- በፍጥነት ይገድላል፣ በዝግታ ያሽከርክሩ›› ንቅናቄ ሊካሄድ ነው
የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ከዚህ በፊት ለጤና መድንና ለሞተ ሰው የሚከፈለው የካሳ ክፍያ እንዲሻሻል ጥናት አድርጎ መጨረሱንና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊያቀርብ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት በደንብ ቁጥር 493/2014 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ፀድቆ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ፣ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ ቢሆንም፣ ለጤና መድንና ለሞተ ሰው የሚከፈለው የካሳ ክፍያ አነስተኛ በመሆኑ የተነሳ፣ ክፍያው ላይ ማሻሻያ እንዲደረግበት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊያቀርብ መሆኑን ማክሰኞ ኅዳር 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ አብራርቷል፡፡
የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት የድህረ ትራፊክ አደጋ አገልግሎትና የመድን አስተዳደር መር ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጫላ ፈይሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተቋሙ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለጤና መድን ኢንሹራንስና ለሞተ ሰው ከሚከፈለው የካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ከጤና ተቋማት፣ እንዲሁም ተጎጂ ከሆኑ አካላት በኩል ቅሬታ ይቀርብበታል፡፡
ተጎጂ ከሆኑ አካላትም ሆነ ከጤና ተቋማት በኩል የሚቀርበውን ቅሬታ ለመመለስ፣ ተቋሙ በቂ የሆነ ጥናት አድርጎ ማጠናቀቁንና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊያቀርብ መሆኑን አቶ ጫላ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በማንኛውም ተሽከርካሪ ለተጎዳ ሰው እስከ 2,000 ብር ነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ የተደረገ ሲሆን፣ ባልታወቁና ሦስተኛ ወገን በሌላቸው ተሽከርካሪዎች ለተጎዱ ዜጎች ደግሞ 40 ሺሕ ብር ድረስ ሲከፈላቸው መቆየቱን አብራርተዋል፡፡
ለጤና መድንና ለሞተ ሰው የሚከፈለው የካሳ ክፍያ ላይ የሚደረገው የገንዘብ ማሻሻያ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ሲፀድቅ መሆኑን፣ ለጊዜውም የገንዘቡ መጠን ምን ያህል ነው የሚለውን እንደማይታወቅ ለሪፖተር አክለው ገልጸዋል፡፡
በፍጥነት ማሽከርከር ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ ንቅናቄን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አባሶ በበኩላቸው፣ በአፍሪካ በየዓመቱ 300 ሺሕ ሰዎች በትራፊክ አደጋ የሚሞቱ መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ለዚህ አደጋ ተጋላጭ የሚሆኑት ሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ናቸው፡፡
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ የትራፊክ አደጋ የሚከሰተው ፍጥነትን ምክንያት ባደረገ መልኩ መሆኑንና ይህንንንም ችግር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመቅረፍ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመንገድ ደኅንነት ምሰሶዎች ላይ ያተኮረ፣ ሁለተኛ የአሥር ዓመት ዕቅድ አዘጋጅቶ ሁሉም አገሮች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ስድስት የመንገድ ደኅንነት ምሰሶዎችን ያቀፈ የአሥር ዓመት ስትራቴጂ በመቅረፅ፣ የተለያዩ ተግባራቶችን እያከወናወነች መሆኑን፣ ፍጥነት ላይ ያተኮረ አሠራር ተዘርግቶ እየተሠራ እንደሆነ አክለዋል፡፡
ተቋሙም ‹‹ፍጥነት ይገድላል፣ በዝግታ ያሽከርክሩ!›› በሚል መሪ ቃል ለስድስት ሳምንት የሚቆይ አገር አቀፍ ንቅናቄ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡
በአገር አቀፍ ንቅናቄው ላይም ለትራፊክ አደጋ ዋነኛ መንስዔ በፍጥነት ማሽከርከር በመሆኑ የምሥል፣ የድምፅና ማስታወቂያዎች በበርካታ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሚተላለፉ መሆኑን በወቅቱ ተገልጿል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በፍጥነት ማሽከርከር ላይ ያተኮሩ መልዕክቶች በቢል ቦርዶ፣ በፓስተሮች፣ በስቲከሮችና በሌሎች ነገሮች በማስተላለፍ፣ ለአሽከርካሪውም ሆነ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ይሰጣል፡፡