅ ጉድለት ወረርሽኙ ለመስፋፋቱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መገለጹ ይታወሳል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ጁጆሪክ በሰጡት መግለጫ ደግሞ፣ በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በሦስት ወረዳዎችና በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን እየተባባሰ በሚገኘው የኮሌራ ወረርሽኝ 500 የሚደርሱ ዜጎች መያዛቸውን፣ ከዚህም ውስጥ ሃያ ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በበሽታው የመያዝ ሥጋት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከአጋሮች ጋር በመሆን የውኃ፣ ንፅህናና ጤና አገልግሎት አቅርቦት ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ስቴፋን የገለጹ ሲሆን፣ በምዕራብ ኦሮሚያ የቀጠለው ግጭት ሰዎችን ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ በማድረጉ የዕርዳታ አቅርቦት ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ‹‹ተረድተናል›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር በጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝትና ምላሽ ኃላፊን የጠየቀ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ምላሽ መስጠት  እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነትና ቡድን መሪ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ሊሳካ አልቻለም፡፡

ከወር በፊት በቀረበው የሪፖርተር ዘገባ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክተሩ ወረርሽኙ ወደ ሌሎች ክልሎች ሊዛመት ይችላል በሚለው ሐሳብ እንደማይስማሙ ገልጸው፣ ‹‹ወረርሽኙን እየተከታተለና ለጽሕፈት ቤቱ መረጃ እየሰጠ ያለው ኢንስቲትዩቱ ነው፡፡ በእኛ በኩል ያለው ግምገማ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንደሚስፋፋ አያሳይም፡፡ ባለፉት ተከታታይ ቀናት የተመዘገበ አዲስ ኬዝም የለም፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...