Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት (ኢ-ፓስፖርትን) አገልግሎት ላይ ለማዋል፣ የቅድመ ዘግጅት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የፓስፖርት፣ የቪዛና የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎቶችን የሚሰጠው ተቋሙ፣ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በአገልግሎት ላይ ያለውን ፓስፖርት ወደ ኢ-ፓስፖርት ለመቀየር ዕቅድ መያዙ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ ፓስፖርት ዓይነት የራሱ የሆነ የተለየ መለያ ያለው በመሆኑ ለሕገወጥ ወንጀሎች የመዋል ዕድሉ ዝቅተኛ ይሆናል ተብሏል፡፡

የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት በላዩ ላይ ‹‹ቺፕስ›› (መረጃ የሚይዝ መሣሪያ) ተገጥሞለት በውስጡ የግለሰቦች መረጃ በተለያየ ሁኔታ የሚያስቀምጥ፣ ለሕገወጥ ሥራዎች በተለይም ለፎርጅድ የማያጋልጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህ አገልግሎት በሥራ ላይ መዋሉ የአንድ አገር ፓስፖርትን ደረጃ ከፍ የሚያደርግ እንደሆነ፣ ከዚህ ቀደም በመደበኛው ፓስፖርት የባር ቁጥር (ባር ኮድ) ተጠቅሞ የሚደረገውን የፍተሻና ማረጋገጥ ሥራ የሚያስቀር መሆኑን በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ የሕትመትና ሥርጭት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጌታቸው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ግንበቶ በበኩላቸው፣ በፎርጅድ ፓስፖርት እንዳይሠራ ለማድረግ የአሌክትሮኒክ ፓስፖርትን ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ፓስፖርት የሚታተመው በፈረንሣይ አገር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሰለሞን በበኩላቸው፣ ይህም በጥብቅ ቁጥጥር የሚከናወን በመሆኑ ጠንካራ ገጽታዎችን የተላበሰ ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዓለም ወደ ኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገልግሎት እየተቀየረ መሆኑን ያስረዱት የኅትመትና ሥርጭት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከጊዜው አንፃር አስገዳጅ ስለሆነና በአፍሪካ 40 ያህል አገሮች ፓስፖርታቸውን ወደ ኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት እየቀየሩ ስለሆነ፣ ኢትዮጵያም የምትጠቀምበትን ፓስፖርት ወደ ኢ-ፓስፖርት ለመቀየር የቅድመ ዝግጅትና የጥናት ሥራዎች እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለሚመለከተው አካል አገልግሎቱን ለማስጀመር የመጀመሪያ ዙር ጥናት ማቅረቡ የታወቀ ሲሆን፣ በቀጣይ በጀት ማስፈቀድ እንደሚቀረውና ያ ሲጠናቀቅ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ የኢ-ፓስፖርትን መተግበሯ ፎርጅድን ማስቀረት ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አገግሎቱን የተገበሩ አገሮች ዝርዝር ውስጥ እንድትገኝ የሚደርግና የፓስፖርቱን ደረጃ ከፍ እንደሚያደርግ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያን ተለምዷዊ የፓስፖርት አሰጣጥ ወደ የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ለማዘመን የሚያስችል የቴክኖሎጂ ውጤት፣ በቀድሞው የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ተዘጋጅቶ ከዚህ ቀደም ውይይቶች ሲደረጉበት እንደነበር ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገራዊ ደኅንነትን አጠናክሮ ለመጠበቅ፣ ሕገወጥ ስደተኞችን ለመቆጣጠርና ገቢን ለማሳደግ የሚያግዝ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች