Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመምህራንና ሠራተኞች የመኖሪያ ቤቶች ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመምህራንና ሠራተኞች የመኖሪያ ቤቶች ሊገነባ ነው

ቀን:

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው በጀት ዓመት ለዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሠራተኞች የመኖሪያ ቤቶች እንደሚገነባ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው የራሱን አፓርታማ ገንብቶ ገቢ እንዲያመነጭ በአዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ አራት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ የተፈቀደለት ሲሆን፣ መምህራንና ሠራተኞች በአነስተኛ የኪራይ ክፍያ የሚገለገሉበት ባለ 15 ፎቅ ሕንፃ ለመገንባት መታቀዱን ፕሬዚዳንቱ ጣሰው (ፕሮፌሰር) ወልደሃና ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከመኖሪያ ቤቶች ሕንፃ በተጨማሪ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሚገነባ፣ ትምህርት ቤቶቹ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ሲሉ ጣሰው (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የቤት ኪራይ ችግር ለመፍታት ዩኒቨርሲቲው በዕቅድ ከያዛቸው መፍትሔዎች መካከል፣ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታና ዩኒቨርሲቲው የራሱን የገቢ ምንጭ የሚያገኝበት መንገድ መፍጠር ተጠቃሽ መሆናቸውን አክለዋል።

በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር የሚወሰነው የኪራይ ክፍያ መጠን ከመምህራን ወርኃዊ ደመወዝ የሚቆረጥ መሆኑን፣ የመኖሪያ ቤቶቹን የተረከቡ ሠራተኞችና መምህራን ጡረታ በሚወጡበትና ሥራ በሚለቁበት ጊዜ ለዩኒቨርሲቲው እንደሚመልሱ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ለጉዳዩ ቅርበት ያለቸው ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል።

ከሦስት ዓመታት በፊት ከከተማ አስተዳደሩ ለዩኒቨርሲቲው ከተፈቀደው 11.5 ሔክታር መሬት ውስጥ አራት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ብቻ የተረከቡ መሆኑን የተናገሩት ጣሰው (ፕሮፌሰር)፣ የተቀረው በዩኒቨርሲቲው ስም የሚገኘውን ይዞታ የአካባቢው አርሶ አደሮች ባለመልቀቃቸው መረከብ አልተቻለም ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ ለአርሶ አደሮቹ ተገቢውን ካሳ በመክፈል የተቀረውን ይዞታ ለዩኒቨርሲቲው እንደሚያስረክብ ቃል መግባቱን ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማኅበር በማደራጀትና በሌሎች አማራጮች ለዩኒቨርሲቲ መምህራን የሚያደርገውን የቤት አቅርቦት መቀጠል እንዳለበት ያስረዱት ጣሰው (ፕሮፌሰር)፣ የመኖሪያ ቤቶቹ የሚገነቡት በሥሩ የሚገኙ የአካዴሚክና የአስተዳደር ሠራተኞች ከፍተኛ ቁጥር በመድረሱና የውስጥ ገቢውን ለማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከራሱ 450 የመኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ ከ50 በላይ ቤቶች እንዲሰጡት ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል፡፡

‹‹ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሒደት ላይ ለመምህራን ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በማለት በዕቅድ የያዘው የመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ቀደም ያሉት የዩኒቨርሲቲው መምህራን ከከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ተረክበዋል። በተረከቡት ቦታ አንዳንዶች መኖሪያ ቤት ሲገነቡ አንዳንዶቹ ደግሞ ሸጠውታል። አሁን ላሉት የተቋሙ ወጣት መምህራን ደግሞ ቤት ማቅረብ አስፈላጊ ነው፤›› ሲሉ ጣሰው (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ለመጀመር የታቀደው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል። ዩኒቨርሲቲው ከአንድ ሺሕ በላይ የአካዴሚክና ከአራት ሺሕ በላይ የአስተዳደር ሠራተኞች እንዳሉት ይታወቃል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...